የተመድ የእርዳታ አስተባባሪ

ከ 5 ሰአት በፊት

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ኤጀንሲዎች በጋዛ ሰርጥ ውስጥ ያለው ሁኔታ እየከፋ መምጣቱን ተከትሎ ሰብዓዊ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ ጥሪ አቀረቡ።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና የዓለም የጤና ድርጅትን ጨምሮ አምስት የተመድ ኤጀንሲዎች የጋዛን ሁኔታ “አሰቃቂ” ሲሉም በጋራ ባወጡት መግለጫ አስፍረዋል።

እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ አስገብቻታለሁ ባለቻት ጋዛ ሰርጥ የተጠናከረ ጥቃት እንደሚቀጥል እያስጠነቀቀች ባለችበት ወቅትም ነው የተባበሩት መንግሥታት ግጭቱ እንዲረግብ እየተማጸነ ያለው።

ግጭቱ ከተጀመረ ከሁለት ሳምንት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ 20 እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች በግብጽ የድንበር ማቋረጫ ራፋህ በኩል ወደ ጋዛ ገብተዋል።

ሆኖም በጋዛ ከሚያስፈልገው እርዳታ አንጻር “የውቅያኖስ ጠብታ” ሲሉም ተሟጋቾች እርዳታው አናሳ ነው ሲሉ ወቅሰዋል።

ከግጭቱ በፊት 500 የሚጠጉ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች በየቀኑ ወደ ጋዛ ይገቡ እንደነበር የአክሽን ኤይድ የፍልስጥኤም ቃለ አቀባይ አስረድተዋል።

በጋዛ ሰርጥ ከሚኖሩት መካከል ወደ 1.2 ሚሊዮን ነዋሪዎች በእርዳታዎች ላይ ጥገኛ እንደነበሩም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ያሳያል።

ከሁለት ሳምንታት በፊት ሐማስ በወሰደው ያልተጠበቀ ወታደራዊ እርምጃ 1ሺህ 400 ሰዎች በእስራኤል ተገድለዋል።

የሐማስ ታጣቂዎች በጋዛ ሰርጥ በኩል ድንበር ተሻግረው ነበር በንጹሐን እና በወታደሮች ላይ ጥቃት የፈጸሙት።

እስራኤል ላለፉት ሁለት ሳምንታት ቀን ተሌት ጋዛን በቦምብ በመደብደብ ላይ የምትገኝ ሲሆን በዚህም ከ4 ሺህ 300 ሰዎች በላይ ተገድለዋል።

እስራኤል በቅርቡ እግረኛ ጦሯን እንደምታስገባም እየተጠበቀ ይገኛል።

እስራኤል ጋዛ ሰርጥን ሙሉ በሙሉ በመዝጋት ከበባ እንዲደረግ ያዘዘች ሲሆን፣ በጋዛ ‘ኤሌክትሪክ፣ ምግብ፣ ነዳጅ አይኖርም ሲሉም የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት ባለፈው ሳምንት ትዕዛዝ መስጠታቸው ይታወሳል።

ጋዛ ሰርጥ ወደ 2.3 ሚሊዮን የሚጠጉ ፍልስጥኤማውያን መኖሪያ ስትሆን፣ ለ16 ዓመታት ያህል የቆየ ከበባ ውስጥ ትገኛለች።

ቅዳሜ እለት ወደ ጋዛ የገባው የእርዳታ አቅርቦት መድኃኒት፣ ምግብ፣ ውሃ እና የሬሳ ሳጥን ያካተተ ቢሆንም ነዳጅ አልነበረም።

የተመድ ኤጀንሲዎች ህጻናት፣ ነፍሰ ጡሮች እና አዛውንቶች ለከፋ ችግሮች እንደተጋለጡ ጠቅሰው ከጋዛ ሰርጥ ህዝብ ግማሽ የሚጠጉት ህጻናት መሆናቸውንም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ከተኩስ አቁም ስምምነቱ በተጨማሪም “በመላው ጋዛ አፋጣኝ እና ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነት” እንዲሁም የረድዔት ድርጅት ሰራተኞች ለተቸገሩ ፍልስጥኤማውያን እንዲረዱ መፈቀድ አለበት ብለዋል።

“በጋዛ ሰርጥ ከ1.6 ሚሊዮን በላይ ፍልስጥኤማውያን አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል” ብለዋል።