የ30 ዓመቱ ሄዋ ራሂምፑር

ከ 4 ሰአት በፊት

በእንግሊዝ ቻናል በኩል ሰዎችን በህገ-ወጥ መንገድ በማሻገር ከተሳተፉት የአዘዋዋሪ ቡድኖች አንዱን ሲመራ የነበረው ግለሰብ በቤልጂየም የ 11 ዓመት እስራት ተፈረደበት ።

ትናንሽ ጀልባዎችን በመጠቀም 10 ሺህ ሰዎችን ወደ ዩናይትድ ኪንግደም እንዲገቡ ካደረጉት መካከል ቀንደኛው የ30 ዓመቱ ሄዋ ራሂምፑር እንደነበር ፖሊስ ያምናል።

ራሂምፑር እአአ በ2016 ብሪታንያ ሲደርስ እና ጥገኝነት ሲጠይቅ 23 ዓመቱ ነበር። በወቅቱም ኢራናዊ ኩርድ በመሆኑ ወደ አገሩ ቢመለስ ችግር እንደሚያጋጥመው ተናግሯል።

በአውሮፓውያኑ 2020 እንዲቆይ ፈቃድ ተሰጠው።

በዩናይትድ ኪንግደም የመቆየት ፍቃድ የተሰጠው ራሂምፑር ከጓደኛዋ ጋር በለንደን ፀጉር ቤት ከፈተ። ቀጥሎም ብሪታንያን ለሚመራው ትልቅ የወንጀል ኦፕሬሽን ማዕከል አደረጋት።

ለስደተኞች መሻገሪያ የሚያገለግሉ ጀልባዎችን፣ ሞተሮችን እና የህይወት አድን ጃኬቶችን የሚያቀርቡ ቡድኖች አለቃ ሆነ። እቃዎቹን ከቱርክ እና ከቻይና በመግዛትም ወደ ጀርመን፣ ቤልጂየም እና ኔዘርላንድስ አጓጉዘዋል።

ጀልባዎቹ ወደ ሰሜናዊ ፈረንሳይ የባህር ዳርቻ አቅንተው በካሌ እና ዱንኪርክ ለሚገኙ ስደተኞች ተሰጡ።

ሴቶች እና ህጻናትን ያካተቱት ስደተኞች በጀልባዎቹን ተጠቅመው እንዴት ወደ ብሪታንያ መግባት እንደሚችሉ መሠረታዊ መረጃ እየተሰጣቸው ቻናሉን አቋርጠዋል።

አንዳንዶቹ ጀልባዎች ደህንነታቸው ያልጠበቁ፤ በፕላስተር እና በእንጨት ጭምር የተያያዙ እንደነበር ተነግሯል።

የስደተኞች ጉዳይ ባለሙያው ስቴፍ ያንሰንስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በእያንዳንዱ ጀልባው ከ30 እስከ 40 የሚደርሱ ሰዎች እንዲጫኑ ተደርጓል። “አሻጋሪዎቹ ለሰው ህይወት ምንም ክብር አያሳዩም። የሚገርመው ከዚህ በላይ ሞት አለመመመዝገቡ ነው” ብለዋል።

ከ12 እስከ 18 ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ለመሻገር ከሞከሩ ስደተኞች 10 በመቶ ለሚጠጉት የራሂምፑር ቡድን ተጠያቂ እንደሆነ ይታመናል።

“ትንንሽ ጀልባዎችን በመጠቀም ሰዎችን የሚያዘዋውር ቡድን መሪ የሆነ ሰው ተጠያቂ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው” ያሉት ያንሰን፤ የፍርዱ ዓለም አቀፍ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ለመዋጋት ወሳኝ እርምጃ እንደሆነ ገልጸዋል።

“ጉዳዩ በሰሜን ባህር ከሞቱት 31 ሰዎች ጋር በቀጥታ ሊገናኝ ይችላል” ሲሉም አክለዋል።

ቻናሉን የሚያቋርጡ ሰዎች ሊሞቱ መሆኑን በመግለጽ ራሂምፑር ለፖሊስ እንዲደውል የተነጋገሩበትን የዋትስአፕ መልዕክት ልውውጥ እንዳዩ ያንሰን ገልጸዋል።

 የ30 ዓመቱ ሄዋ ራሂምፑር

በሌላ መልዕክት ራሂምፑር የብሪታንያ ውሃ ክልል እስኪደርሱ እንዲጓዙና በዚያም መጓዝ የዩናይትድ ኪንግደም የባህር ጠረፍ ጥበቃ ቡድን ወደ እንግሊዝ እንደሚወስዳቸው ምላሽ ሰጥቷል።

“ከዚህ የመልዕክት ልውውጥ የምንረዳው ትንሽ ገንዘብ ላለማግኘት እነዚህ ሰዎች እስከመጨረሻው እየገፉ እንደሆነ መናገር ይቻላል” ብሏል።

በዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የወንጀል ኤጀንሲ እና በቤልጂየም ባለስልጣናት ጥምረት በተደረገ የጋራ ምርመራ፤ እአአ በ2021 በቤልጂየምና ፈረንሳይ ድንበር አቅራቢያ በመኪና ጀርባ ላይ በርካታ ጀልባዎችን አግኝተዋል።

በ2022ም ፖሊስ ራሂምፑርን ምሥራቅ ለንደን ተያዘ። 135 ጀልባዎችን፣ 45 ሞተሮችን እና 1200 የነፍስ አድን ጃኬቶችንም በቁጥጥር ስር አዋለ።

በቁጥጥር ስር የዋለውም በእንግሊዝ፣ በፈረንሳይ፣ በጀርመን፣ በቤልጂየም እና በኔዘርላንድስ ፖሊስ ባደረገው የተቀናጀ ምርመራ ነው።

በዓይነቱ ትልቅ በተባለለት የሕግ ማስከበር ዘመቻ በአራት አገሮች ውስጥ ከ40 የሚበልጡ ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

ራሂምፑር የ80,000 ዩሮ ቅጣትም ተላልፎበታል። ባለሥልጣናት የተወሰነበት የ11 ዓመት እስር ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎችን ከድርጊታቸው ሊገታ እንደማይችል ያምናሉ።

የሰዎች አዘዋዋሪ መረቦች በደንብ የተደራጁ እና ለመለየትም በጣም አስቸጋሪ እየሆኑ ነው።

ራሂምፑር ከታሰረ በኋላም በርካታ ሰዎች በትናንሽ ጀልባዎች ወደ እንግሊዝ መምጣታቸውን ቀጥለዋል። በዚህ የፈረንጆች ዓመት ከ24,200 በላይ ሰዎች ከፈረንሳይ በመነሳት የእንግሊዝን ቻናል አቋርጠዋል።

ቻናሉን ለማቋረጥ የሚፈልጉ በርካታ ሰዎችም አሉ።

ስደተኞች በሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎቹ ጀልባ ለመሳፈር ሲሉ ብዙ ገንዘብ ይከፍላሉ። ራሂምፑር የሚመራው ቡድን በ2021 ወደ 52 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ እንዳገኘ ይገመታል።

በጣም አደገኛ የሆኑት አደጋዎች እንኳን ሰዎች በትናንሽ ጀልባዎች ወደ አውሮፓ ለመግባት የሚያደርጉትን ሙከራ እንዲያቋርጡ አላደረጋቸውም። ባለፈው ሰኔ በደቡብ ግሪክ የባህር ዳርቻ ላይ አንድ ጀልባ በመስጠሟ የ500 ሰዎች ህይወት አልፏል።