· ልደቱ አያሌው
ጥቅምት 06 ቀን 2016 ዓ.ም
መግቢያ
ግጭትም ሆነ ጦርነት ቅራኔ ነው። ትርክት ለአንድ ግጭት ወይም ጦርነት መፈጠር ምክንያት ከሆነ በኋላም ባለበት አይቆምም።
ለተገባበት ጦርነት ለአሸናፊነት የሚያበቃ ዋና ግብዓት ሆኖ የበለጠ ተጋኖ እና ተጠናክሮ ይቀጥላል። በተለይም የሚካሄደው ጦርነት ከብሔር ወይም ከሃይማኖት ጋር ግንኙነት ካለው የሚካሄደው ትርክትና ፕሮፓጋንዳ ለእውነትና ፍትሃዊነት ቦታ አይኖረውም። ዋና ትኩረቱ “ጠላት” ብሎ የፈረጀውን አካል ስብዕና “ጭራቅ” አድርጎ በመሳልና ለአሸናፊነት በመብቃት ላይ ብቻ ይሆናል።በአሁኑ ወቅት በአገራችን እየተካሄደ ባለው ጦርነት በርካታ ብሔርተኞች ጆሴፍ ጉብልስን የሚያስንቁ ፕሮፓጋንዲስቶች ለመሆን ሲፎካከሩ እያየን ያለነው ያለምክንያት አይደለም። ፕሮፓጋንዳ አንድን ጦርነት አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት የማይተካ ሚና ያለው መሆኑን ስለሚረዱ ነው። ይህንን መረዳታቸው ችግር የለውም። ችግሩ ያለው “ማሸነፍ ማንን? እንዴት? አስከምን ድረስ? እና ለምን?” በሚሉት መሰረታዊ ጥያቄዎች ዙሪያ ጦረኛ-ብሔርተኞች እምብዛም ቦታ የማይሰጡ መሆናቸው ነው።አንድን ጦርነት ለማሸነፍ ከሚኖር የፍላጎት አድማስ ባሻገር የጦርነቱ ሂደትና የመጨረሻ ውጤት በአገርና በህዝብ ላይ ስለሚኖረው ትሩፋትና ጣጣ ለአፍታም ቆም ብሎ ለማሰብ የማይሞክር ያልተገራ ብሔር-ተኮር ትርክት በአገርና በህዝብ ላይ ከፍተኛ አደጋ ያስከትላል። በተለይም ዘር ወይም ብሔር-ተኮር ያልተገራ ትርክት እጅግ አሰቃቂና ዘግናኝ ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል በዓለማችን ጀርመንን፣ ዩጎዝላቪያንና ሩዋንዳን በመሳሰሉት አገሮች በገሃድ ታይቷል። በእኛም አገር ለሚሊዮኖች መፈናቀል፣ ሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ መደፈር፣ መሰደድ እና እልቂት ምክንያት በመሆን አሰቃቂ ገጽታውን ደጋግሞ እያሳየን ይገኛል። ይሁንና “ሁላችንም ሞተን ካላለቅን በቀር አናምንም” ብለን የማልንና የተገዘትን ያህል ችግሩን የበለጠ ዛሬም አጠናክረን ቀጥለንበታል።ከአሁን በፊት አንድን በስልጣን ላይ የሚገኝ መንግሥት “በህዝብ ስም” የመፈረጅ ትርክት ሲቀርብ የምናውቀው ስርዓቱን በሚቃወሙ ኃይሎች ቢሆንም በጥፋት ላይ ጥፋት መደረብ የማይታክተው የወቅቱ የዶ/ር ዐቢይ አገዛዝ ግን በታሪካችን አይተነውና ሰምተነው በማናውቅ ሁኔታ ራሱን በአንድ ብሔር መንግሥትነት በኩራት ፈርጆ የሚታይ ሆኗል። ይህ በራሱ ከችግሩ አዙሪት የመውጣት ሳይሆን ችግሩን የበለጠ የማባባስና የማወሳሰብ ሂደት ላይ መግባታችንን የሚያሳይ ነው። የዚህ መጣጥፍ ዓላማም እንዲህ ዓይነቱ በህዝብ ላይ የተሳሳተ ትርክት የማቅረብ አዙሪት አንድ ቦታ ላይ ካልቆመ በስተቀር በህዝብና በአገር የወደፊት ህልውና ላይ ሊያስከትል ስለሚችለው ከፍተኛ አደጋ የግል ዕይታዬን ለማጋራት መሞከር ነው። ምክንያቱም በእነዚህ ትርክቶች ዙሪያ ያሉብን የተካረሩ ልዩነቶች ካልረገቡና በተወሰነ ደረጃ የተቀራረበ አመለካከት ካልፈጠርን በስተቀር ወደ በጎ አቅጣጫ የመሸጋገርም ሆነ ከህልውና አደጋ የመዳን ዕድላችን እጅግ ጠባብ ስለሚሆን ነው።1. አጼ ምኒሊክ እና አጼ ኃይለስላሴ የመሩት ስርዓት የማን ስርዓት ነበር…?ከዘመነ መሳፍንት በኋላ አንሳና ተዳክማ የነበረችውን ኢትዮጵያ እንደገና የማስፋትና የማጠናከሩ ሂደት በአጼ ቴዎድሮስ እና አጼ ዮሃንስ ተጀምሮ ትርጉም ባለው መጠን የተሳካው በአጼ ሚኒሊክ ዘመን ነበር። አጼ ሚኒሊክ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የኢትዮጵያን ግዛት በተሟላ ሁኔታ ማስጠበቅ ሳይችሉ ቢቀሩም ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ያካሄዱት መስፋፋት ግን ውጤታማ ነበር ማለት ይቻላል። “ውጤታማ ነበር” የምለው በኃይል መስፋፋትን በመደገፍ ሳይሆን በእሳቸው ዘመን በኃይል ግዛትን ማስፋፋት በሌላው ዓለምም የተለመደና የአንድን መንግሥት ጥንካሬ የሚያሳይ የአገዛዝ ስልት ስለነበር ነው። በአጭሩ ኢትዮጵያ ከሞላ-ጎደል አሁን ላይ የያዘችውን መልከዓ-ምድራዊ ቅርጽ የያዘችው፣ የአድዋን ድል በመጎናጸፍ በዓለም ገናና ስም ለመያዝ የበቃችውና ከዓለም የቴክኖሎጂ ትርፋት ተቋዳሽ መሆን የጀመረችው በአጼ ምኒሊክ ዘመን ነበር።ከዚህ አንፃራዊ የንጉሠ-ነገሥቱ ውጤታማነትና ገናናነት ጋር በተያያዘ ሊሆን ይችላል፣ “ጭቆናና በደል ደርሶብናል” ብቻ ሳይሆን “ያለ ፍላጎታችን በኃይል የኤምፓዬሩ አካል ተደርገናል” ብለው የሚያምኑ ብሔርተኞች በዋናነት ሲወቅሱና ሲያወግዙ የሚታዩት ዳግማዊ አጼ ምኒሊክን ነው። እንደ አብዛኛው የዓለም ህዝቦች የአሁኑ ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሁላችንም እየኖርን ያለነው ራሳችን በገነባነው ሳይሆን ከነጥንካሬውና ድክመቱ በወረስነው አገር ቢሆንም ብሔርተኞች ግን ከሌላው ህዝብ በተለየ ጭቆናንና ድህነትን ለብቻቸው የወረሱ ይመስል በአለፉት ስርዓቶች ላይ የከሳሽነት ትርክት የማቅረቡን ድርሻ ለራሳቸው ወስደዋል። አሁን ላይም ይህንን