
ማኅበራዊ ድርቅና ረሃብ የነጠቃቸው
ቀን: October 22, 2023
በኢትዮጵያ ባለፉት ጊዜያት በተከሰተው የዝናብ እጥረት እንዲሁም በሰሜኑ ክፍል በተፈጠረው ግጭት በርካታ ዜጎች በድርቅ እየሞቱ መሆኑ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ በተለይ በአማራ፣ በትግራይ፣ በአፋርና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ በተከሰተው ድርቅ ሰዎች እንደ ቅጠል እየረገፉ ሲሆን፣ አርሶ አደሮችም ከብቶቻቸውን በሞት እያጡ መሆኑ ችግሩን አባብሶታል፡፡
ችግሩን ለመፍታት መንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተለያዩ ድጋፎችን ቢያደርጉም፣ አሁንም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ለከፋ ረሃብ እየተጋለጡ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ይደመጣል፡፡

በተለይ በአማራና በትግራይ ክልሎች ውስጥ ችግሩ የከፋ ሲሆን፣ በእነዚህ አካባቢ የሚገኙ ወገኖች አፋጣኝ ድጋፍ ካላገኙ ሕፃናት፣ አረጋውያን፣ ወጣቶች፣ እንዲሁም እንስሳት ለሞት የሚጋለጡበት አጋጣሚ ሰፊ እንደሆነ ሁኔታው ያሳያል፡፡
የትግራይ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኣለምብርሃን ሃሪፈዮ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በትግራይ ክልል በሚገኙ 27 ወረዳዎችና 107 ቀበሌዎች ውስጥ ባለፉት ሦስት ወራት በተከሰተው ድርቅ 2,800 ሰዎች ሞተዋል፡፡
በትራግይ ክልል ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ብቻ 237 ሰዎች በረሃብ መሞታቸውን የተናገሩት ምክትል ኃላፊው፣ በክልሉ የተከሰተው ድርቅ በዚሁ ከቀጠለ በርካታ ሰዎችና እንስሳት ለሞት እንደሚዳረጉ አስረድተዋል፡፡
በክልሉ የተሻለ ምርት ይገኝበታል በተባለው ሰሜን ምዕራብ አካባቢ በተከሰተው የበረሃ አንበጣ መንጋ፣ ከፍተኛ የሰብል ምርት መውደሙን አክለው ገልጸዋል፡፡
በተለይ የደቡብ ምሥራቅ አካባቢዎች ከፍተኛ ድርቅ ያለባቸው መሆናቸውን ገልጸው፣ 132 ሺሕ ሔክታር መሬት በድርቅ መመታቱን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በ31 ወረዳዎች ውስጥ ድርቁ መከሰቱን ያስታወሱት ኣለምብርሃን፣ በተለይ በክልሉ የከብት መኖ፣ የመጠጥ ውኃ እንዲሁም የመድኃኒት እጥረት በመከሰቱ ምክንያት ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ሰዎች ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን አብራርተዋል፡፡
በክልሉ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የተፈጥሮ ሀብቶች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ በጦርነቱም ሆነ በድርቁ የተነሳ ቁጥራቸው በውል የማይታወቁ ሰዎች መሞታቸውን ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ በክልሉ የሴፍቲኔት ተጠቃሚ የነበሩ አርሶ አደሮችም ሆኑ አረጋውያን አገልግሎቱ ስለተቋረጠባቸው ለችግርና ሞት እየተዳረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ በክልሉ ጦርነቱ የፈጠረው ችግር ዕልባት ሳያገኝ ድርቅ መከሰቱ፣ በሥራቸው ችግር እየፈጠረ መሆኑን ያስታወሱት ኃላፊው፣ ይህንን ችግር ለመወጣትና ማኅበረሰቡን ለመታደግ መንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
አርሶ አደሩ የተሻለ እንዲያገኝና አንበጣም በተከሰተባቸው ቦታዎች ማኅበረሰቡ ተደራጅቶ እንዲመክት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከዚህ ቀደም የአንበጣ መንጋውን ለመመከት የግብርና ሚኒስቴርም ኬሚካልና ባለሙያችን በመመደብ የበኩሉን ድርሻ መወጣቱን አስታውሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ በክልሉ ከተፈጠረው ችግር አንፃር የእንበጣ መንጋውን ለማጥፋትም ሆነ ለድርቁ የተደረገው ድጋፍ አነስተኛ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በክልሉ እስካሁን ባለው ሁኔታ 2,800 ሰዎች፣ 28,330 እንስሳት መሞታቸውን ገልጸዋል፡፡
