
Bedilu Wakjira
ቢያንስ በአጸያፊ ስሙ እንጥራው! (በድሉ ዋቅጅራ)
የመስዋእትነቱና የሰማእትነቱ ውጤት ምንድነው? የትግራይ፣ የአማራ . . . የኢትዮጵያ እናቶች እንባ!?
ስሙን አታሳምሩት! መስዋእትነትም፣ ሰማእትነትም አይደለም፡፡ በዚያ ጦርነት የተከበረ ድንበር፣ የተነሳ ሰንደቅ፣ የተመለሰ ነጻነት፣ የተረጋገጠ መብት፣ የተቀረፈ ድህነት፣ የለም፡፡ . . . . ልጆቿን ለተነጠቀች እናት ጠብ ያለ ነገር የለም፡፡ ከጦርነቱ ፍጻሜ በኋላ፣ እንደሀገርና እንደህዝብ ከጦርነቱ በፊት ከነበርንበት ጎድለን እንጂ ሞልተን፣ ደህይተን እንጂ በልጽገን አልተገኘንም፡፡ ያ ጦርነት የዘር ፖለቲካ የወለደው የእርስ በርስ መጨፋጨፍ እንጂ ሰማእትነትም፣ መስዋእትነትም አይደለም፡፡
ቢያንስ በአጸያፊ ስሙ እንጥራው፡፡ አጸያፊነቱን መቀበል ዳግም ላለመፈጸም የመጀመሪያ እርምጃ ነው፡፡ መጨፋጨፍን መስዋእትነትና ሰማእትነት እያሉ ማንቆለጳጰስ ከብሄር ተኮር የእርስ በርስ መጨፋጨፍ እንዳንወጣ ያደርገናል፡፡ አዲስ አይን ለማውጣት፣ አዲስ ሰላማዊ መንገድ ለመከተል ቢዘገይም ዛሬ እጃችን ላይ እድል አለ፤ መንግስት ከክልሎችና ከተለያዩ ቡድኖች ጋር የሚገጥመውን አለመግባባት ለመፍታት ሰላማዊ ድርድርን ብቸኛ አማራጭ ማድረግ አለበት፡፡ ጦርነት ይብቃን፤ የወጣቶች ሞት ይብቃን፤ የእናቶች ሙሾና እንባ ይብቃን፡፡
