መንግሥት የቻይና አበዳሪ ተቋማት የብድር ክፍያ ሽግሸግ እንዲያደርጉለት ጠየቀ
(አዲስ ማለዳ) በቤልት ኤንድ ሮድ ፎረም ላይ እየተሳተፈ የሚገኘውና በገንዘብ ሚንስትሩ አህመድ ሽዴ የሚመራው ልዑካን ቡድን፤ የቻይናው ኤክሲም ባንክ ላለፋት ዓመታት የያዘውን የብድር ክፍያ ለፕሮጀክቶች በሚለቀቅበትና የብድር ክፍያ ሽግሸግ በሚደረግበት ጉዳይ ላይ ከባንኩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቷል፡፡
ልዑካን ቡድኑ ውይይቱን ያደረገው ከባንኩ ሊቀመንበር ከሚስተር ውፍሊን እና ከባንኩ ሀላፊ ዋኑ ጋር ሲሆን፤ ከባንኩ የከፍተኛ ሥራ ኃላፊዎች አበረታች ምላሽ ማግኘቱን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
በተመሳሳይ ልዑካን ቡድኑ ከቻይና ልማት ባንክ ሚስተር ዋንግ ዎልዶንግ፣ ከምክትሎቻቸው እና ከተለያዩ ዘርፍ ኃላፊዎች ጋር ተወያይቷል፡፡
በዚህም ቀደም ሲል የተጀመረው የብድር ክፍያ ማራዘሚያ ድርድር በቶሎ በሚቋጭበትና ባንኩ በቀጣዩ የኢትዮጵያን የልማት ፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች በሚደግፍበት ኹኔታ ላይ ውይይት ማድረጉ ተገልጿል፡፡
ከዚህም ሌላ ልዑካን ቡድኑ በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን ከፈሰሱና ወደፊት በኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት ስራዎች መሳተፍ ከሚፈልጉ ካምፓኒዎች የሥራ ኃላፊዎች ጋር የተናጥል ውይይት ያደረገ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከልም ከቻይና መንገድና ድልድይ ኮንስትራክሽን ድርጅት (CRBC)፣ CGCOC እና CGGC ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጉን አስታውቋል፡፡
በውይይቱም ካምፓኒዎቹ በቀጣይ በኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ ለመሳተፍ የሚፈልጉ መሆናቸውን በመግለፅ፤ ከመንግሥት እንደሁልግዜውም የሚደረግላቸው ድጋፍ እንዳይለያቸው መጠየቃቸውን አዲስ ማለዳ ከሚኒስቴሩ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል፡፡
በኢትዮጵያ ልማት ለሚሳተፋ የቻይና ድርጅቶች የሚደረገው የመንግስት ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገንዘብ ሚንስትሩ አህመድ ሽዴ በውይይቱ ለተሳተፋት አረጋግጠዋል፡፡