የተሳሳተ ትርክት የሚቀበሉና በጨቋኝነት ተከሳሽ ከሆነው ወገን ዙሪያ የሚገኙ አንዳንድ ብሔርተኞችም ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። ማለትም አንዳንድ አክራሪ የአማራ ብሔርተኞች ላለፉት ስርዓቶች በተለየ ሁኔታ ተቆርቋሪና ጠበቃ ሆነው ከመቅረብም ባለፈ “የእኛ አባቶችና አያቶች አገር በመሩበት ዘመን” በማለት ራሳቸውን ያለፉት አገዛዞች ወራሽ አድርገው ለማቅረብና ለመመጻደቅ ሲሞክሩ እያየን ነው። አጼ ምኒሊክ ከሞቱ ከአምስት ትውልድ በላይ አልፏል። በእሳቸው ዘመን የነበሩ ጨቋኞችም ሆኑ ተጨቋኞች ዛሬ ላይ አንዳቸውም በህይወት የሉም። የዚያን ዘመን የታሪክ ምዕራፍ በሚዛናዊነት ማየትና በወቅቱ ስለተፈጸሙ በደሎች ሁላችንም ተገቢ እውቅና መስጠት፣ ተገቢ ፀፀትና ቁጭት ማሳትም ይጠበቅብናል። ከዚያ ውጭ በዚያ ዘመን ለተሰሩ በጎ ነገሮችና ጥፋቶች ዛሬ ላይ ማንም ተመስጋኝና ተሸላሚ ወይም ተወቃሽና ተቀጪ መሆን የሚገባው ብሔርም ሆነ ግለሰብ መኖር የለበትም። ከመብት አኳያ ችግር የሌለው ቢሆንም ማንም ብሔርም ሆነ ዜጋ ከሌላው ህዝብ በተለየ ሁኔታ በቀድሞዎቹ ስርዓቶች ተግባር ሊኮራም ሆነ ሊያፍር አይገባውም። የሚያኮራውም ሆነ የሚያሳፍረው የታሪካቸን ገጽታ የሁላችንም የጋራ ታሪክ ሆኖ መወሰድ ይኖርበታል።ከ50 ዓመት በፊት በስልጣን ላይ የነበሩትን ንጉሳዊ ስርዓቶች – ሲያንስ የአማራ ጨቋኝ መደብ፣ ሲበዛ ደግሞ የአማራ ህዝብ ስርዓት እንደነበሩ ተደርጎ የሚቀርበው ትርክት ተጨባጭ አመክንዮ ስለሌለው ሊቆም የሚገባው ነው። ይህንን ለማለት የሚያበቁን የሚከተሉት ምክንያቶች ናቸው።ሀ. በአንድ አገር ለስልጣን የበቃ አንድ መሪ ከአንድ ቤተሰብና ከአንድ አካባቢ መፈጠሩ የግድ ነው። ይሁንና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ባልነበረበት ዘመን ለስልጣን የበቃንና “ስዩመ እግዚአብሔር” ነኝ ብሎ የሚያምንን አንድ ንጉሳዊ የአገር መሪ የአንድ ብሔር ወኪል ወይም “ስዩመ-ብሔር” አድርጎ ለማየት መሞከር ከጅምሩ ስህተት ነው።ለ. በአጼ ምኒሊክም ሆነ በአጼ ኃይለስላሴ ዘመን “አማራ” የሚባል የፖለቲካ ማህበረሰብ፣ “አማራ” የሚባል ጠቅላይ ግዛት፣ “አማራ” የሚባል የፖለቲካ ድርጅት ወይም የትግል እንቅስቃሴ ኖሮ አያውቅም። እንዲህ ዓይነት መዋቅራዊ መገለጫዎች በአገሪቱ ባልነበሩበት ዘመን የነበረን ስርዓት “የአማራ” ስርዓት አድርጎ መፈረጅ መሰረተ-ቢስ ነው።ሐ.አጼ ምኒሊክንም ሆነ አጼ ኃይለስላሴን ውጫዊ ኃይሎች በተለያየ ማንነት ይጠሯቸው የነበረ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ራሳቸውን ግን እንደ “ሸዋ” ተወላጅ፣ የሰሎሞን ስርወ-መንግሥት ወራሽና ክርስቲያን አድርገው ከማየት ባለፈ ከብሔር ወይም ከዘር አኳያ ራሳቸውን “አማራ ነን” ብለው ያዩ እንደነበር የሚያሳይ የታሪክ መረጃም ሆነ ማስረጃ የለም። ዛሬ ላይ በተፈጠረ አዲስ ብሔር-ተኮር አስተሳሰብ ላይ ተመስርቶ የቀድሞ ነገስታትን የብሔር ማንነት (የሚናሩትን ቋንቋ በማየት ብቻ) ለመበየን መሞከር ስህተት ነው።መ. አጼ ምኒሊክም ሆኑ አጼ ኃይለስላሴ ይመሩት የነበረው ስርዓት በዋናነት ማዕከል አድርጎ የተቋቋመው የሸዋ መኳንንቶችን ነበር። እነዚህ መኳንንቶችም በዋናነት አማርኛ፣ ኦሮምኛና ጉራግኛ ተናጋሪ ከነበረውና ከሸዋ በቅርብ ርቀት ከሚገኙ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ነበሩ። አጼ ሚኒሊክም በዘመናቸው ያካሄዱት ግዛትን እንደገና የማስፋፋት ዘመቻ የተመራውም በዋናነት በእነዚህ ኃይሎች ጥምረት ነበር።የአጼዎቹ ስርዓቶች መላውን የአገሪቱን ህዝብ በጭቆና ማስተዳደር የቻሉት ከማዕከል በሚልኳቸው “ነፍጠኞች” ብቻ ሳይሆን በየግዛቱ በነበሩ የአካባቢው ባላባቶች ትብብር ጭምር ነበር። እንኳንስ ከማዕከሉ በርቀት የሚገኙት ህዝቦችና ከአዲስ አበባ በቅርብ እርቀት የሚገኘው የሸዋ ህዝብም የባላባቶቹ የጭቆና ሰለባ በመሆን እስካሁን ድረስ በነተበ ድህነት ለመኖር የተገደደ ነው። በተለይም ፌደራላዊ ይዘት ከነበረው የአጼ ምኒሊክ አስተዳደር በተለየ የተማከለ (አሀዳዊ) የአስተዳደር ስልት ያራምድ በነበረው የአጼ ኃይለስላሴ መንግሥት ዛሬ በአማራነት የሚታወቁት ሸዋ፣ወሎ፣ ጎጃምና ጎንደር ጭምር ይተዳደሩ የነበረው ከአዲስ አበባ ተሹመው በሚላኩላቸው ገዢዎች ነበር። እንዲህ ዓይነቱን ስርዓት በአንድ ብሔር ስርዓትነት ወይም በአንድ ብሔር ስም በሚጠራ ገዢ መደብ ለመፈረጅ መሞከር ከብሔርተኝነት ፕሮፓጋንዳ ያለፈ ፋይዳና ትርጉም የለውም።እውነታው ይህ ባይሆን ኖሮ ኋላ ላይ የንጉሱን ስርዓት ለመጣል በተካሄደው ትግል ብሔርን መሰረት ያደረገ ቅራኔ ጎልቶ በታየና አማርኛ ተናጋሪውም ህዝብ ንጉሳዊ ስርዓቱን በግንባር ቀደምትነት ለመጣል የሚታገል ሳይሆን ከጥቃት ለማዳን የሚከላከል በሆነ ነበር።ከ1953 ዓ.ምቱ የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ በፊት እንኳንስ ከብሔር ጭቆና ከአገዛዝ ጭቆና ነፃ የመውጣት ትርጉም ያለው ህዝባዊ ትግል በአገሪቱ ተካሂዶ ነበር ማለት አይቻልም። በዚህም ምክንያት ነው በቀዳማይ ወያኔ፣ በባሌና በጎጃም ገበሬዎች የተካሄዱ አካባቢያዊ አመጾች በታሪክ መፃህፍቶቻችን ላይ እንደ ከፍተኛ አገራዊ የህዝብ ትግል ተደርገው የጎላና የተጋነነ ቦታ ይዘው የምናገኛቸው።