
ተሟገት የመከራ መካሪነት ምክር ለመስማታችን ዋስትና?
ቀን: October 22, 2023
በበቀለ ሹሜ
እጅግ የከፋ የመከራ ምክር የደረሰበት አካባቢ የመከራውን ብርታት ያህል የጠለቀ ትምህርት ይወስዳል ብሎ በጥቅል መደምደም አይቻልም፡፡ በማያዳግም ደረጃ ከመከራ የመማር ውጤት በብዙ ሰበዞች መስተጋብር የሚወሰን ነው፡፡ በመሬት ግብግብ አገር እስከመናድ አደጋ ከርሮ በሰሜን ኢትዮጵያ የደረሰው አገርን ያራገፈ፣ የአካባቢ ሕዝቦንችም የህልውና አቅም መቀመቅ ያወረደ ዕልቂትና ውድመት፣ ጠመንጃ በዞረበት አያዙረኝ/ጠብ ደጋሾችን አያሳየኝ ሊያሰኝ የሚገባው ነው፡፡ የቂም፣ የጥላቻና የዕብሪት ምርኮኝነትን እየሰባበረ ፈጣሪና ሕዝብን ማረኝ ወደ ማለት ሊወሰድ የሚገባው ነው፡፡ ነገሮች ግን እንደዚያ እየሆኑ ነው? በጦርነቱ ጊዜ በተወራሪ ሥፍራዎች ላይ እንዲውሉ በወጣቶች ህሊና ላይ የተዘሩ የጥላቻና የበቀል መርዞች በሌሎች አካባቢዎች ተረጭተው ከተመለሱ በኋላ በሥርዓት አልባነት ክፍተትና በጉርስ ፈተና ግፊት ትግራይም ላይ ቢፈጸሙ አያስገርምም፡፡ ወጣቶቹን የመረዙትና የወረራ ማገዶ ያደረጉት ሰዎች ግን ሕዝብን ማረን የሚያሰኝ ፀፀት አንገታቸውን ምን ያህል ሰብሯል? ያን ሁሉ ሰውና ጥሪት የበላ ጦርነት ካከተመ በኋላ ሕዝብ እህህታውን በሆዱ ይዞ በሰላም ወጥቶ ለመግባት እንኳ የተቸገረበት የትግራይ እውነታ ሕዝብን የመካስ መንፈስን አያንፀባርቅም፡፡ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ውጪ የማይታይ ድብቅ እስር ቤት ያለው ሥውር የአፈናና የዘረፋ ‹‹መንግሥት›› መሳይ አካል መኖሩ ፀፀትን አይናገርም፡፡
በጠራራ ፀሐይ ግድያ፣ የሴቶች መደፈርና ዘረፋ በሚከሰትበት ትግራይ ውስጥ፣ የትግራይ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የትግራይን ሕዝብ እንደ ሕዝብ ለማጥፋት የተካሄደ ጦርነት የሚል ‹‹ቂም›› ሙጥኝ ብሎ የመያዙስ እንቆቅልሽ ምን ተብሎ ይፈታል? የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጦርነት ወንጀል ነክ ድርጊቶች በጦርነት ጊዜ ሊፈጸሙ የሚችሉ እንደመሆናቸው፣ እነዚህን ነገሮች በተመለከተ ማንም እንቅስቃሴያችን ፅዱ ነበር ለማለት የሚችል አይመስለኝም፡፡ የሰሜኑ ጦርነት ‹‹የትግራይን ሕዝብ እንደ ሕዝብ ለማጥፋት የተካሄደ ጦርነት›› የሚል ክስ ግን መቶ በመቶ ብቻ አይደለም፣ ለመቶኛ መግለጫ የሚውል ቁጥርን ሁሉ ተጠቅሞ ሐሰትነቱን መመስከር በእርግጠኝነት ይቻላል፡፡ የሰሜን ዕዝን አዘናግቶና በመልከ-ብዙ ግፍ ሰባብሮ አገር የማጥቃት ወረራ የተከፈተው ከዚያው ከትግራይ ነበር፡፡ በእነዚህ ሁሉ ተግባራት ውስጥ የቤተ ክህነት ሰዎች ሚና ተጫውተዋል፡፡ የመጀመሪያው ጥቃት ተመክቶና ከሽፎ፣ የአገሪቱ መከላከያ ከትግራይ ከወጣም በኋላ ሁለት ጊዜ ወረራዎች የተከፈቱት ከትግራይ መሆኑ ሊካድ የማይችል እውነት ነው፡፡ በጦርነቱ ጊዜ፣ ይህንን ሁሉ የሸመጠጠና ‹‹የትግራይን ሕዝብ እንደ ሕዝብ ለማጥፋት የተካሄደ›› የሚል ውንጀላ ከጦረኞቹም ከቤተ ክርስቲያን ግድምም ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ፣ እንዲህ ያለ ውሸት ፕሮፓጋንዳዊ የውጊያ ጥቅም ስላለው መደረጉ አይደንቅም፡፡
