ሲሳይ ሳህሉ

October 18, 2023

ዓለም አቀፉ የቁም እንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት ግቢ ውስጥ የተካሄደው ውይይት የተቋማት ኃላፊዎች ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት በዲጂታል ዘዴዎች አካሄድኩት ባለው ጥናት መሠረት፣ የአገሪቱ መሬት ለምነት 40 በመቶ የሚሆነው አሲዳማ መሆኑ መረጋገጡ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያሳይ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር ይፍሩ ታፈሰ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ተቋማቸው ባካሄደው የአፈር ናሙና ጥናት መሠረት ከአጠቃላይ የአገሪቱ መሬት ከ40 በመቶ በላይ የሚሆነው በአሲድ የተጠቃ ነው፡፡

በዚህም የተነሳ ይህ በአሲድ የተጠቃ መሬት በምርትና ምርታማነት ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ቀላል የማይባል በመሆኑ፣ ይህንን አክሞ ወደ ለምነት መቀየር ትልቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ረገድ ከምርምር ተቋማት ጋር በቀጣይ አምስት ዓመታት መሬቱን አክሞ ወደ ሥራ ለማስገባት በጋራ እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአካባቢ ንብረት ለውጥ ላይ የሚሠሩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ግብ እንዲመቱ የሚሠራው አይክራ (AICCRA) የተሰኘው ድርጅት፣ ከ12 በላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልማት ተኮር ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ ድርጅቶችን ወደ አንድ በማምጣት ከሚሠራው ሲጂአር (CGIAR) የተሰኘ ድርጅት ጋር በመሆን በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ውስጥ የአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተስማሚ ቴክኖሎጂን ለመተግበር ያለመ አንቅስቃሴና ድጋፍ ከጀመሩ ሦስት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት የያዛቸውን የልማት ዕቅዶች በመመልከት የሚቀረፁ ፕሮጀክቶች የሚያስፈልጋቸውን የቴክኒክና የቴክኖሎጂ ድግፍ ማድረግን ያለመ መሆኑን የኢትዮጵያ አይክራ (AICCRA) ፕሮግራም መሪ ዳዊት ሰለሞን (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በዓለም አቀፍ የእንስሳት የምርምር ተቋም (ILRI) ቅጥር ግቢ ውስጥ የዘርፉ ተዋናኞችን፣ ዓለም አቀፍ የጥናትና ምርመር ተቋማት ተወካዮች፣ የግብርና ባለሙያዎች፣ አርሶ አደሮችና ሌሎችም በተገኙበት ውይይት ተካሂዷል፡፡ ውይይቱ እየተቀያየረ ከመጣው የአካባቢ አየር ንብረት ለውጥ ጋር ተስማሚ የሆነና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ የግብርና ሥርዓት መተግበር ላይ ያተኮረ መሆኑንም ዳዊት (ዶ/ር) አክለው ተናግረዋል፡፡

የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር እንደሚሉት እየጨመረ በመጣው የአካባቢ ንብረት ለውጥ ምክንያት ከዚህ በፊት የማይታወቁ የሰብል ተባዮች መፈጠራቸውን ጠቅሰው ‹‹እኔ በዕድሜዬ ጤፍን ተባይ ሲበላው ዓይቼ አላውቅም፤›› ብለዋል፡፡

የአየር ንብረት ለውጥ እስከ ስድስት በመቶ የመቀነስ አደጋ ይቀንሳል የሚሉት ይፍሩ (ዶ/ር) ከዓለም አቀፍ የጥናት ተቋማት ጋር በመሆን የሚገኙ የጥናት ውጤቶችን በመተግበር የመንግሥት አካል ብቻም ሳይሆን የግሉ ዘርፍ የልማት አካላቶች፣ የዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች ተቋማት በ2030 የተሸጋገረ ግብርና ዕውን ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ በቀጣይ የግብርናውን ዘርፍ በዲጂታል አማራጮች በማዘመን የአርሶ አደሩን የመረጃ ፍላጎት ተደራሽ የሆነ ሥርዓት መዘርጋት በአገሪቱ ባሉ ወደ 70 ሺሕ የሚደርሱ የልማት መረጃ ሠራተኞችን ድካም መቀነስ ይቻላል ብለዋል፡፡

የግብርና ዳታ ቋት ለመገንባት ለግብርና ሚኒስትሩ ቀርቦ እየተጠበቀ መሆኑን የገለጹት ምክትል ዳይሬክተሩ የዳታ ቋቱ ሲገነባ በተቀናጀ መንገድ አየር ለውጥን ከግብርና ጋር አጣጥሞ ለመሄድ ያስችላል ብለዋል፡፡

የትብብሩ ዓላማ ግብርናን የማሳደግ ተግባር ሲሆን፣ በመሠረታዊነት፣ ለዘርፉ ተዋናኞች የአቅም ግንባታ ሥራ፣ የአየር ንብረት ለውጥን በትምህርት ማካተት፣ የአየር ንብረት ትንባያን ማጠናከር፣ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ ዘመናዊ የግብርና ዘዴዎችን ለአርሶ አደር በተገቢው መንገድ የሚደርሱበትን መንገድ በመፍጠርና ወቅቱን የጠበቀ መረጃ በማሠራጨት ለኢትዮጵያ ግብርና አስተዋጽኦ ማበርከት ነው፡፡

አይክራ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ በስድስት አገሮች በጋና፣ በሴኔጋል፣ በማሊ፣ በዛምቢያና በኬንያ የሚሠራ ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ በማያደርገው ሥራ በአገር ውስጥ የሚገኙ ተቋማትን በማስተባበር ይሠራል፡፡

የማይክሮ ኢኮኖሚክስ ምሁሩ ዓለማየሁ ገዳ (ፕሮፌሰር) የአካባቢ አየር ንብረት ለውጥ በማይክሮ ኢኮኖሚው ላይ ቢያንስ በአራት መንገድ ተፅዕኖ ያሳድራል ይላሉ፡፡ ለአብነትም በኢትዮጵያ ቢያንስ 65 በመቶ የሚሆነውና በግብርና የሚተዳደረው የገጠር ሕዝብ የዝናብ መጠን ሲወጣና ሲወርድ ሙቀት ሲቀንስ የእህል ምርቱንም ይሁን የእንስሳት ልማቱን አደጋ ላይ ይጥለዋል ብለዋል፡፡

በሌላ መንገድ የዋጋ ንረት መባባስ፣ የውጭ ምንዛሪና እጥረት፣ የገቢ ምርት መቀነስ ከሚያደርሰው ጉዳት መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን ጠቅሰው መንግሥት የማይክሮ ፖሊሲን መነሻ ሲያደርግ የአካበቢ አየር ንብረት ለውጥን ግምት ውስጥ በማስገባት መሆን ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ዓለማየሁ (ዶ/ር) ከተቋማት አገኘሁት ባሉት መረጃ መሠረት ሲናገሩ አሁን ያለው የአየር ንብረት መጨመር በዚሁ ከቀጠለ በ2050 የኢትዮጵያ ምርት መጠን በ15 በመቶና የሚታረስ የእርሻ መጠን በ21 በመቶ ይቀንሳል ብለዋል፡፡