በብሔር መስመር ተቧድኖና ድርጅት ፈጥሮ ፖለቲካዊ ትግል ማካሄድ የተጀመረው የንጉሱ ስርዓት ያለቀለት መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ነበር። ከዚያ በፊት በነበረው የለውጥ ትግል ህዝባዊ መንግሥት እንዲቋቋምም ሆነ “መሬት ለአራሹ” እንዲታወጅ ጥያቄ ይቀርብ የነበረው ከአንድ አካባቢ ሳይሆን ከሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በመጡ ተማሪዎች ነበር። ዛሬ የአማራ ክልል ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ የወጡ ተማሪዎች በዚህ የትግል ሂደት የነበራቸው ተሳትፎ በግንባር ቀደምትነት ሊጠቀስ የሚችል እንጂ ከሌሎች ያነሰ አልነበረም። ሌላው ቀርቶ የብሔር ጥያቄን በአደባባይ ይዞ በመቅረብ በአገራችን ብሔርተኞች ዘንድ እንደ ፋና ወጊ የሚወሳው ዋለልኝ መኮንንም ከአማርኛ ተናጋሪው ህዝብ የተገኘ ነበር።በሂደት ሁኔታዎች መልካቸውን እየለወጡ ቢመጡም መጀመሪያ ላይ ራስን በብሔር ማንነት አደራጅቶ የመታገል ምርጫ ታክቲካዊ እንጂ ስትራቴጂካዊ ዓላማ አልነበረም። በወቅቱ “የወዝ አደር መደብ ገና ባልተፈጠረበት አገር ህዘቡን በትግሉ ዙሪያ ለማሰባሰብ የብሔር አደረጃጀት የተሻለ ስልት ነው” የሚለው የእነ ስታሊን ታክቲካዊ ምርጫ ነበር በሂደት ህወሃትና ኦነግን በመሳሰሉ ብሔርተኛ ድርጅቶች ወደ ስትራቴጂካዊ ዓላማነት የተቀየረው። በዚህም ምክንያት ነው – ንጉሳዊ ስርዓቱን በጋራ ሲታገሉ የነበሩ ወጣቶች ከደርግ መምጣት በኋላ በሁለት የአደረጃጀት አቅጣጫ ለመከፋፈል የተገደዱት። በዚያ ጊዜ የተፈጠረው መለያየትም ዛሬም ድረስ ዋናው የአገሪቱ የፖለቲካ ቅራኔ መገለጫ ሆኖ ቀጥሏል።በአጠቃላይ፣ በማንኛውም አገር ፖለቲካ ሲሆን እንደታየው ለስልጣን በበቃ አንድ የፖለቲካ ኃይል ውስጥ የአንድ አካባቢ ተወላጆች በአንጻራዊነት ከሌላው በቁጥር ወይም በስልጣን ደረጃ በልጠው ወይም አንሰው ሊገኙ ይችላሉ። እንዲህ ዓይነቱን አንድና ቁንጽል ማሳያ ይዞ የአንድን አገር ስርዓት የአንድ ብሔር ስርዓት አድርጎ ለመፈረጅ መሞከር ግን ስህተት ነው። የሚያሳዝነው በጨቋኝነት ይፈረጅ የነበረው ንጉሳዊ ስርዓት ከስልጣን ከተወገደ ከ50 ዓመት በኋላና ብሔርተኛ ኃይሎች አሸንፈው ቤተ-መንግሥት ከገቡ ከ32 ዓመት በኋላ ዛሬም ድረስ አማራውን ህዝብ ጨቋኝ ገዢ መደብ አድርጎ የመቀስቀሱ ትርክት ተጠናክሮ ቀጥሏል። ይህ እየሆነ ያለውም በሌላ አሳማኝ ምክንያት ሳይሆን በአገሪቱ የበለጠ ገንግኖና መዋቅራዊ ሆኖ የቀጠለው የብሔርተኝነት ፖለቲካ አንድን ብሔር በጠላትነት ካልፈረጀ በስተቀር ህልውና ኖሮት መቀጠል ስለማይችል ነው።2. የደርግ መንግሥት የማን መንግስት ነበር…?በአጼ ኃይለስላሴ ዘመን በስራ ላይ ከነበሩት የመንግሥት ተቋማት ውስጥ በአንፃራዊነት የተሻለ የህዝብ ተዋፅዖና ማህበራዊ ተቀባይነት የነበረው የአገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ነበር። የሰራዊቱ አብዛኛዎቹ የበላይ አመራሮች ኦሮምኛ ተናጋሪ ከሆነው ህዝብ የወጡ ቢሆንም ሰራዊቱ በወቅቱ ከነበረው የህዝብ ተዋፅዖም ሆነ ከስነ-ልቦና አኳያ የማንኛውም ብሔር ሳይሆን የኢትዮጵያ ሰራዊት ተደርጎ የሚታይ ነበር። በ1966 ዓ.ም በመጣው ለውጥ በድንገት ለስልጣን የበቃው ይህ የአገሪቱ ወታደራዊ ኃይል ስለሆነ የደርግን መንግስት የአንድ ብሔር ስርዓት አድርጎ ለማየት የሚያስችል ምንም ዓይነት አሳማኝ ምክንያት ከጅምሩም አልነበረም።ደርግ ራሱን እንደ ጭቁን ህዝቦች አካልና ወኪል አድርጎ ያይ ስለነበር ከላይ እስከ ታች በዙሪያው ያሰባሰበው የአንድ ወይም የውስን ብሔሮችን ህዝብ ሳይሆን ለውጥ ፈላጊ ነኝ ብሎ የሚያምነውን ማንኛውንም ዜጋ ነበር። በአንፃሩ ስልጣኑን ለማጠናከር በማሰብ በጠላትነት ፈርጆ ያጠቃውም አንድን ወይም የተወሰኑ ብሔሮችን ሳይሆን አድሃሪ፣ ፊውዳልና ፀረ-ህዝብ መስሎ የታየውን ዜጋ ሁሉ ነበር።ደርግ ስልሳዎቹን የአጼ ኃይለስላሴ መንግስት ሚኒስትሮችን እና ባለስልጣናትን በአንድ ምሽት ያለ ፍርድ ሲገድል፣ በቀይ ሽብር ዘመቻ በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን ሲጨፈጭፍ፣ በመሬት ለአራሹና በትርፍ ቤቶች አዋጅ የዜጎችን ንብረት ሲወርስ መመዘኛው የብሔር ማንነት ሆኖ አያውቅም። ይህ የሆነው በዋናነት በደርግ ምርጫ ሳይሆን ከደርግ በፊት የነበረው አገራዊ ሁኔታ የፖለቲካ ድጋፍን ለማሰባሰብም ሆነ ጥቃትን ለመፈጸም ብሔርን በመስፈርትነት መጠቀም የሚያስችል ስላልነበር ነው።የኤርትራ፣ የትግራይና የኦሮሞ የፖለቲካ ኃይሎች ተጠናክረው በመውጣት ጦርነት እያካሄዱ በነበረበት ወቅትም ደርግ ተፋላሚዎቹን ይገድል የነበረው የፖለቲካ አመለካከታቸውን እንጂ የብሔር ማንነታቸውን መሰረት አድርጎ አልነበረም። ለዚህም ነው ደርግ ከስልጣን እሰከተወገደበት ጊዜ ድረስ በአገሪቱ የአስተዳደር መዋቅሮች ብቻ ሳይሆን የበለጠ ታማኝነት በሚጠይቀው የደህንነትና የመከላከያ መዋቅር ጭምር የኤርትራ፣ የትግራይና የኦሮሞ ተወላጆች የጎላ ተሳትፎ ይዘው የኖሩት። መስፈርቱ የብሔር ማንነት ሆኖ ባያውቅም በአስራ ሰባት ዓመቱ የደርግ ዘመን አማርኛ ተናጋሪው ህዝብ ምን አልባት የበለጠ ተጠቂ እንጂ ተጠቃሚ አልነበረም። በደርግ ስርዓት ንብረቱን ተወርሶ ለከፋ ድህነት የተጋለጠው፣ በአድሃሪነትና በፀረ-ህዝብነት እየተፈረጀ በየአደባባዩ የተረሸነው አማርኛ ተናጋሪ ህዝብ ቁጥር ቀላል አልነበረም።