ጦርነቱ ቆሞ፣ ድርድርና ስምምነት ተከናውኖ፣ ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሞ፣ ግንኙነቶች መለስለስ በጀማመሩበትና የሕዝብ ለሕዝብ ዕርቅ በሚናፈቅበት ሁኔታ ውስጥ፣ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክን ያካተተ የይቅርታና የዕርቅ ተማፅኖ ትግራይ ድረስ መጥቶ እጁን ሲዘረጋ፣ በግንባር መገናኘትን እስከመንፈግና ወንጃይ ሠልፍ እስከ ማካሄድ ድረስ የቂም ሃይማኖተኛ መሆን በምን ይብራራል? ‹‹የትግራይ ሕዝብን እንደ ዘር የማጥፋት ጦርነት ተካሄደበት›› የሚል ቂም በሃይማኖት መሪዎች ስለተያዘ የታሪክ ሀቆች አይደመሰሱም ወይም ድራሻቸው አይጠፋም፡፡ ወይስ በዕብሪተኛ ጦረኝነት የትግራይን ወጣት ርካሽ ማገዶ ያደረገውን ፖለቲካ ከመቃብር ለማስነሳትና የትግራይ ሕዝብን ህሊና ዳግም እንዲቆጣጠር ለማድረግ የሚለፉ የሃይማኖት መሪዎችን እያየን ነው? ወይስ ትግራይን የመነጠል ጤና ቢስ የፖለቲካ ፍላጎት ቤተ እምነት ውስጥ ተሸሽጎ እንዲቀመጥ ተፈልጓል? ወይስ ለወረራ የተድፋፋውን የወጣቶች ደም በአርበኝነት ተጋድሎ ሊሠውር ለሚሻው ቡድን ቡራኬ ሰጪ ለመሆን ተፈልጎ ነው? እስከዚህ ድረስ ሃይማኖት የፖለቲካ መሣሪያ ሆኗል እንበል? እንዲህ ያሉ ገታራ አቋሞች እንደምን ለተማመነ የጋራ ልማት አስፈላጊ የሆነውን ዕርቅ ለማግኘት ይጠቅማሉ?
ወደ አማራ አስተዳደር መለስ እንበል፡፡ የአማራ ሕዝብ ውሎ ያደረ የበደልና የጥቃት ሮሮ እንዳለው፣ በዚህ ዙሪያ ያሉ ጥያቆዎችም እንዳሉት ግልጽ ነው፡፡ ራሱን ‹‹የኦሮሞ ነፃ አውጪ ሠራዊት›› ብሎ የሚጠራ ቡድና ቡድን መሬት አለኝ ባለባቸውና ሰላም ለመንሳትና ኢኮኖሚ ነክ ጥቃት ለማድረስ ይመቹኛል ባላቸው ሥፍራዎች እየገባ ሲተኩስ ቆይቷል፡፡ ለዚህ ቡድንና ለብጤዎቹ ተኳሾች ንፁኃን አርሶ አደሮችን፣ ሕፃናትና አዛውንቶችን በጭካኔ መግደል፣ ንብረታቸውን መዝረፍ/ማቃጠል ታክቲክ ነው፡፡ በዚህ ጥቃት ውስጥ ደግሞ የአማራ ዒላማነት ጎልቶ ቆይቷል፡፡ በዚህ የአራጅነት ታክቲክ ምክንያት የፌዴራል መንግሥትና ጥቃት የሚመላለስባቸው የአካባቢ አስተዳደሮች በሥውር አስጠቂነት ሲጠረጠሩ ኖረዋል፡፡ ጥርጣሬው እንዲወፍር ያስቻሉ ነገሮች ከጊዜ ጊዜ እየተጋገዙና እየተደራረቡ የመጡ ናቸው፡፡ የጥቃቶች አለመደረቅ፣ ለአማራ እንቆረቆራለን የሚሉ ፖለቲከኞችም ይህንኑ ሁኔታ በሥውር ሻጥር ሲተረጉመት መቆየታቸው፣ የፕሪቶሪያው ስምምነት አተገባበር