October 19, 2023 – Konjit Sitotaw
ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ሰላምን፣ ደህንነትን፣ ንግድና ዉህደትን ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን የአገሪቷ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ሱማሊያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አሊ ኦማር፤ ሶማሊያ ሰላምን፣ ደህንነትን፣ ንግድና ዉህደትን ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኗን የገለጹ ሲሆን፤ ነገር ግን እንደ ወድብ የመሰለ ስትራቴጂያዊ ንብረት የመልቀቅ ፍላጎት የላትም ማለታቸውን ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
አክለውም “የሶማሊያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት እንዲሁም መሬት፣ ባህር እና አየር በሕገ መንግሥታችን እንደተደነገገው “ቅዱስ ነው” ለዉይይት ክፍት አይደለም” ሲሉ መናገራቸውን ዘገባው አመላክቷል።
በሌላ በኩል የጅቡቲው ፕሬዝዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አሌክሲስ መሀመድ፤ “የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አቋም አሁን በቀጥታ ወደፊት ይምጣ እንጂ፤ ቀድሞ የነበረ አቋም ነው” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አክለውም “ጅቡቲ ከጎረቤት አገሮች ጋር በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ግንኙነት ለመፍጠር ምን ጊዜም በሯ ክፍት ነው ያሉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ቀይ ባህርን ለመጠቀም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ጥያቄ እስክታቀርብ ጅቡቲ እንደምትጠብቅ አመላክተዋል።
በተጨማሪም ጅቡቲ ኢትዮጵያን የባህር በር አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ከፍተኛ አማካሪው ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ቀይ ባህርን አስመልክተው ባለፈው ሳምንት በሰጡት ማብራሪያ፤ “በታሪክ፣ በጂኦግራፊ፣ በዘር (በብሄር) እና በኦኮኖሚ ምክንያቶች የቀይ ባህር ጉዳይ ይመለከተናል።” ያሉ ሲሆን፤ “ቀይ ባህር ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ እንጂ ቅብጠት አይደለም።” ማለታቸው ይታወሳል፡፡
አክለውም፤ “አባይና ቀይ ባህር የኢትዮጵያን ልማትና ጥፋት የሚወስኑ የኢትዮጵያ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ናቸው።” ያሉ ሲሆን፤ ለጎረቤት አገራት ከሕዳሴ ግድብ፣ ከአየር መንገድ፣ ከኢትዮ ቴሌኮም ድርሻ በመስጠት፤ የባህር በር ድርሻ የመውሰድ አማራጮችን መጠቀም እንደሚቻል ገልጸው ነበር፡፡
የጠቅላ ሚኒስትሩን ማብራሪያ ተከትሎም፤ የኤርትራ መንግሥት የመረጃ ሚኒስትር ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ የኢትዮጵያን ሥም ባይጠቅስም “በቅርብ ጊዜ ስለ ውሃ እና ስለ ባህር በሮች እንዲሁም ተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳዮች የተነገረው እና የተባለው ቁጥር የለውም፡፡ በዚም ያልተገረመ ታዛቢ የለም” ሲል ገልጿል፡፡
በመግለጫው አክሎም “ኤርትራ እንደኹልጊዜው በእንደዚህ ዓይነቱ ጉዳዮች ላይ ለውይይት እንደማትታደም ያስታወቀ ሲሆን፤ “ይህ ነገር ይመለከተናል የሚሉ ኹሉም አካላት ጉዳዩን እንዳይነኩት” ሲል ማሳሰቡን አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የጅቡቲ፣ የሶማሌላንድ እና የኬንያ ወደቦችን ትጠቀማለች።
በምስራቃ አፍሪካ ካሉ አገራት ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያላት ኢትዮጵያ፤ አሁን ላይ አንድም ወደብ የሌላት አገር ስትሆን፤ በአገሪቱ ካለው ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ የወደብ ፍላጎቷ እያደገ መጥቷል።