እውነታው ይህ ሆኖ እያለ ብሔርተኛ ኃይሎች 1983 ዓ.ም ላይ ደርግን ጥለው ለስልጣን ሲበቁ እነሱ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው ከ17 ዓመት በፊት ግብዓተ-መሬቱ የተፈጸመውን የንጉሳዊ ስርዓት ህልውና እንዳለው በመቁጠር “የትምክህተኛና የነፍጠኛ ስርዓት” የሚለውን ጊዜ ያለፈበት ትርክታቸውን ዋና የመታገያ አጀንዳቸው አድርገው መቀጠልን መረጡ። በአማርኛ ተናጋሪው ህዝብ አጋርነት ደርግን ለመጣል እንደበቁ ረስተውትም “የአማራ ገዥ መደብንና የኦርቶዶክስን የበላይነት አከርካሪውን ሰበርነው” የሚል ፉከራ ማስተጋባት ጀመሩ።በአጭሩ ኢህአዴግ ከ17 ዓመት የትጥቅ ትግል በኋላ ለስልጣን ሲበቃ ከኢትዮጵያ ህዝብ አመለካከትና ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ 17 ዓመት ወደኋላ የቀረ ነበር። የብሔር ጥያቄን የሚያቀነቅኑ የብሔር ድርጅቶች መኖራቸው እንደተጠበቀ ሆኖ በደርግ ጊዜ የነበረው የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ትውልድ ቀዳሚ ጥያቄዎች ግን የዴሞክራሲ፣ የሃሳብ ነፃነት፣ የሰብዓዊ መብት መከበርና ከድህነት አዙሪት የመውጣት ነበር። እውነታው ይህ ሆኖ እያለ የኢህአዴግ ትርክት በዋናነት ያተኮረው ግን የብሔር ጥያቄን በመመለስ አጀንዳ ላይ ነበር።በአጠቃላይ፣ የስርዓቱ ቁንጮ የነበሩት ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማሪያምና ጓዶቻቸው ብሔራቸው ከየትም ይሁን ከየት የ17 ዓመቱን የደርግ ስርዓት በአማራ ገዥ መደብነት ለመፈረጅ ይቅርና ለመጠርጠር የሚያስችል ምንም ዓይነት አሳማኝ ምክንያት የለም።3. የኢህአዴግ ስርዓት የማን ስርዓት ነበር (ነው)…?በብሔር አድልዎ ጉዳይ ከማንም በላይ ሌሎችን በመክሰስ የሚታወቀው ኢህአዴግ ቢሆንም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ራሱን በብሔር ስም አደራጅቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ለስልጣን የበቃው ኃይል ግን ኢህአዴግ ነው። ኢህአዴግ ለስልጣን ሲበቃ ቀዳሚ አጀንዳው ያደረገው የደርግ ስርዓት አልመለሰውም ብሎ የሚያምነውን የብሔር ጥያቄ ለመመለስ ነው። ደርግ ብሔር-ብሔረሰቦችን አበላልጦ የማያይ መንግሥት ቢሆንም አሃዳዊና የኢትዮጵያ ብሔርተኝነትን የሚያቀነቅን ስርዓት ስለነበር ኢህአዴግ ከብሔር-ብሔረሰቦች መብት አኳያ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ ብሎ ማመኑና መልስ እንዲያገኙ ለመስራት መሞከሩ ችግር የለውም።ችግሩ ያለው፡-አንደኛ – የደርግ መንግሥትንም እንደ ንጉሳዊው ስርዓት የአማራ ገዢ መደብ ስርዓት አድርጎ የሚከስ ትርክት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማድረጉ፤ሁለተኛ – በደርግ ዘመን የነበረው አብዛኛው ትውልድና ህዝብ ቀዳሚና ብቸኛ አጀንዳ የብሔር ጥያቄ የነበረ ይመስል የብሔርተኝነት ፖለቲካን በሁለንተናዊ መልኩ መዋቅራዊ እንዲሆን ማድረጉ ነው።ኢህአዴግ ወደ ስልጣን በመጣበት ወቅት ለብሔር ጥያቄ ቀዳሚ ትኩረት የሚሰጡ የፖለቲካ ኃይሎች የነበሩ ቢሆንም የአብዛኛው ህዝብ ቀዳሚ ጥያቄ ግን በሁለንተናዊ መልኩ መልካም አስተዳደር የማግኘትና ከድህነት ኑሮ የመላቀቅ ነበር። ኢህአዴግ ግን የመረጠው “የራሴ” የሚለውን አጀንዳ በህዝብ ላይ ለመጫን ነው እንጂ ሚዛናዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ አግባብ የህዝቡን እውነተኛ ጥያቄዎች ለይቶ ለማወቅና አግባብ ባለው ቅደም ተከተል ለመመለስ አይደለም።በተለይም ኢህአዴግ በገዢ መደብ ስም ለአገሪቱ ሁለንተናዊ ችግሮች የአማራውን ህዝብ ተጠያቂ የማድረግ ያልተገባ ትርክት ይዞ መቀጠሉ የአማራው ህዝብ የኢህአዴግን ስርዓት ከጅምሩ በጥርጣሬና በጥላቻ አይን እንዲያየው አድርጓል። ከዚያም በላይ በሚካሄደው ፀረ-አማራ ትርክት ምክንያት የአማራውን ህዝብ የበርካታና ከፍተኛ ጥቃቶች ሰለባ እንዲሆን አድርጎታል። ይህ ችግር የበለጠ እየተባባሰ በመምጣትም ለወቅቱ የአማራ ክልል ጦርነት ዋና ምክንያት ሆኗል።ኢህአዴግ መጀመሪያ ላይ ለስልጣን ሲበቃ የአራት ድርጅቶች ጥምረት የነበረ ሲሆን፣ በሽግግሩ ወቅት የተለያዩ ተጨማሪ ብሔር ተኮርና ህብረ-ብሔራዊ ድርጅቶችን በማካተት አገሪቱን ለ3 አመታት አስተዳድሯል። ቋሚ መንግሥት ካቋቋመም በኋላ ከአራት አባል ድርጅቶቹ በተጨማሪ 5 አጋር ድርጅቶችን በዙሪያው አሰባስቦ አገሪቱን ለ24 ዓመት ገዝቷል። ከሽግግሩ ወቅት በተለየም የቀድሞው “ኢህዴን” ራሱን ወደ “ብአዴን”ነት ቀይሮ በአማራ ህዝብ ተወካይነት ስም አገሪቱን ከሌሎች ጋር በጋራ፣ አማራ ክልልን ደግሞ በተናጠል ለ24 ዓመት አስተዳድሯል።