ድፍንፍን ያለ መሆኑ፣ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሥልጣን ከግለሰቦች መለዋወጥ በቀር በድፍኑ በሕወሓታውያን እጅ እንዲገባ መደረጉ፣ ከዚህ ድርጊትና ከመመሳጠር ሐሜት ጋር ‹‹ሕወሓት መሣሪያ ደብቋል… የተደበቀ ሠራዊት አለው… የውስጥ አዋቂ መረጃ አለን…›› የሚል የሶሻል ሚዲያ ውስወሳ መድራቱ፣ ይህ ውስወሳ መረጃ በመስጠትና መረጃ በመተርጎም ስም አማራ ውስጥ ያሉ የታጠቁ አካላት እንዲያምፁ የለየለት ቅስቀሳና ‹‹ሳይቀሰቅሱ›› የመቀስቀስ ሥራ መሥራቱ፣ የፌዴራል መንግሥት በመንግሥትና በሕዝብ መሀል ሊኖር የሚገባውን ትምምን በማፋፋትና በመንከባከብ ረገድ ያለበትን ድክመት እንደታቀፈ፣ ‹‹ሕወሓት ባግባቡ ትጥቅ አልፈታም…›› የሚል ወሬ በተንሰራፋበት አየር ውስጥ ‹‹ልዩ ኃይልን›› እና ኢመደበኛ ታጣቂነትን ወደ መከላከያና ወደ መደበኛ ፖሊሲ ሥምሪት የማዛወር ዕቅድ ማምጣቱ፣ እናም የዕቅዱ ውስጠ ወይራ ‹‹አማራ ሕወሓትን እንዳይመክት የማድረግ ደባ ነው/እነ ወልቃይትን ለሕወሓት ለማስረከብ ነው…›› የሚል የሴራ ትንታኔ ማኅበራዊ ሚዲያን ማጣበቡ፣… ይህ ሁሉ በተጋገዘበት ውስወሳ ተገፋን/ተካድን የሚል ስሜት ንሮ፣ በአማራ ክልል ውስጥ እንቢኝ ባይ የፋኖ ትጥቅ ትግሎች እዚያም እዚያም ተከሳሰቱ፡፡ ከዚያ በኋላ በፖለቲካ ‹‹መሪነት›› ታጣቂዎቹን የመፈናጠጥ ሩጫው፣ የ‹ግፋ በለው› ሞቅ ሞቁ፣ ከመከላከያ ጋር መጋጨቱ፣ የፋኖዎችን ኃያልነት የሚያናፋ የፕሮፓጋንዳ ቱማታው፣ ሰላም ማጣት የክልሉ ትልልቅ ከተሞች ድረስ መዝለቅ ሁሉ ተከታተሉ፡፡ እናም፣ የክልሉ አስተዳደር በመደበኛ ሁኔታ ማስተዳደር አለመቻሉን አንተርሶ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ በጠየቀው መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አስተዳዳርና የመከላከያ ኃይል ፀጥታ የማስከበር ሙሉ እንቅስቃሴ መጣ፡፡ አጠቃላይ ሥዕል ለማግኘት እስካሁን የተባለው በቂ ነው፡፡
በአማራ ክልል ውስጥ ፋኗዊ ትጥቅ ትግል ብዙ ሰው የደገፈው ሆነም አልሆነ፣ ለአማራ ሕዝብ የሚበጅ ነው?
ወደ እንቢኝ ባይ የጠመንጃ ትግል የተዞረው ልዩ ኃይል ፈርሶ ወደ መከላከያና መደበኛ የፖሊስ መዋቅር (ፍላጎት፣ መመዘኛዎችና ሥልጠና በተቀናበሩበት መልክ) ይደልደል የሚል የመንግሥት ውሳኔ በመጣ ጊዜ ነው፡፡ ሌሎች የአካባቢ አስተዳደሮች ውሳኔውን ሲቀበሉ አማራ ውስጥ ከማንገራገርም በውሳኔው ላይ መሸፈት የተከሰተው፣ ቀደም ብሎ እንደተገለጸው ‹‹አማራ ለሌላ የሕወሓት ወረራ ይጋለጣል/ወልቃይትና ራያ እንደገና በሕወሓት ይያዛሉ…፣ መንግሥት ከሁሉ በፊት የአማራ ልዩ ኃይልንና ፋኖን ትጥቅ ለማስፈታት የፈለገው በአማራ ላይ የተደበቀ አጀንዳ ስላለው ነው፣ ወዘተ›› የሚሉ ውስወሳዎች አዕምሮና ስሜትን መጋለብ ስለቻሉ ነበር፡፡ መንግሥት በቂ የትምምን ሥራ ያለ መሥራት ጥፋቱ የፈለገውን ያህል ቢሆን፣ መንግሥትን መጠራጠርና የማኅበራዊ ሚዲያ አሳሳችነት ጠመንጃ ለማንሳት ተገቢና በቂ ምክንያት ነው ብሎ መከራከር ፈፅሞ አይቻልም፡፡ ወይስ ከዚህ የላቀ ትክክለኛ ምክንያት ከጀርባ አለ? እንፈልግ፡፡