በክልሉም ‹‹ኤሌፊዲ›› የተሰኘ እንስሳትን የሚያጠቃ ወረርሽኝ በስፋት በመሠራጨቱ፣ 31 በመቶ የሚሆኑ እንስሳት መሞታቸውን ስምንት በመቶ ደግሞ መታመማቸውን አስረድተዋል፡፡
ባለፉት ሦስት ወራትም በክልሉ የሴፍቲኔት ተጠቃሚ የሆኑ አርሶ አደሮች ሆኑ አረጋውያን ምንም ዓይነት ክፍያ ባለማግኘታቸው የተነሳ ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ ከፌዴራል መንግሥትም ሆነ ከሌሎች ተቋሞች የሚደረገው ድጋፍ በቂ የሚባል እንዳልሆነ የተናገሩት ኃላፊው፣ ሰዎች ድጋፍ ማግኘት ካልቻሉ፣ በክልሉ ከዚህ የበለጠ ሞት እንደሚመዘገብ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በክልሉ 13,780 ሔክታር መሬት በአንበጣ መንጋ መጠቃቱን ጠቅሰው፣ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ በተከሰተ የአንበጣ መንጋ 8,500 ሔክታር መሬት መጠቃቱን አስታውሰዋል፡፡
የተከሰተውን ድርቅ ለመመከት ውኃን ከሩቅ ለመሳብ የሚያስችሉ ሞተር ፓምፖችና የመኖና ሌሎች መሰል ነገሮች እጥረት እንዳጋጠመም አክለው ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል የአደጋ መከላከልና የምግብ ዋስትና ኮሚሽን የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ዳይሬክተር ኦቶ ብርሃኑ ዘውዱ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአማራ ክልል በስምንት ዞኖች ላይ ከፍተኛ ድርቅ በመከሰቱ ምክንያት ከ77 ሺሕ በላይ የቁም እንስሳት ሞተዋል፡፡
በክልሉ ድርቅ ለተከሰተባቸው ቦታዎች ምላሽ ለመስጠት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) አማካይነት የተዋቀረ ቡድን እንዳለ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ቡድኑ ምን ያህል ሰዎች ሞተዋል? ለምን ያህል ሰዎች ድጋፍ ያስፈልጋል? የሚለውን ለማወቅ የመለየት ሥራ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በተለይ ‹‹በድርቅ ምክንያት ምን ያህል ሰዎች ሞተዋል?›› የሚለውን ለመለየት፣ በክልሉ ውስጥ የተከሰተው ጦርነት ችግር እንደሆነባቸው ገልጸው፣ ለእንስሳት መኖ፣ ለውኃ፣ ለምግብና ለሌሎች መሠረታዊ ነገሮችን ሀብት ማሰባሰብ ካልተቻለ በርካታ ዜጎች ሊሞቱ እንደሚችሉ አብራርተዋል፡፡
በአማራ ክልል የተከሰተው ድርቅ ከዚህ በፊት በቦረና አካባቢ ከተከሰተው ድርቅ ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ፣ ድርቁም በ45 ወረዳዎች ውስጥ መከሰቱን፣ እነዚህም ድርቁ በተከሰተባቸው ስምንት ዞኖች ሥር እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በከፍተኛ ሁኔታ ድርቅ በተከሰተባቸው 17 ወረዳዎች ለአንድ ቀን የሚሆን ከ9 ሺሕ በላይ ኩንታል እህል ክልሉ በራሱ ወጪ ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው፣ በተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ የውኃ እጥረት በመከሰቱ ምክንያት በርካታ ዜጎች በቆዳ በሽታ ሊጠቁ መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በክልሉ በርካታ ዜጎች ከቀዬአቸው መፈናቀላቸውን፣ ለእነዚህ ተፈናቃዮች የዕለት ከዕለት ድጋፍ ለማድረግ ቀርቶ ለአንድ ጊዜ የሚሆናቸውን ግብዓት ለመሸፈን ክልሉ ችግር ውስጥ መሆኑን አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡
በአማራ ክልል ከሚገኙ ነዋሪዎች ውስጥ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ችግር ውስጥ መሆናቸውን፣ ይህም በግጭት ቀጣና ውስጥ ያሉ ዞኖችንና ሦስት ወረዳዎችን ሳይጨምር መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡
ከችግሩ አንፃር፣ በክልሉ እዚህ ግባ የሚባል ድጋፍ እየተደረገ አለመሆኑን ገልጸው፣ ይህንን ምላሽ ለመስጠት ሰፋ ያለ ሀብት ማሰባሰብ ያስፈልጋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በተለይ የምግብ፣ የውኃና የሌሎች መሠረታዊ ነገሮች ድጋፍ ዝቅተኛ ነው ብለዋል፡፡