በአጠቃላይ ኢህአዴግ ለ27 ዓመታት በነበረው የስልጣን ቆይታ አገሪቱን የገዛው በአንድ ፓርቲ ወይም የብሔር አባላት ብቻ ሳይሆን ከመላው አገሪቱ የተሰባሰቡ ድርጅቶችንና ከ10 ሚሊዮን በላይ የሆኑ አባላቶቹን በዙሪያው አሰባስቦ ነው። በስልጣን ላይ የነበሩት ፓርቲዎች በአገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ራሳቸውን በብሔር ማንነት አደራጅተው ለስልጣን የበቁ ቢሆንም አገሪቱን በማዕከል ደረጃ የገዙት ግን በጋራ ተጣምረው ሲሆን የመጡበትን ክልል ደግሞ በተናጠል ገዝተዋል። በመካከላቸው ሚዛን ያልጠበቀ የአቅምና የተፅዕኖ ፈጣሪነት ሚና የነበረ ቢሆንም ከአለፉት ስርዓቶች ጋር ሲነፃፀር ከማዕከሉ ፖለቲካ ርቀው የኖሩ የዳር አገር ህዝቦችን እንወክላለን የሚሉ ፓርቲዎች አካባቢያቸውን በራሳቸው የማስተዳደርና በማዕከላዊ መንግሥቱ አንፃራዊ ውክልና የማግኘት ዕድል አግኝተዋል።ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ከኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች መካከል ህወሃት የበለጠ አቅምና የተፅዕኖ ፈጣሪነት ሚና የነበረው ድርጅት መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ይህ በኢህአዴግ ውስጥ የነበረው “የተዛባ የኃይል ሚዛን ገፅታ” ግን በስልጣን ላይ የነበረውን የኢህአዴግና የአጋር ድርጅቶቹን አገዛዝ “የህወሃት” ወይም “የትግሬዎች” አገዛዝ ብቻ አድርገን ለመፈረጅ በፍጹም አያስችለንም።ህወሃት በመንግስት መዋቅር ውስጥ በፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በሚኒስትሮች ምክር ቤት የነበረው ውክልና በአማካይ ከ5% (አምስት በመቶ) ያልበለጠ ሲሆን፣ በኢህአዴግ ምክር ቤትና ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ የነበረው ድርሻ ደግሞ 25% (ሃያ አምስት በመቶ) ነው። ነገር ግን ህወሃት ቁልፍ የሚባሉ ኃላፊቶችን በመከላከያ፣ በደህንነት፣ በፌዴራል ፖሊስና ውጭ ጉዳይን በመሳሰሉ መስሪያ ቤቶች ይዞ ስለነበር አጀንዳ ከመቅረፅና ውሳኔን ከመስጠት አኳያ ቀላል የማይባል ተፅዕኖ ነበረው። ይህ የስርዓቱ አንድ የኢ-ፍትሃዊነት መገለጫ የሆነ ዋና ደካማ ጎን የነበረ ቢሆንም ከፍ ሲል ለመግለፅ እንደተሞከረው ስርዓቱን እንኳንስ የአንድ ብሔር የአንድ የብሔር ድርጅት ስርዓት አድርጎ ለመፈረጅና ትርክት ለማቅረብ ግን አያስችልም።የ27 ዓመቱን የኢህአዴግ መንግሥት ሲበዛ የትግራይ ህዝብ፣ ሲያንስ ደግሞ የህወሃት (ወያኔ) ስርዓት አድርጎ ትርክት ማቅረብ በአገራችን የፖለቲካ የሃሣብ ልውውጥ እውነት በሚመስል መጠን የተለመደ ሆኗል። ነገር ግን ለዚህ ዓይነቱ ፍረጃ የሚቀርበው ክርክር ቢያንስ በሚከተሉት ሁለት ምክንያቶች ውሃ የማይቋጥር ነው።አንደኛ – ኢህአዴግ በነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ስላልተመረጠ እውነተኛ የኢትዮጵያ ህዝብ መንግሥት አልነበረም ብለን ብዙዎቻችን እንደምናምነው ሁሉ ህወሃትም በትግራይ ህዘብ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ተመርጦ አያውቅምና በህወሃት ምክንያት የ27 ዓመቱ መንግስት በየትኛውም መመዘኛ የትግራይ ህዝብ ስርዓት ተደርጎ ሊፈረጅ አይችልም።ሁለተኛ – ህወሃት በኢህአዴግ ውስጥ አንድ አራተኛ፣ በሌሎች የመንግሥት ምክርቤቶች የነበረው ድርሻ ደግሞ በአማካኝ ከአምስት በመቶ ያልበለጠ ስለነበር በፀጥታና በዲፕሎማሲ መስሪያ ቤቶች የነበረው የበላይነት ብቸኛ መመዘኛ ሆኖ ስርዓቱን የህወሃት ስርዓት ብሎ ለመፈረጅ በቂና አሳማኝ ምክንያት ሊሆን አይችልም።ለ27 ዓመት በስልጣን ላይ የነበረው የኢህአዴግ መንግስት ለሰራቸው በጎ ነገሮች መመስገን ያለባቸው፣ ለፈፀማቸው ጥፋቶችም መወቀስ ወይም መጠየቅ ያለባቸው ሁሉም የኢህአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶች ናቸው። ላለፉት 5 አመታት ሲባል እንደምንሰማው የኢህአዴግ አንድ አካልና አምሳል ሆነው በህዝብ ላይ ጭቆና ሲፈጽሙ የኖሩ ድርጅቶችና ባለስልጣናት “እኛ የህወሃት ተላላኪዎች ነበርን፣ ውሳኔ የመስጠት መብትም አልነበረንም” በማለት ስርዓቱን የህወሃት ስርዓት ብቻ አስመስለው ለመናገርና ራሳቸውን ከተጠያቂነት ነፃ ለማድረግ ሲሞክሩ አይተናል።እንዲህ ያለው ንግግርም ሆነ አመለካከት ከሃቅ ጋር በገልፅ የተጣላ ድፍረትና ክህደት ነው። በ27 ዓመቱ ስርዓት ለተሰራው ማንኛውም ጥፋት ሁሉም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶችና ባለስልጣናት በህግ ፊት እኩል ተጠያቂ መሆን የሚገባቸው ናቸው። እንዲያውም ከሞራልና ከታሪክ አኳያ በማያምኑበት ጉዳይ በአድርባይነት ታዛዥ ሆነው በህዝብ ላይ ጥፋት የሰሩት ተላላኪዎች የበለጠ ተጠያቂ ሊሆኑ ይገባል። ነገር ግን ‘ከኢህአዴግ አባላት መካከል የማን ወንጀል የበለጠ ወይም ያነሰ ነው?’ የሚለው ጥያቄ መልስ ማግኘት ያለበት ሃቀኛ በሆነ የሽግግር ፍትህ ሂደት ነው እንጂ በስሜትና በደቦ ፍርድ አይደለም።