የሕወሓት ወረራ የተከሰተው የልዩ ኃይል መዋቅር በነበረበት ጊዜ ነው፡፡ ያኔ ከትግራይ ውጪ ያሉ የክልል መንግሥታት፣ የፌዴራሉ መንግሥትና ሕዝቦች ጥቃቱን የመላ ኢትዮጵያ ጥቃት ብለው ነበር የተንቀሳቀሱት፡፡ ይህ የመስተጋብር መርህ ልዩ ኃይሎች ፈርሰው መከላከያንም ሆነ መደበኛ ፖሊስን ስለተቀላቀሉ የሚቀየር አልነበረም፡፡ ክልሎች ጦር አደራጆች ለመሆን የቻሉበትን ቀደዳ ደፍኖ ልዩ ኃይሎችን ሕገ መንግሥታዊ የአወቃቀር ሥርዓት ውስጥ ማስገባትም የኃይል አቅምን አያጎድልምና ክልሎችን ለጥቃት ስለማጋለጡ መርቻ ማስረጃ ማቅረብ አይቻልም፡፡ ሕወሓት የተደበቀ መሣሪያና ጦር ኖሮት ለወራራ ብቅ ቢል (ወልቃይትና ራያን በኃይል ወሮ ለመያዝ ቢሞክር) የፕሪቶሪያውን ስምምነት በመሸፈጥ/በሕገወጥና በወራራ ተግባር ከመንግሥትና ከመላ ኢትዮጵያ ጋር ነው የሚጋጨው፡፡ ይህንን ያላስተዋለው ፋኖ ዘራፍ ብሎ ከመከላከያ ጋር ውጊያ ውስጥ መግባቱ በምንም ተዓምር እነ ወልቃይትን ከጥቃት ለመጠበቅ ወታደራዊ አቅም አይሆነውም፡፡ የእነ ወልቃይት በትግራይ ክልልም ውስጥ ሆነ በአማራ ክልል ውስጥ የመካተትና የመቆየታቸው ነገር በየአካባቢዎቹ የጉልበት ኃይል የሚከናወን ሳይሆን በሰላማዊ መፍትሔ የሚከናወን ነው፡፡ እስካሁን ሳይፈታ የቆየውም ተመልሶ ወደ ዘራፍ ባይነት በማያስገባ አኳኋን ችግሩን ለመፍታት የሚያስችሉ ሁኔታዎች ስላልነበሩ መሆኑም ግልጽ ነው፣ ለእኔ ይዳላ ላልተባለ በቀር፡፡ ከልዩ ኃይልና ከፋኖ ታጣቂዎች እየሸፈቱ ወደ አመፅ መግባትም የጉዳዩን በሰላምና በመግባባት የመፈታት ዕድል ያርቀዋል እንጂ አያቀርበውም፡፡ በመደበኛና ሕጋዊ የኃይል መዋቅሮች ውስጥ ገብቶ የአካባቢና የአገር መከታ የመሆንን ዕድል ረግጦ የአመፅ ኃይል መሆንም የአማራ ደኅንነትን የማስከበር ክንዋኔን አያስገኝም፡፡ አምፆ ጠመንጃ መተኮስ በቀጥታ የፀጥታ አደፍራሽነት ሠፈር ውስጥ ቀላቅሎ፣ ከመከላከያና ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር መጋጨት ውስጥ ይከታል፤ ከትቷልም፡፡ ይህ እየሆነ በመቀጠሉም፣ አሳር የተከመረበት የአማራ እውነታ የሚጠይቀው አንገብጋቢ የሰላምና ልማት ጥያቄ ተረባበሸ፡፡ በሕወሓት ሁለት ወራራዎች መሠረተ ልማቱና ሌላ ሌላ ጥሪቱ አፈር ድሜ በልቶ፣ ከውስጡ በተፈጠረ መፈናቀልና ከሌላ አካባቢ በመጣ ተፈናቃይነት የተጨናነቀ ምድር፣ በዋናው የክረምት እርሻ ወቅት በሚቻለው ሁሉ ነፍስ በማቆየትና በማገገም ተግባር ላይ እንዳይውተረተር የሚያውክ (የግብዓቶችን/የፍጆታዎችን ሥርጭትና የገበያዎችን መደነቃቀፍ፣ ዕጦትንና መፈናቀልን የሚያብስ)፣ ሰላም ማጣት እዚያም እዚያም ተባዛበት፡፡ የፋኖ የጠመንጃ ትግል ብዙ ሆይ ሆይ ባይ ኖረውም አልኖረውም፣ ለአማራ ሕዝብ ከአንጀት እቆረቆራለሁ የሚሉ ሰዎች ሁሉ መመለስ ያለባቸው ቁልፍ ጥያቄ ያለው፣ አሁን የአማራ ሕዝብ ህልውና የገባበት አዙሪት ውስጥ ነው፡፡