አብዛኛውን ጊዜ ድርቅ ሲከሰት ሕፃናትና አረጋውያን በሰፊው ተጎጂ እንደሚሆኑ ገልጸው፣ ሕፃናትና እናቶች በምግብ እጥረት በሽታ ውስጥ መውደቃቸውን ጠቁመዋል፡፡
40 በመቶ የሚሆኑ ሕፃናትና እናቶች ለችግሩ መጋለጣቸውን፣ ችግሩ በዚሁ ከቀጠለ በርካታ እናቶችና ሕፃናት ሕይወታቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
በአማራ ክልል የተከሰተወን ድርቅ በተመለከተ መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ድጋፍ በማድረግ የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በኢትዮጵያ በተለያዩ ቦታዎች የተሰከሰተውን ድርቅ ለመመከትና ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ከምግብ ነክ ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረጉ መሆኑን፣ በኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያ ምላሽ ዳይሬክተር አቶ ታዬ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡
ለ7.3 ሚሊዮን ዜጎች በመንግሥት ወጪ በሁለት ዙር ድጋፍ መደረጉን፣ በተለይ በአሁኑ ወቅት የቅድሚያ ቅድሚያ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎችን በመለየት የምግብ፣ የአልባሳትና ሌሎች ድጋፎች እየተደረገ መሆኑን እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡
ከዚሁ ጎን ለጎን በድርቅና በጦርነት ምክንያት ተፈናቅለው መጠለያ ውስጥ ለሚገኙ ወገኖችና በጎርፍ ለተጎዱ ሰዎች ቅድሚያ እንደሚሰጥ ገልጸው፣ አብዛኛው ድጋፍ የሚከናወነው በመንግሥት በኩል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ኮሚሽኑ በአሁኑ ወቅት እየሠራ ያለው ከመንግሥትና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች በሚያገኘው ድጋፍ አማካይነት እንደሆነ ገልጸው፣ ለከብቶች፣ ለመኖና ለተለያዩ በሽታዎች የተጋለጡ ሰዎችን ለመርዳት የዓለም ጤና ድርጅትንና ግብርና ሚኒስቴርን የሚመለከት ጉዳይ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ለተለያዩ ችግር ለተጋለጡ ወገኖች 80 በመቶ የሚሆን ምግብ ነክ ነገሮችን ኮሚሽኑ ድጋፍ ማድረጉንና የከፋ ችግር ውስጥ ያሉ ቦታዎችን የመለየት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በተለይ አማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያና አፋር ክልሎች በከፍተኛ ሁኔታ በድርቅ መጎዳታቸውን ገልጸው፣ በእነዚህም ክልሎች ውስጥ ከድርቅ በዘለለ በርካታ ዜጎች ከቀዬአቸው መፈናቀላቸውን አክለዋል፡፡
ኦቻ ከሳምንት በፊት ባወጣው ሪፖርት በአማራ፣ በትግራይና በአፋር ክልሎች በተለያዩ ሥፍራዎች የሚኖሩ ዜጎች ለተመጠጠነ ምግብ እጥረት ተጋልጠዋል፡፡
በአፋር፣ በአማራ፣ በድሬዳዋ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሌያና በትግራይ አካባቢዎች የበረሃ አንበጣ ያስከተለው ውድመት የምግብ ዋስትናውን ይበልጥ ችግር ላይ ጥሎታል፡፡ ከመስከረም እስከ ታኅሣሥ የወባ በሽታ ሥርጭት የሚጨምርበት መሆኑን በመግለጽም ለዚህ የሚሰጠውን ምላሽና ዝግጁነት ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡
እንደ ኦቻ 20.1 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የምግብ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ 4.4 ሚሊዮን ደግም የተለያዩ ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች የሚፈልጉ ሲሆን፣ ለዚህ ምላሽ ለመስጠት 4 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል፡፡ እስካሁን 1.2 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን ኦቻ የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርቱ አሥፍሯል፡፡