ለሁለት ዓመታት በትግራይ ህዝብ ላይ የተካሄደውን ጦርነት ብዙዎች መቃወም የተሳናቸው፣ አለመቃወምም ብቻ ሳይሆን ጦርነቱን በይፋና በአደባባይ ሲደግፉ የታዩት ያለምክንያት አይደለም። የ27 ዓመቱን ስርዓት ከህወሃትም በላይ የትግራይ ህዝብ ስርዓት እንደሆነ ተደርጎ በተሳሳተ መንገድ የቀረበው ትርክት በበርካታ ዜጎች ልብ ውስጥ ተቀባይነት ስለአገኘ ነው።እውነታው ይህ ባይሆን ኖሮ የትግራይ ህዝብ በራሱ አገር በከበባ ውስጥ ገብቶ እየተራበ እንዲኖር ሲደረግ፣ በራሱ አገር ሠራዊት ብቻ ሳይሆን በአረመኔው የሻዕቢያ ሠራዊት ዘግናኝ ጭፍጨፋና ዘረፋ ሲፈጸምበት አንድም ጦርነቱን የሚደግፍ ጤናማ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ባልኖረ ነበር። በነገራችን ላይ ብዙ ትኩረት ያልተሰጠው ቢሆንም አቶ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩበት ዘመን የሚመሩት ስርዓት እንደ ወላይታዎች ስርዓት ተቆጥሮ ብዙ ድሃ የወላይታ ተወላጆች በሃዋሳ፣ በሻሸመኔና በዝዋይ በግፍ ሲገደሉ ታይቷል። በ2010 ዓ.ምህረቱ አመፅ ወቅትም በቢሾፍቱ ከተማ ብቻ ከ1,500 የሚበልጡ በሊስትሮነትና በሱቅ-በደረቴ ንግድ ላይ የተሰማሩ የወላይታ ወጣቶች በጅምላ ታፍሰው ወደ ሶዶ ከተማ ተግዘዋል።እንዲህ ዓይነቱን ብሔርተኞች ለራሳቸው የፖለቲካ ጥቅም ሲሉ በህዝብ ላይ የሚያራምዱትን የተሳሳተ የትርክት አዙሪት ወደ ፊት አንድ ቦታ ላይ ማቆም ካልቻልን በስተቀር ከገባንበት ሁለንተናዊ ቀውስ ለመውጣት መቻልም ሆነ ህልውናችን የመዳን ዕድል እንደሌለው መጠራጠር አይቻልም።4. የብልጽግና አገዛዝ የማን ነው…?የወቅቱ የብልጽግና መንግሥት ከመሃሉ ህወሃትን ከመቀነሱና መጠሪያ ስሙን ከመቀየሩ በስተቀር በማንነትም ሆነ በይዘት ከቀድሞው የኢህአዴግ ስርዓት የተለየ አዲስ ፓርቲ አይደለም።አሁን ላይ በብልጽግና ስም በስልጣን ላይ የቀጠለው ኃይል የ27 ዓመቱ ስርዓት አንድ አካልና አምሳል ሆኖ ህዝብን ሲያፍንና ሲጨቁን የነበረው ኃይል ነው። የብልጽግና ኃይል በአደናጋሪ የፕሮፓጋንዳ ስልት ራሱን ከቀድሞው ስርዓት የተለየ አዲስ ስርዓት አድርጎ ለማቅረብና ህዝብን ለማታለል ሞክሮ ለተወሰነ ጊዜ የተሳካለት ቢሆንም ከምንም ነገር በላይ ተጨባጭ ተግባሩ የአለፈው ስርዓት ተቀፅላ ብቻ ሳይሆን የበለጠ የአጭበርባሪነትና የአፈና ክህሎት ያለው አገዛዝ መሆኑን እያሳየ ይገኛል። እርግጥ ነው የአደናጋሪ ትርክቱ ሰለባ በመሆን በመጀመሪያዎቹ ሁለት ወይም ሦስት ዓመታት ቀላል የማይባሉ የኦሮሞና የትግራይ ብሔርተኞች የዶ/ር ዐቢይን አገዛዝ አሃዳዊነትን ለማምጣት የሚሰራ “የአማራ ገዢ መደብ” አገዛዝ አድርገው ለማሳዬት ሲሞክሩ አይተናል። ይሁንና ከፕሪቶሪያው የሠላም ስምምነት በኋላ ይህ ትርክት እንደገና ተቀይሮ በአብዛኛው የኢትዮጵያ እና የአማራ ብሔርተኛ ኃይል የዶ/ር ዐቢይ አገዛዝ “የኦሮሞ ወይም የኦነግ” ተረኛ አገዛዝ ተደርጎ መታዬት ጀምሯል።የሚገርመው በአገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ከተለመደው ውጪ አንዳንድ የብልጽግና ከፍተኛ አመራሮች ጭምር የሚመሩትን ስርዓት “በኦሮሞ ህዝብ ትግል የመጣና ለኦሮሞ ህዝብ ጥቅም የሚሰራ የኦሮሞ መንግሥት” እንደሆነ አድርገው በድፍረት ለማቅረብ ሲሞክሩ ታይቷል። በኦሮሞ ህዝብ የተቃውሞ ትግል የጎላ ሚና ያላቸው አቶ ሌንጮ ለታ እና አቶ ጀዋር መሃመድን የመሳሰሉ ተዋቂ የፖለቲካ ሰዎች ሳይቀሩ የወቅቱን የብልጽግና አገዛዝ “የኦሮሞ ህዝብ መንግሥት” አድርገው ለማቅረብ ሲሞክሩ ታይቷል። በዚህም ምክንያት “የብልጽግና አገዛዝ የማንና ለማን ጥቅም የቆመ አገዛዝ ነው?” የሚለው ጥያቄ በአገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ መድረክ አከራካሪ ጥያቄ ሆኖ ብቅ ብሏል።መቼም ፖለቲካን በመጠኑ ለሚገነዘብ ሰው እያደናገሩ መግዛትን የአመራር ስልቱ ያደረገው የብልጽግና ፓርቲ የወቅቱን የራሱን ስርዓት “የኦሮሞ ህዝብ ስርዓት” አድርጎ ለማቅረብ መሞከሩ በውስጡ የፖለቲካ ሴራ እንዳለው ማሽተት የሚከብድ አይመስለኝም። ስርዓቱ ጊዜያዊ ጥቅሙን አስልቶ እንዲህ አይነት የማይገባ ስልት ለመከተል መምረጡ የማይጠበቅ ባይሆንም የስርዓቱ ተቃዋሚ የሆነው ኃይል ግን ካለፈው ስህተት ባለመማር እንዲህ ዓይነት የተሳሳተ ብቻ ሳይሆን የራሱንም የትግል ሂደት ጠልፎ የሚጥል ወጥመድ ውስጥ መግባቱ አሳዛኝ ስህተት ነው።በእኔ እይታ የብልጽግናው አገዛዝ ከኢትዮጵያና ከአማራው ብሔርተኛ ኃይል በአሳሳች ፕሮፓጋንዳ አግኝቶት የነበረውን ጊዚያዊ ድጋፍ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ሲያጣ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ያልተገባ ድጋፍ አግኝቶ ዕድሜውን ለማራዘም ለጀመረው የሴራ ትርክት ሰለባ ሆኖ መገኘት ትልቅ ስህተት ነው። እንዲህ አይነቱን የአገዛዙን የተሳሳተ ትርክት ተቀብሎ ማስተጋባት ምንም ዓይነት የሃቅ መሰረት የሌለው ከመሆኑም በላይ በወቅቱ የህዝብ ትግል ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል የተሳሳተ ስልት ነው።