‹‹መንግሥት ጥያቄዎቻችንን እስካልመለሰ ትግላችን ይቀጥላል›› የሚባልላቸው ጥያቄዎች አንድ ላይ ተደምረው በከባድ ጉስቁልና ውስጥ የሚገኘው የአማራ አካባቢ ሕዝብ በአሁን እውነታው የሚያሻውን ሙሉ ቀልብንና ጥሪትን ያማቀቀ ኑሮን በማቅለል ርብርብ ላይ የማዋል ተግባርን ይበልጣሉ? የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ፣ ከመከላከያ ጋር እየተታኮሱ የአማራን ሕይወት ማመስን ይሻል? የወልቃይትና የራያ የማንነት ጥያቄ ምላሽና በሌላ አካባቢ የሚከሰት የአማራን ጥቃት የማስቆም ትግል የአማራ ሕዝብን ሰላም በጠመንጃ መረበሽን ይሻል? ይህ የትግል ዘዴ ለአማራ ሕዝብ የደቀቀ ሕይወት በቡሃ ላይ ቆረቆር ከመጨመር በቀር ዕውን ይፈይዳል?
የመንግሥት ሲቪልና ወታደራዊ መሪዎች ጎርጎራን በጎበኙበት ሰሞን ‹‹ከበባና ጥቃት ተሞክሮ ለትንሽ ተረፉ›› ሲባል የሰማነው የጉራ ወሬ እውነት ለመፈጸም ችሎ ቢሆን ኖሮ፣ ኢትዮጵያ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት እንተወውና፣ የአማራ ሕዝብ እንዳይሆኑ ለመሆን አደጋ አይጋለጥም ነበር? እንዲህ ያሉት የውርውር እንቅስቃሴዎችና ከተለያዩ የፋኖ ትግል አካባቢዎች የምንሰማቸው ሐሳቦች የማይገጣጠሙ ናቸው፡፡ ‹‹ጥያቄዎቻችን ከተመለሱ መሣሪያ እናወርዳለን… ይህ ሥርዓት ባህርይውን እስኪቀይር ድረስ ትግሉ ይቀጥላል/ዓላማችን ሥርዓቱን መቀየር ነው…፣ አማራነት ታክቲካችን ኢትዮጵያዊነት ስትራቲጂያችን…›› የሚሉት ንግግሮች ውስጥ ያለው የሐሳቦች መፈነጋገጥ ትግሉ ውል የያዘ የፖለቲካ ዓላማ እንደሌለው የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ ድምዳሜዬ የፋኖን ትግል ከማዋደቅ ይቆጠር ይሆናልና የነገሮችን መሄጃና መድረሻ እየተሰነዘሩ ካሉት ሐሳቦች ጋር እያገናዘብን ጥቂት እንፈትሽ፡፡
- ጥያቄዎቻችን ከተመለሱ የመሣሪያውን ትግል አቁመን ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንመለሳለን የሚባለው እንደምን ተጨባጭ ይሆናል? የጥያቄዎቹ ምላሽ ከየትኛውም የኃይል አስገዳጅነት ተላቆ ለሰላማዊ የመፍትሔ ፍለጋ ዝግጁ መሆንን ይሻል፡፡ የጥያቄዎቹ አመላለስም የአማራን ፍላጎት በማሟላት በጎ ፍላጎት ውስጥ የሚገባደድ አይደለም፡፡ በሌሎች አካባቢዎች ያለ የአማሮችን ጥቃትና መፈናቀል እንዳያዳግም አድርጎ የማስቆም ጉዳይ፣ የአጠቃላይ ኢትዮጵያን ሰላምና መረጋጋት የማሳካት ጉዳይ ነው፡፡ ከእነ ወልቃይትም ጋር የተያዘው ጥያቄና መልስም ከአማራ በኩል የቀረበውን ፍላጎት ተግባራዊ የማድረግ ጉዳይ ሳይሆን የሁለት አካባቢዎችን ጉዳይ የመዳኘት ጉዳይ ነው፡፡
