October 21, 2023 – Konjit Sitotaw
በደብረ ማርቆስ ከተማ በድሮን ጥቃት በርካታ ንፁሐን መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
በትናንትናው እለት በደብረ ማርቆስ ከተማ በመከላከያ ሰራዊት እና በአማራ ፋኖ መካከል ከባድ ጦርነት መካሄዱን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል። ውጊያውን ተከትሎም የብልፅግና መንግስት በደብረማርቆስ ከተማ ሶስት ቦታዎች ላይ የድሮን ጥቃት ፈፅሟል። በጥቃቱ በርካታ ንፁሀን የሞቱ ቢሆኑም፤ ትክክለኛ ቁጥሩን ግን የአካባቢው ነዋሪዎች ለጊዜው ማወቅ እንዳልቻሉ እማኞች ተናግረዋል። የድሮን ጥቃቱ ተቋማትን እና ንፁሐንን ኢላማ ያደረገ ነው ያሉት የዐይን እማኖች፤ የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ጤና ካምፓስ ላይ፣ ውትር ወንዝ እና ዮሀንስ አካባቢ የድሮን ጥቃት ተፈፅሟል ብለዋል።
አካባቢው ነዋሪዎች አክለውም በድሮን እና ከባድ መሳሪያ የሞቱ ንፁሐንን አስክሬን ለማንሳት የሞከሩ የአካባቢው ነዋሪዋች በመከላከያ ሰራዊት መገደላቸውን ተናግረዋል።
ከውጊያው በፊት ደብረማርቆስን ለቀናት ተቆጣጥሮ የቆየው የመከላከያ ሠራዊት፤ በአካባቢው በንፁሐን ላይ ግፍ ሲፈፅም መቆየቱን የገፈቱ ቀማሾች ተናግረዋል።
ለአብነትም በከባድ መሳሪያ የተገደሉትን የአብነት ተማሪዎች ጨምሮ የአብማ ማርያም ቤተ ክርስቲያን በከባድ መሳሪያ መጎዳቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
የብልፅግና መንግስት በወርሃ ጥቅምት 2016 ዓ.ም ብቻ በሶስት የተለያዩ አካባቢዎች የድሮን ጥቃቶችን ፈፅሞ በርካታ ሰላማዊ ዜጎችን መግድሉ ይታወቃል። በደብረማርቆስ ከተፈፀመው በተጨማሪ፤ በቅርቡ ኦሮሚያ ክልል ሻንቡ ዞን አቤ ደንጎሮ ወረዳ 23 ሰዎች እንዲሁም በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በረኸት ወረዳ 35 ሰዎች በድሮን ጥቃት ተገድለዋል።
በተጨማሪም በአማራ ክልል ፍኖተ ሰላም፣ ደብረብርሃን፣ ቋሪት፣ ደምበጫ፣ ደብረማርቆስ እና በረኸት ከባድ የድሮን ጥቃት የተፈፀመባቸው እና በርካታ ሰዎች የተገደሉባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡
በደብረ ማርቆስ ከተማ በተፈፀመው የድሮን ጥቃት የተገደሉ ንፁሐን ሰዎች አስመልክቶ የድምፅ መልዕክት የምናቀርብ መሆን ለመግለፅ እንወዳለን፡፡
