ሳሙኤል ቦጋለ

October 18, 2023

የኢትዮጵያና የሊባኖስ መንግሥታት በቤይሩት የሥራ ሥምሪት ስምምነቱን በተፈራረሙት ወቅት

የኢትዮጵያና የሊባኖስ መንግሥታት የተፈራረሙትና በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የቤት ሠራተኞችን መብት ያስከብራል የተባለው ስምምነት፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊፀድቅ ነው፡፡

ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ከልዑክ ቡድናቸው ጋር በሊባኖሷ ዋና ከተማ ቤይሩት ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ፣ ከሊባኖስ የሥራ ሚኒስትር ሙስጠፋ ባይላን ጋር የተፈራረሙት ኢትዮጵያውያን ሠራተኞችን በሊባኖስ ቀጥሮ በማሠራት ላይ የተዘጋጀውን ስምምነት ነበር፡፡

ስምምነቱ ማክሰኞ ጥቅምት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. በፓርላማው ለማፀደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ፣ የምክር ቤቱ አባላት አስተያየት ሰጥተውበት ወደ የሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡

ሪፖርተር የተመለከተው ባለ 25 አንቀጾችና 20 ገጽ የሁለቱ አገሮች ስምምነት፣  ሠራተኞቹ መብቶቻቸው ተጠብቀውና አስተማማኝ የሥራ ሁኔታ ተመቻችቶላቸው እንደሚሠሩ ይደነግጋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች በግዳጅ የጉልበት ሥራ እንዳይሠሩ፣ በሕገወጥ መንገድ ፓስፖርታቸውን እንዳይነጠቁ፣ የመንቀሳቀስ መብታቸውንና የሥራ ደመወዛቸውን እንዳይነፈጉ፣ አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊና ፆታዊ ጥቃት እንዳይደርስባቸው የሊባኖስ መንግሥት ማረጋገጥ አለበት፤›› ይላል የስምምነቱ አካል የሆነው አንደኛው አንቀጽ፡፡

የሁለቱ አገሮች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ስምምነቱን የማስፈጸም ኃላፊነት የተሰጣቸው ሲሆን፣ ሠራተኞቹ ለግል ኤጀንሲዎች ሥራቸውን በተመለከተ ምንም     ዓይነት የገንዘብም ሆነ የዓይነት ክፍያ እንዳይፈጽሙ ሚኒስቴሮቹ ማረጋገጥ እንዳለባቸውም ተደንግጓል፡፡

የሠራተኞች የደመወዝ ክፍያንና የገንዘብ አላላክን በሚመለከት፣ ሠራተኞቹ በተቀጠሩ በመጀመሪያው ወር በስማቸው የባንክ አካውንት እንዲከፍቱና ገቢያቸውንም ወደ አገር ቤት እንደ ፍላጎታቸው እንዲልኩ ሙሉ መብት እንዲኖራቸው በስምምነቱ ተገልጿል፡፡

‹‹ደመወዛቸው ከመጀመሪያው ወር ጀምሮ ሊከፈላቸው የሚገባ ሲሆን፣ ከክፍያ ቀኑ ከአምስት ቀናት ባልበለጠ ሊዘገይ አይገባም፤›› ይላል ስምምነቱ፡፡

በሠራተኛው ፍላጎትና ጥያቄ መሠረት የደመወዝ አከፋፈሉ በስሙ በሊባኖስ ወይም በኢትዮጵያ በሚከፈት አካውንት ውስጥ፣ በሠራተኛው ለተመረጠ ተቀባይ ወደ ኢትዮጵያ ለማስተላለፍ፣ አልያም በሊባኖስ የሥራ ሚኒስቴር በተረጋገጠ ደረሰኝ መሠረት በጥሬ ገንዘብ ሊሆን እንደሚችል ተደንግጓል፡፡

የስምምነቱን ማፅደቂያ ረቂቅ አዋጅ ማብራሪያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በንባብ ያቀረቡ ሲሆን፣ አባላቱ አስተያየታቸውን አክለውበት ለውጭ ግንኙነቶችና ለሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል፡፡

በዕለቱ ስድስት አዋጆች ለምክር ቤቱ ቀርበው ሁለቱ ሲፀድቁ፣ አራቱን ለተጨማሪ ዕይታና ሐሳብ ለማከል ወደ ቋሚ ኮሚቴዎች ተመርተዋል፡፡