- ‹‹የትግራይ መከላከያ ኃይል›› ብሎ ራሱን የጠራ ሕወሓታዊ ጦር በጥቅሉ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ በፈጸመበት ጊዜ የኢትዮጵያን ጦር የአንድ ፋሽስት ግለሰብ ጦር አድርጎ ሲሥል የነበረው ኢትዮጵያን የመናድ ግብን በጊዜው አንግቦ ስለነበር ነው፣ ለዚያ ይጠቅማኛል ያለውን የፕሮፓጋንዳ ሰይፍ ሁሉ ተጠቅሟል፡፡ የአማራ ፋኖዎች ይህንን ትምህርት ብለው ቀድተው በአራጋቢዎቻቸው በኩል የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት ‹‹ፀረ ሕዝብ/የዓብይ ጦር/ የአንድ ብሔር ጦር›› እያሉ ስም ማጉደፋቸው፤ የጥያቄዎቻቸውን መልስ የሚጠቅም ሳይሆን የሚጎዳ ነው፡፡ ጉዳቱ ከዚያም የከፋ ነው፡፡ ክፋቱን ቀለል ካደረግነው ውግዘቱ ሁሉ የኢትዮጵያ መላ ኅብረተሰብ ልጆቹንና የአገር ፍቅሩን አገማሽሮ ያደረጀውን መከላከያ ኃይል ወደ አንድ ግለሰብ/ወደ አንድ ብሔር ይዞታነት እንዲቀየር የሚለማመን ድንቁርና ነው፡፡ መድረሻ ውጤቱን ካሰብነው ደግሞ ኢትዮጵያን የሚፈረካክስ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ‹‹አማራነት ታክቲካችን ኢትዮጵያዊነት ግባችን›› ባይነት ባዶ ቧልት ነው፡፡
- ‹‹የዓብይ መንግሥት ባህርይውን እስኪቀይር›› ባይነትንና ‹‹ሥርዓቱ እስኪለወጥ…›› ባይነትን አንድ ሐሳብ አድርገን ብንወስድ፣ የፋኖዎች ትግል ሕገ መንግሥቱንና አወቃቀሩን ‹‹የአንድ ግለሰብ/የአንድ ብሔር›› ካሉት ጦር ጋር እስከማስወገድ የረዘመ የፖለቲካ ግብ ሊኖረው ነው፡፡ ‹‹ትግላቸው›› ይህንን እንደምን ተጨባጭ ሊያደርገው? የፖለቲካ ምሪት በመስጠት ስም ፋኖዎችን ሊጋልቡ ከሞከሩት ሰዎች አንዱ ግደይ ዘረዓ ፂዮን እንዳለው፣ የአማራ ፓርቲ ሆነው ባንክ እየዘረፉ በረዥም የትጥቅ ትግል ሥልት ነፃ የአስተዳደር መሬት እየፈጠሩና እያስፋፉ ከሌሎች ነፃ አውጪዎች ጋር ከረዥም ዓመታት በኋላ አዲስ አበባን በመቆጣጠር ነው? ለመሆኑ ፋኖዎች ማን ማን ከሚባሉ ፓርቲዎችና ‹‹የነፃነት›› ቡድኖች/ሠራዊቶች ጋር ተቃቅፈው ነው ኢትዮጵያን አዲስ ሥርዓት ውስጥ የሚያስገቧት? በ‹ነፃ አውጪ› ጦር ድል አድራጊነት የእነ ወልቃይትና ራያን የአማራ ይዞታነት ሲያረጋግጡ፣ የትግራይን የኢትዮጵያ አካልነት የሚያስቀጥሉት ከእነ ማን ጋር ሆነው? አማራን ሲያጠቁ ከነበሩና አማራንም ፋኖንም በነፍጠኛነት ከሚያዩ ጠመንጃ የያዙና ያልያዙ ቡድና ቡድኖች ጋር እንደምን ይግባባሉ? ወይንስ የፋኖ ሠራዊት ግዙፍ የሆነበትና እንደ እስክንድር ነጋና ሻለቃ ዳዊት የመሳሰሉት ሰዎች ቁንጮ የሆኑበት የኢትዮጵያ ኃይሎች ሰብስብ ተፈጥሮ ‹‹ፀረ አማሮችንና›› ተነጣዮችን በኃይል ልክ የማስገባት ዘመቻ ይከፈታል?
