October 21, 2023 

በሱዳን ጉዳይ የሚመክር የሲቪል ተቋማት ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ ይጀመራል ተባለ

(አዲስ ማለዳ) በሱዳን ያለውን ጦርነት ለማቆም የሚቻልበትን መፍትሔ ለመፈለግ ያለመ የሱዳን ሲቪል ተቋማት ለአራት ቀናት የሚቆይ ጉባኤ ዛሬ በአዲስ አበባ እንደሚጀመር ተገልጿል፡፡

በጉባኤው  ከ70 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የሱዳን ሲቪል ተቋማት፣ የአገር መሪዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች እና ተጽእኖ ፈጣሪዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ ራድዮታማዙጂ ባወጣው ዘገባ አመላክቷል።

የሱዳን ሲቪል ሀይሎች በአዲስ አበባ በሚያካሂዱት ጉባኤ ዋነኛ ትኩረት የሚሆነው፤ በአገሪቱ የተከሰተውን ግጭት እልባት ለማስገኘት የሚያስችል ስትራቴጂ መቀየስ መሆኑም ተገልጿል።

እንዲሁም በመጪው ሕዳር ወር ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው የሲቪል ተቋማት ጠቅላላ ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ የሚደረገውን ጉባኤ ለማሳለጥ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ተመላክቷል።

ስበሰባው የሚካሄደውም በኮሙዩኒኬሽን ባለስልጣን፣ በፖለቲከኞች፣ በተቃዋሚ አካላት እና በተለያዩ የሲቪል ማህበራት መካከል ሰፊ ምክክር ከተደረገ በኃላ መሆኑም ተገልጿል።

በሲቪል ሀይሎች በተደረገው ስብሰባ መሰረት የመጀመሪያ ደረጃ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን፤ ኮሚቴው በስብሰባው ላይ በቀረቡት ጉዳዮችና አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ለጠቅላላ ጉባኤ ቀርቦ በሚጸድቀው የፖለቲካ ረቂቅ ላይ መስማማቱ ተገልጿል።

የሲቪል ተቋሙ የፖለቲካ ሂደቱን የሚቆጣጠርበት የተለየ መዋቅር መዘርጋት እንዳለበት የተገለጸ ሲሆን፤ ጦርነቱን ለማስቆም መሰረታዊ የሆኑ የፖለቲካ ጉዳዮችን ለመፍታት እና የሽግግር ጊዜ ለመመስረት ያለመ መሆኑም በዘገባው ተመላክቷል።

በሌላ በኩል አራት የአሜሪካ የላይኛው ሕግ አውጭ ምክር ቤት አባላት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለሱዳኑ ጦርነት መፍትሄ ለማፈላለግ ልዩ መልዕክተኛ እንዲሾሙ መጠየቃቸው ተገልጿል።

ሕግ አውጭዎቹ ደብዳቤውን የጻፉት ጦርነቱ ቀጠናዊ ሊሆንና ወደ ዘር ማጥፋት ወንጀል ሊያመራ እንደሚችል እንዲሁም አገሪቱን ሊበታትናት እንደሚችል በመግለጽ ሲሆን፤ የልዩ ልዑኩ ተጠሪነት ለውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ እንዲሆንም ጠይቀዋል።