Getachew Shiferaw
· የዶ/ር አብይ ጉዳይ!
~ አብይ ለተቃውሞው ጎራም ሆነ ለኢትዮጵያ የሚያመጣው ትልቅ ገፀ በረከት የደከመ ኢህአዴግን ነው! ምን አልባትም ይህን ብቻ ይሆናል!
~ዶ/ር አብይ አህመድ ፓርላማ ላይ የተናገረው በትህነግ/ህወሓት ቱቦነት ነው ለማለት የሚከብድ ይመስላል። እንዲያው ስለ ዘረፋ፣ ኢዲሞክራሲያዊነት፣ እና ሌሎች ብልሹነቶች የተናገራቸው ትህነግ ላይ ያነጣጠሩ ይመስላሉ። ስለ ዳያስፖራው እና ስለ ኤርትራ የተናገረውን ጨምሮ የትህነግ/ህወሓት ፍላጎት ይኖርባቸዋል ቢባል እንኳ አገላለፃቸው አብይ በገለፀበት መንገድ እንዲሆን የሚፈልጉ አይመስለኝም። እንዲያውም አብይ “ሕዝበኛ” ተብሎ የተወቀሰበትን አቋሙን በግልፅ ለሕዝብ ያቀረበበት ይመስለኛል።
~የዛሬውን ንግግር ተቃዋሚ ከሚተነትነው በላይ ከአብይ በተቃራኒ የቆሙ የትህነግ/ኢህአዴግ ሰዎች ንግግሩን ቃል በቃል እየተነተኑ “ብለን ነበር!” እያሉ እንደሚቆዝሙበት፣ አብይን ወደዚህ ቦታ ደግፈው አድርሰዋል ያሏቸውን ስህተት ነበራችሁ የሚሉበት፣ አብይን ለመጥለፍ የሚያስፈልጉ መሰናክሎችን ሁሉ መፈለግ የሚቀጥሉበት ይመስለኛል።
~በሌላ በኩል በተቃውሞው ጎራ የአብይ ንግግር ጮቤ አስረግጧል። በንግግሩ ስለ አንድነትና ዴሞክራሲ በመነሳቱ እነ አብይ “የስልጣን ሽግግር” ያሉትን ያህል፣ ከዛም በላይ ለውጥ የመጣ ያህል ደስታ የተሰማው ተቃዋሚ ብዙ መሆኑን ማህበራዊ ሚዲያው ምስክር መሆን ይችላል።
~ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን በመምጣቱ በውስጠ ፓርቲ ትግል ትህነግ መገደዱን ቢያሳይም የተመረጠው ትህነግ በበላይነት የሚመራው ኢህአዴግ ወኪል መሆኑ የተረሳ ይመስላል። ያም ሆኖ የትህነግ/ኢህአዴግ ሰዎች “ሂስና ግለሂስ” የሚመስል ሀሳብ ባንፀባረቁበት ኢህአዴግ ሲደፍቅ የኖረው፣ እየተደፈቀ ያለው ተቃውሞ ጎራ (ማሕበራዊ ሚዲያውን እንደመለኪያ በመውሰድ)፣ ከኢህአዴግ ፓርላማ በተነገረው ተስፋ አድርጓል።
~ፓርላማው እንዳበቃ፣ እነ አብይም ሆኑ ኢህአዴግ ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎቹ የውስጣቸውን በውስጣቸው ይዘው ከንግግሩ ባሻገር ነገ አንዱ አንደኛውን ለማሸነፍ መስራት እንደሚጀምሩ መገመት ይቻላል። ተቃውሞ ጎራ ደግሞ ንግግሩን በቀጥታ በማድነቅ ላይ የተጠመደ ይመስላል።
~ዶ/ር አብይ አህመድ ከንግግሩ ሕዝብን ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚውን ጎራም ሳያተርፍ አልቀረም። ኢህአዴግም ያተረፈውና የከሰረው ይኖረዋል። ትህነግ የተወሰኑ ድንበሮቹ ተገፍተዋል። ትህነግ በአብይ ደስተኛ እንዳልሆነ ግልፅ ነው። ቀጣዩ ትግል የሚመስለው ኢህአዴግ ውስጥ ነው! ተቃዋሚው ከቻለ ሊጠቀም የሚችለው ይህን አጋጣሚ ነው! ኢህአዴግ ውስጥ የሚፈጠረውን ቀውስ ማባባስ!
~አብይ ያለው ከልቡ ነው ብለን ብንነሳ እንኳ የተናገረውን ለማድረግ አቅም ያለው አይመስልም። የመጀመርያው እንቅፋት የደሕንነት፣ የመከላከያ እና የካድሬ ሰንሰለቱ በትህነግ እጅ መሆኑ ነው። አብይ ኢህአዴግ ውስጥ መሆኑ መረሳት ያለበት አይመስለኝም።
~አብይ ለተቃውሞ ጎራውና ለኢትዮጵያ የሚያበረክተው አንድ ትልቅ ነገር ቢኖር የደከመ ኢህአዴግ ነው። በእነ አብይና በተቃዋሚዎቹ መካከል በሚደረገው የውስጠ ፓርቲ ትግል ኢህአዴግ ከመቼውም ጊዜ በላይ የደከመ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። የደህንነት መስርያ ቤቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ “አብይ አይችልም” ለማለት የማይፈነቅለው ድንጋይ አይኖርም። የካድሬ፣ የደህንትና የሰራዊቱ ዕዝ በሚኖር መገፋፋት፣ አብይ ስልጣኑን ተጠቅሞ፣ በንግግሩ የሰከረውን ሕዝብ ተገን አድርጎ የሚወስዳቸው ማስተካከያዎች ኢህአዴግ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ትንቅንቅ፣ የእርስ በእርስ መወነጃጀል የሚጠበቅ ነው። ከዚህ ሲከፋ በግትሮቹ የሚመራው ደሕንነት መስርያ ቤቱ እና ሰራዊቱ በአብይ ላይ የሚወስደው አፀፋ ኢህአዴግ ውስጥ የሚፈጥረው አለመረጋጋት የከፋ ሊያደርገው ይችላል።
~አብይ ለተቃዋሚው እና ለኢትዮጵያ የሚያመጣው በረከት ዴሞክራሲ ሳይሆን ከመቼውም ጊዜ የደከመ፣ መረጃው የተዝረከረከ፣ የትግል አቅጣጫውን ወደ ውስጠ ፓርቲ ትግል ያደረገ ኢህአዴግን ነው።ተቃውሞ ጎራው የአብይን ንግግርም ሆነ አብይን ሊጠቀም የሚገባው ኢህአዴግን ይበልጥ በማዳከም መሆን አለበት። አሁን እየተሰማ ያለው መወድስ ግን የኢህአዴጉን አብይ መመረጥ የስልጣን ሽግግር፣ አብይ አህመድ እንደግለሰብ የለውጥ መንገድ አድርጎ ነው፣ ይህ የተቃውሞው ጎራ በድስኩር የመስከር አባዜ ከትግሉ የሚያዘናጋ፣ የተገኘውን መልካም አጋጣሚ (ካርድ) ለመጠቀም የማያስችል ይመስለኛል!
~ ከምንም በላይ፣ ‘ኢህአዴግ ካልተወገደ ልውጥ አይመጣም’ ሲል የኖረ የተቃውሞ ጎራ የኢህአዴግ ተወካይ፣ በኢህአዴግ ፓርላማ በ30 ደቂቃ ባደረገው ንግግር ከቀደመው አቋሙ የሚሰንፍ ከሆነ የተቃውሞውን ጎራ ድክመት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ይመስለኛል!