- የፋኖዎች የጠመንጃ ትግል አፍላ ሞቅ ሞቅ ላይ በነበረበት ሰዓት፣ ከሕውሓታውያን አካባቢ ‹‹በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሠራዊት አለን…፣ ትጥቅ መፍታት የሚባለው ነገር እንደሚባለው አይደለም…፣ የፌዴራል መንግሥት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት መሬቶቻችንን ያስረክበን፣ አለዚያ ሌላ አማራጭ ለመውሰድ እንገደዳለን…›› የሚሉ ቃላት በሚዲያ ብቅ ሲሉ እነዚህን መረጃ ብሎ ከመበተንና በአማራ ላይ የተጎነጎነ ሴራ አለ ባይነትን ከማደለብ ይልቅ፣ የአባባሎቹን ሥውር መልዕክት ገላልቦ የሚያሳይ እንደምን ታጣ? የፕሪቶሪያውን ስምምነት የጀርባ ደባ እንዳለው አድርጎ የአማራ ብሶት እንዲረዳው፣ የፋኖ ትኩስ ኃይልም የጠመንጃ ትግሉን ይብስ አቀጣጥሎ የእኔ የሚለውን ሕዝብ ህልውና መቀመቅ እንዲያወርድና ራሱም እንዲራገፍ ለመቆስቆስ ያለመ መልዕክትን ፈልፍሎ ማጤን ይህን ያህል ከባድ ነበር? በመቶ ሺዎች ድብቅ ሠራዊት አለን ብሎ በይፋ መናገርም የፌዴራል መንግሥትን ‹‹ና ትጥቅ አስፈታን›› ብሎ ራስን ከማጋለጥ አይለይም፡፡ ያን ያህል ቁጥር ሠራዊት ያለው ቡድን ከትጥቅ መፍታት ለማምለጥ ሚስጥሩን ይደብቃል እንጂ አይለፍፍም፡፡
- ይህችን ታህል አሠላስሎ ዓይንን መግለጥና ስሜታዊነት የሚያበርድ ጥረት ማድረግ ከባድ ነበር? ቀላሉን ነገር ከባድ ያደረገው ፋኗዊ ብሔርተኞች ከእነጋላቢዎቻቸው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተሰሚነታቸው የት ድረስ እንደሆነ አለማወቃቸው፣ የአማራም ሆነ የኢትዮጵያ ህልውና ምንና ምን እንደሚሻ አለመገንዘባቸውና ጀብደኛ ትግላቸውን በሚያጫፍሩት ብዕሮችና ድምፆች ውስጥ አማራንና ኢትዮጵያን የሚያጠቃ ምን ያህል ደባ እንደተሸሸገ አለመጠርጠራቸው አይሆን ይሆን?
ጥያቄያዊ ፍተሻችን ከዚህ በላይ መርዘም አያስፈልገውም፡፡ የፋኖዎች ‹‹የድል አድራጊነት›› ጉዞ በኢትዮጵያ ምድር ዕውን የሚሆን አይደለም፡፡ እዚያ ደረጃ ላይ ከመደረሱ በፊት፣ የፋኖ ትግል መፍትሔ ያጣ የጉሮሮ አጥንት የሆነበት ሁኔታ ከተፈጠረ፣ ኢትዮጵያ ፍርክስክሷ ሊወጣ የሚችልበት ዕድል ይንጠረበባል፡፡ በረዥም ትጥቅ መንገድም በኩል ሆነ ገጠርና ከተማ ገባ ወጣ በሚል ተኩስ አማራን እያመሱም ሆነ አዲስ አበባን በሽብር ሥልት በሚያናውጥ ትግል ሌላ ባህርይ ያለው መንግሥት እንፈጥራለን የሚል ጉዞ፣ የኢትዮጵያም የአማራም መጥፊያ መሆኑን የሚያስተውል ዓይን ለአማራ እናስባለን ከሚሉ መሀል መታጣቱ ‹‹እግዚኦ!!›› የሚያስብል ነው፡፡ የጎጠኝነትና የብሔርተኝነት ካቴና ይህንን ያህል አዕምሮ ያሳጣል፡፡