ምክንያቱም፡-1ኛ የኦሮሞን ህዝብ ከአለፉት አገዛዞች በባሰ ሁኔታ እያፈነ፣ እያሰረና እየገደለ የሚገኘውን የብልጽግና አገዛዝ “የኦሮሞ ህዝብ ስርዓት” አድርጎ መፈረጅ ኢ-ፍትሃዊ የሆነና ከተጨባጩ ሃቅ የሚቃረን አመለካከት ነው።2ኛ ህዝብ እና አገዛዝን የማይለይ የተሳሳተ ትርክት ማቅረብ የአማራና የትግራይን ህዝብ ከፍተኛ ዋጋ እንዳስከፈለው ሁሉ የወቅቱ ትርክትም ወደፊት የኦሮሞ ህዝብን ያልተገባ ዋጋ የማስከፈል ጣጣ ሊያስከትል ይችላል።3ኛ እንዲህ ዓይነቱ በህዝብ ላይ ያነጣጠረ ትርክት የህዝብ ለህዝብ የጎንዮሽ ቅራኔና ትግል እንዳይቆምና በውጤቱም አገዛዙ ያልተገባ የህዝብ ድጋፍ እንዲያገኝና እድሜው የበለጠ እንዲራዘም ሊያደርግ ይችላል።4ኛ የአገሪቱን የእርስ በርስ ጦርነት የበለጠ እንዲባባስና እንዲወሳሰብ፣ የአገሪቱ የመፍረስ አደጋም የበለጠ እንዲጠናከርና እንዲፋጠን ያደርጋል።የወቅቱ የዶ/ር ዐቢይና የጭፍራዎቻቸው አገዛዝ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያዊነትን አጀንዳ በማቀንቀን፣ በሌላ ወቅት የኦሮሞ ብሔርተኝነት ፖለቲካን የሚያራምድ በመምሰል፣ ሲያስፈልገው ደግሞ ሃይማኖትን እንደ ድጋፍ ማሰባሰቢያ ካርድ በመጠቀም በተለያየ መንገድ ራሱን እንደ እስስት እየቀያየረ ያልተገባ የህዝብ ድጋፍ ለማግኘት የሚጥር አገዛዝ ቢሆንም ከራሱ የስልጣን የበላይነት ባለፈ የየትኛውም ህዝብ ጥቅም አስከባሪ ስርዓት አይደለም።በኦህዴድና በተቃዋሚነት ጎራ ውስጥ ያሉ አንዳንድ የኦሮሞ ብሔርተኛ ኃይሎች ስርዓቱ የኦሮሞ ህዝብ ስርዓት መስሎ እንዲታይ የሚፈልጉበት የራሳቸው ያልተገባ የፖለቲካ ዓላማ እንዳላቸው የምረዳ ብሆንም ዶ/ር ዐቢይና የሚመሩት አገዛዝ ታማኝነቱ ለየትኛውም ዓይነት ርዕዮተ-ዓለም፣ ብሔር ወይም ሃይማኖት ሳይሆን ለራሱ የስልጣን የበላይነት ብቻ ነው። ለስልጣን የበላይነቱ መጠበቅ እስከጠቀመው ድረስ የዶ/ር ዐቢይ አገዛዝ በማንኛውም ጊዜና ሁኔታ የማይጨብጠውም ሆነ የማይጥለው አጀንዳ አይኖርም።ስለሆነም የወቅቱን አገዛዝ “የኦሮሞ ተረኛ አገዛዝ ነው” ብሎ መፈረጅም ሆነ የአገሪቱን መከላከያ ሠራዊት “የኦሮሞ ወይም የኦነግ ሠራዊት” ብሎ መጥራት በአስቸኳይ ሊቆም የሚገባው የተሳሳተና የማይጠቅም ትርክት ነው። መንግስትንም ሆነ መከላከያ ሠራዊቱን በውስጣቸው ባሉና ከበቂ በላይ በሆኑ ችግሮቻቸውና ድክመቶቻቸው መተቸትና ማውገዝ እየተቻለ በአንድ ብሔርም ሆነ ህዝብ ስም ፈርጆ መጥራት ጉዳት እንጅ ጥቅም የለውም።መደምደሚያብዙውን ጊዜ ብሔርተኞች ለምን አንድን ብሔር ወይም ህዝብ ያለ አግባብ በገዢነት እንደሚከሱ ጥያቄ ሲቀርብላቸው “እኛ ገዢ መደቦችን እንጂ ህዝብን አልከሰስንም” የሚል ማስተባበያ ለመስጠት ይሞክራሉ። ይህ ግን አሳማኝ መልስ አይደለም። ምክንያቱም እየቀረበ ያለው ክርክር “በኢትዮጵያ ታሪክ ህዝብ እንደ-ህዝብ ብቻ ሳይሆን የአንድ ብሔር ገዢ-መደብ የበላይ ሆኖ ሌላውን ህዝብ በበታችነት የገዛበት ስርዓታዊ ጭቆና አልነበረም” የሚል ስለሆነ በአንድ ብሔር ስም ሊጠራ የሚገባው ገዢ-መደብም በአገራችን ኖሮ እንደማያውቅ አምኖ መቀበል ያስፈልጋል።በዚህ መጣጥፌ ላይ ለማሳየት የሞከረኩት በሁሉም አገዛዞች ላይ እየቀረቡ ያሉ ትርክቶች ስህተት መሆናቸውን ነው። ይሁንና የአገራችን ብሔርተኞች ለየራሳቸው የሚጥማቸውን ከፊል እውነት እንጂ የተሟላውን እውነት ሊቀበሉት እንደማይፈቅዱ አስቀድሜ እገምታለሁ። በእኔ በኩል እንዲህ ዓይነቱ ድምዳሜ ላይ የደረስኩት ግን ያልተገባ እኩልነት (Unfair equivalence) በአገዛዞቹ መካከል ለመፍጠር ሳይሆን በሁሉም አገዛዞች ላይ እየቀረቡ ያሉት ትርክቶች ስህተቶች ናቸው የሚል ልባዊ ድምዳሜ ላይ ስለደረሰኩ ነው። እስካሁን በአገሪቱ በስልጣን ላይ የተፈራረቁት አገዛዞች በምርጫና በውክልና የአንዳችንም ያልሆኑ፣ በታሪክ ግን የሁላችንም የሆኑ አገዛዞች መሆናቸውን አምነን በመቀበል በዚህ ረገድ የሚታየውን የውዝግብ ምዕራፍ ብንዘጋው ተገቢ ይሆናል።በራሳችን የፖለቲካ ሂደት በተደጋጋሚ እንዳየነው አንድን የአገዛዝ ስርዓት ከአንድ ብሔር ወይም ህዝብ ጋር በማያያዝ የሚቀርብ ትርክት ሁሉ ምክንያታዊና ተገቢ አይደለም። ይሁንና እንዲህ ዓይነቶቹ ትርክቶች ትክክል ካለመሆናቸውም በላይ በህዝብ ላይ ያልተገባ በደል እንዲፈጸም ዋና አስቻይ ምክንያቶች መሆናቸውን እያየንም ከተደጋጋሚ ስህተታችን መታረም አልቻልንም። ይህም የሆነው ለአለፉት 50 ዓመታት በአገራችን የፖለቲካ ምህዳር ከጊዜ ወደ ጊዜ የበለጠ እየገነገነና እየተጠናከረ የመጣው የብሔርተኝነት ፖለቲካ ስለሆነ ነው።ብሔርተኝነት ደጋፊዎቹን እያስፈራራ የሚያሰባስብበት አንድ ግልጽ ጠላት ካልፈጠረ በስተቀር ህልውናው ሊቀጥልም ሆነ አንድን ትግል በአሸናፊነት ለመወጣት የሚያስችለው ሌላ ተጨባጭና ተመራጭ አጀንዳ ሊኖረው አይችልም። “እኛ እና እነርሱ” ከሚል የልዩነት ፍረጃ ውጪ ከሌላ ህዝብ ጋር የጋራ የሆኑ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፖሊሲ ነክ አጀንዳዎችን መያዝና ማራመድ ለብሔርተኞች የሚመረጥ አይደለም። ፖሊሲ-ነክ አጀንዳዎች ከአንድ ብሔር ውጭ ያሉ ሌሎች ህዝቦችም ስለሚጋሯቸው የአንድን ብሔር ህዝብ የብቻ የድጋፍ መሰረት አድርጎ ለመያዝ አያስችሉም። ስለሆነም ሁልጊዜም የብሔርተኞች ምርጫ የጋራ የሚባሉ አጀንዳዎችን እንደሌሉ መቁጠርና “የእኛ ብቻ” በሚሏቸው የልዩነት አጀንዳዎች ላይ ማተኮር ነው። ከሁሉም በላይ አንድን ሌላ ህዝብ ጨቋኝና ጠላት አድርጎ መፈረጅ የሰዎችን ስሜት በቀላሉ በማነሳሳት ጠንካራ ድጋፍ ለማግኘት የሚያስችል አቋራጭ ስልት ስለሆነ ሁልጊዜም የብሔርተኞች ቀዳሚ ምርጫ ነው።