October 22, 2023 – EthiopianReporter.com

ዜና የተመድና ኢሰመኮ የጋራ ምክረ ሕሳብ የኢትዮጵያውያንን ውሳኔ የሚሹ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ጉዳዮችን…
ቀን: October 22, 2023
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤትና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በጋራ የሚሰጡት ምክረ ሐሳብ፣ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሊወስኑ በሚገባቸው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ጉዳዮች ላይ እንዳያተኩር ማሳሰቢያ ተሰጠ።
ማሳሰቢያውን የሰጠው በኢትዮጵያ የታቀደውን የሽግግር ፍትሕ ሒደት የማማከርና ፖሊሲውን የማርቀቅ ኃላፊነት ተሰጥቶት በፍትሕ ሚንስቴር አማካይነት የተቋቋመው ገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድን ነው።
የተመድና ኢሰመኮ የሽግግር ፍትሕ አማራጭ የፖሊሲ ግብዓቶችን ለማሰባሰብ የባለሙያዎች ቡድኑ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ሲያካሂድ የቆየውን ውይይት አጠናቆ፣ ወደ ፖሊሲ ማርቀቅ ምዕራፍ እየተሻገረ መሆኑን በማስመልከት የጋራ ዝርዝር ምክረ ሐሳቦችን መስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም. በይፋ አቅርቧል።
ተመድና ኢሰመኮ ባቀረቡት የጋራ ዝርዝር ምክረ ሐሳብ ላይ የተካተቱ የተወሰኑ መሠረታዊ ነጥቦች፣ የፖሊሲ ማርቀቅ ኃላፊነት በወሰደው የባለሙያዎች በድን ተቀባይነት አላገኘም። የባለሙያዎች ቡድኑም ይህንን መነሻ አድርጎ ለተመድና ኢሰመኮ ምላሽና ማሳሰቢያ የሰጠበትን መግለጫ ጥቅምት 7 ቀን 2016 ዓ.ም. አውጥቷል።
‹‹የፖሊሲ ማርቀቅ ሒደቱ በኢትዮጵያ ልዩ ሁኔታዎች ላይ በመመሥረት በኢትዮጵያ ሕዝብ ምርጫና ፍላጎት ብቻ መመራት አለበት፤›› ያለው የባለሙያዎች ቡድኑ መግለጫ፣ ‹‹ከዚህ አንፃር የተመድና የኢሰመኮ የኢትዮጵያ የሽግግር ፖሊሲ ማርቀቅ ሒደትን አስመልክቶ በቀጣይ በጋራ የሚያቀርቡት ማንኛውም ምክረ ሐሳብ የፖሊሲ ማዕቀፉ በምንና እንዴት መደራጀት እንዳለበት የሚወስኑ መሠረታዊ ዝርዝር ጉዳዮችን ከማንሳት መቆጠብ አለበት፤›› ሲል ማሳሰቢያ አዘል ምክረ ሐሳብ ሰጥቷል።
የባለሙያዎች ቡድኑ ይህንን ማሳሰቢያ ለመስጠት መነሻ የሆነው ተመድና ኢሰመኮ በጋራ ያወጡት ምክረ ሐሳብ ላይ በዳኝነትና በዳኝነት የማይታዩ ዕርምጃዎች ጥምረት (Combination of judicial and non-judicial measures) በሚል ንዑስ ርዕስ ሥር ያስቀመጡት ምክረ ሐሳብ ይዘት ነው።
ተመድና ኢሰመኮ ከላይ በተጠቀሰው ንዑስ ርዕስ ሥር ካስቀመጧቸው ምክረ ሐሳቦች አንዱ በባለሙያዎች ቡድኑ የሚረቀው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ በዳኝነት ሊታዩ የሚገባቸውንና ከዳኝነት ውጪ የሚታዩ ጉዳዮችን በግልጽ ለይቶ ማስቀመጥ እንዳለበት ይገልጻል።
ተመድና ኢሰመኮ በጋራ በሰጡት ምክረ ሐሳብ፣ ‹‹የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው አጠቃላይ ይዘት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የቀድሞ የመብት ጥሰቶች ውርስ በአገሪቱ የፈጠረው ውስብስብ ችግርን ለመፍታት ሲባል የሚረቀቀው ፓሊሲ ፆታዊ ጥቃትን ጨምሮ ሌሎች በአገሪቱ የተፈጸሙ ዓለም አቀፍ ወንጀሎች ላይ ክስ መመሥረትን ከግንዛቤ በማስገባት፣ በዳኝነትና ከዳኝነት ውጪ የሚታዩ ጉዳዮችን እንዲሁም ሒደትና ዘዴዎቹን በግልጽ ተርጉሞ ማስቀመጥ አስፈላጊ ነው፤›› ብለዋል።
በማከልም፣ ‹‹የሚረቀቀው ፖሊሲ ለዓለም አቀፍ ወንጀሎችና ለከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምሕረት መስጠትን ክልክል መሆኑን በግልጽ ማስቀመጥ አለበት፤›› ብሏል።
የፖሊሲ ማርቀቅ ኃላፈነቱን የወሰደው የባለሙያዎች ቡድን ማሳሳቢያ አዘል ምላሽ የሰጠውም ከላይ በተጠቀሱት የተመድና ኢሰመኮ የጋራ ምክረ ሐሳቦች ተገቢነት እንደሌላቸው በማመን ነው።
የባለሙያዎች ቡድኑ ከተመድና ኢሰመኮ ጋር ለሚሰጡት ድጋፍ ከፍተኛ አድናቆት ያለው መሆኑን፣ በቀጣይ የሚሰጧቸው ምክረ ሐሳቦችም ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የሚያሟላ የሽግግር ፖሊሲ ማርቀቅ ሒደትን ለማረጋገጥ ወሳኝነት መሆኑን ጠቁሟል። አጋርነቱ በዚህ ደረጃ የሚገለጽ ሆኖ ሳለ በኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያውያን ብቻ ሊወስኑ በሚገባቸው የሽግግር ፍትሕ ጉዳዮች ላይ መሠረታዊ ዝርዝር ጉዳዮችን ከማቅረብ መቆጠብ እንደሚገባቸው ማስገንዘብም አስፈላጊ መሆኑን የባለሙያዎች ቡድኑ አስረግጦ ተናግሯል።
‹‹ማንኛውም የሽግግር ፍትሕ ምርጫ በኅብረተሰቡ ሐሳብ እንዲሁም የፍትሕና የዕርቅ ፍላጎቶች ላይ ተመሥርቶ መወሰን አለበት፣ ይህም ማለት የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲው ትኩረት በዕርቅ፣ በፈውስና በፍትሕ ላይ ነው ወይም በራሱ ልዩ ዓውዶችና እውነታዎች ላይ የተመሠረቱ ዕርምጃዎች ጥምረት ነው፤›› ሲል የባለሙያዎች ቡድኑ መግለጫ አስረድቷል።