ብሔርተኞች የሚያራምዱት ማንኛውም አቋም የህዝብን ስሜት አነሳስቶ የሚፈልጉትን ድጋፍ ለጊዜው አስካስገኘላቸው ድርስ የያዙት አቋም የሩቅ ጊዜ ስትራቴጂካዊ ፋይዳው ምንም ይሁን ምን ደንታቸው አይደለም። እነሱ የደጋፊዎቻቸውን ስሜት ለማነሳሳት ብለው የሚያራምዱት የፅንፈኝነት አቋም በተመሳሳይ ሁኔታ በጠላትነት የተፈረጀውን አካል ስሜት የበለጠ በማነሳሳት ማባሪያና አሸናፊ ወደሌለው የጥላቻና የግጭት አዙሪት ውስጥ ሊያስገባ እንደሚችል አይገነዘቡም። ቢገነዘቡም ሁኔታዎችን ለማለዘብ የሚያስችል ሳይሆን “በይለይልን” ስሜት የተፈጠረውን ቅራኔ የበለጠ የሚያባብስ እና የጋራ ጥፋትንና ተሸናፊነትን የሚያስከትል ስልትን መከተል ይመርጣሉ።የአንድን አገር የሩቅም ሆነ የቅርብ ጊዜ ታሪክ በሚዛናዊነት ማየትና መቀበል ተገቢ ነው። ሲቻልም ባለፈ ታሪካችን ስለተሰሩ ጥፋቶች ፀፀትና ቁጭት ማሳየትና ተገቢ ትምህርት መቅሰም ጠቃሚ ይሆናል። ያለፈው የታሪካችን ሂደት በሁለንተናዊ መልኩ እኩልነትና ፍትህ የሰፈነበት ሳይሆን ከቋንቋ፣ ከባህል፣ ከሃይማኖት፣ ከፆታና ከተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮች አኳያ የተዛቡ ግንኙነቶች የነበሩበት መሆኑንም አምኖ መቀበል ያስፈልጋል። የባህል ተወራራሽነትንና መዋዋጥን በርግጠኝነት ማስቀረት ባይቻልም ሁሉም የየራሱን ማንነት አስጠብቆ የማስቀጠል መብት ያለው መሆኑን አምኖ መቀበል ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ የሁላችንንም ማንነት አጣምራ የያዘች የጋራ አገር እንጂ አንዳችንን ብቻ የምትመስል አገር ልትሆን አይገባም። በታሪክ ተፈፅሞ ያለፈውን ሁነት ዛሬ ላይ በክርክር መለወጥ የማንችል ቢሆንም የወደፊቱ ጉዟችን ግን በዚህ አግባብ መቃኘትና መካሄድ ይኖርበታል።የአንድ ህዝብ የአገረ-መንግሥት የግንባታ ሂደት በበጎ አቅጣጫ ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚችለው በጎ የታሪክ ገፅታዎችን ለትውልድ አጉልቶ በማቅረብና አዳዲስ መልካም አስተሳሳሪ ሁነቶችን ሆን ብሎ በመፍጠር ነው እንጂ በአሉታዊ የታሪክ ገፅታዎች ላይ መቋጫ የሌለው ንትርክና ግጭት በመፍጠር አይደለም። በልዩነት ላይ ያተኮረ የብሔርተኝነት ፖለቲካ እያካሄድን ወደ ዘላቂ አብሮነት፣ ሰላምና መረጋጋት በጭራሽ ልንሸጋገር አንችልም። ይህንን የጥፋት አዙሪት የሚቀለብስ ሌላ አዲስ አቅጣጫ በፍጥነት መከተል ካልጀመርን የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር እየተላለቅን ከመፈራረስ ከቶውንም አንድንም። የአገራችን ችግር በየፊናችን በምናካሂደው የታሪክ ትርክት፣ በየራሳችን አለን በምንለው አማራጭ ሃሳብም ሆነ በተናጠል እንደምንመኘው በአንዳችን አሸናፊነትና ድል ሊፈታ የሚችል አይደለም። ዛሬ ላይ ከፊታችን ያለው ቀዳሚና እጅግ አንገብጋቢ የሆነው የጋራ አጀንዳችን “አገርን እየተጨራረሱ ከመበታተን አደጋ መታደግ” መሆኑን ተገንዝበን ለጋራ ህልውናችን መቀጠል በጋራ ተባብረን መታገል አለብን።ዛሬ ላይ የሚስፈልገን፡- ‘አገሪቱ እንዴት ትመራ?’ በሚሉ የፖሊሲ ጉዳዮች መወዛገብ፣ ገዢዎችንና ህዝብን የማይለይ የሃሰት ትርክት እያቀረቡ ህዝብና ህዝብን ማራራቅ፣ ብሔር ተኮር የጎንዮሽ ግጭትና ጦርነት እያካሄድን የአገዛዙን እድሜ ማራዘምና የአገሪቱን የመፍረስ ሂደት የበለጠ ማፋጠንና አይቀሬ ማድረግ አይደለም።ይልቁንም ዛሬ ላይ የሚያስፈልገን፡- እንደ አንድ አገር ህዝብ መከባበርና መደማመጥ፣ እንዳችን ለሌላችን መጠቃት ተገቢ እውቅና መስጠትና በመካከላችን የተሻለ መተማመን መፍጠር፣ ሁላችንም የአገዛዙ ተጠቂዎችና በህልውና አደጋ ላይ የምንገኝ መሆኑን መገንዘብ፣ የማያግባቡንን አጀንዳዎች ወደፊት ለሚካሄድ የብሔራዊ መግባባት ሂደትና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማቆየትና እየተላለቁ ከመፈራረስ ለሚያድኑን ውስን የጋራ አጀንዳዎች ቀዳሚ ትኩረት መስጠት ነው።ከሁሉም በላይ አገሪቱ የምትገኝበት ከባድ ፈተና በስልጣን ላይ ባለው መንግስትም ሆነ በአንድ ተቃዋሚ ኃይል አሸናፊነት ዘላቂ መፍትሄ ሊያገኝ እንደማይችል መገንዘብና ሁሉን-አቀፍ አዲስ የሽግግር ሂደት እንዲፈጠር መታገል ይኖርብናል።ከዚህ በተቃራኒ አሁን ላይ ሁላችንም በየፊናችን እያካሄድነው ያለው የጽንፈኝነት፣ የብሔርተኝነትና የጦረኝነት አካሄድ ለብዙዎቻችን የመፍትሄ መዳረሻ መንገድ መስሎ ስለታየን በስሜትና በፍጥነት እየተጓዝንበት ነው። በእኔ እይታ ግን – እየተጓዝን ያለነው ለህልውናችን መድህን ወደ ሆነ መፍትሄ ሳይሆን እየተጨራረሱ መፈራረስን አይቀሬ ወደሚያደርግ አደጋ ነው። ——ልደቱ አያሌውጥቅምት 06 ቀን 2016 ዓ.ምLikeCommentShare