የ1960ዎች ተራማጅ እንቅስቃሴ ተደቋቋሶ ከመሸነፉ ጋር ተያይዞ ለሕዝብ ልሥራ የሚል የፖለቲካ ፍላጎት እንኩትኩቱ ወጥቶ፣ ተልዕኮ በግለኝነትና ጥቅም በማካበት ሩጫ ተወርሯል፡፡ ብዙ ሰው ከኢዓማኒነት ወደ አማኒነት ዞሯል፤ አማኝነት ትኩስ በነበረበት ጊዜም ለእምነት መታመንና ሃይማኖታዊ ሥነ ምግባር አክባሪነት ጠንካራ ነበር፡፡ እየዋለ እያደረ ሲሄድ፣ አማኝነት ያንኑ ያህል እየተስፋፋ ቢመጣም፣ ከጊዜ ጊዜ የሰብዕና መከርጨትና የሥምረቱ መፋለስ (ዳይኮቶሚ) እየጨመረ ሄዷል፡፡ የሥምረት መፋለሱ አፍና ልብን፣ አፍና ተግባርን እስከ ማለያየት የዘለቀ ነው፡፡ ራስ ወዳድነት/የአጋጣሚ ጥቅመኝነት፣ ሙሰኝነት የኑሮ ፍልስፍና በመሆን ምላጩ ያልሰረሰረው ሰብዕናና ቤተ እምነት የለም፡፡ በዚህም ሥርሰራው የትኛውንም ቀዳዳ ተጠቅሞ የግል ጥቅምን ከማካበት መስነፍን ከጅልነት የሚቆጠር ማፈሪያነት አድርጎታል፡፡ ሰው በጉብዝና የምናደንቅበትን የግብረ ገብነት መለኪያ አወላልቋል፡፡
ያንኑ ያህል ብሔርተኝነትም ሰብዕናን/ለሙያና ለእምነት መታመንን ቦርቡሯል፡፡ በብሔረሰብ አመጣጥ የሰውን ማንነት መለካት፣ ሥልጣንንና የጥቅማ ጥቅም ድርሻን ከብሔረሰባዊ ማንነት ጋር ማገናኘትና መብሰልሰል ተሸሽገውም ሆነ አግጥጠው በሁላችንም ህሊና ውስጥ ሠርገዋል፡፡ ከእነሱ ጋርም አብረው በደል ቆጠራና ቂም እያደቡ ሰውነትን ቦርቡረዋል፡፡ እየተከናወነ ያለ የአሁን በደል በሌለበት፣ ያለፈ ትርክትን ይዞ ሰዎችን በበዳይነት ማየትና ማንጓለል ህሊናን አጨርቷል፡፡ የብሔርተኝነት እንቅስቃሴ እምነትን ሽመሉ እስከ ማድረግ እንደሄደ ሁሉ፣ በእምነት ነክ ግጭቶች ውስጥም የብሔርተኛ አንጓላይነት ትርታን ልናገኝ እንችላለን፡፡ የ‹‹ሀ›› እምነት የብዙኃን በሆነበት አካባባቢ በሰበብ አስባብ ጠብ ተነስቶ በንዑሳኑ ላይ የሚደርሱት የደቦ ጥቃቶች ቀረብ-ጎላ ተደረገው ሲታዩ፣ ‹‹በእኔ ሠፈር መጥተህ ከእኔ እኩል ልትሆን ያምርሃል!? መብትህ በእኔ ሥር መሆኑን አውቀህና አጎንብሰህ እደር›› የሚል ዓይነት አንድምታ አለባቸው፡፡
በየበኩላችን የእምነት አቋም ይኖረናል፡፡ ብሔርተኛ ነኝ/ብሔርተኛ አይደለሁም ልንልም እንችላለን፡፡ የተማርኩ ነኝ እንልም ይሆናል፤ ሌላም ሌላም፡፡ በይፋ አለን የምንለውን አቋምና አድራጎታችንን እየመረመሩ ስህተትነትና ልክነቱን መለየት፣ በዚያም መሠረት ግንዛቤንና ምግባርን ማሻሻል በብዙዎቻችን ዘንድ የሌለ ያህል ሆኗል፡፡ ግንዛቤያችን፣ ጭርንቁስና አዳዲስ እራፊው/እምኩና እብቁ ሁሉ የተደበላለቀበት ግሳንግስ እየሆነ ነው፡፡ የአፍ ለአፍና የሶሻል ሚዲያው አሉባልታና ወሬ ቀን በቀንና ሰዓት በሰዓት ህሊናችን ውስጥ ይንቆረቆራል፤ ልቦናችንና ስሜታችን ያዳውራል፡፡ መንግሥትን መጠርጠር/ከመንግሥት የሚነገርን ሰምቶ ማፍሰስ፣ የሶሻል ሚዲያን ቅራቅምቦ ግን እንደ ሱስ መናፈቅና ሳይጠረጥሩ መዋጥ፣ በሰዎች ህሊና ውስጥ አንድ ላይ ሲኖሩም ለማስተዋል ተችሏል፡፡
በሰብዕና ውስጥ ያየነው የሥምረት መፋለስ (ዳይኮቶሚ) እና ዝግንትልነት በፖለቲካችንም ውስጥ የዘለቀ ነው፡፡ ምላስ የሚያወራው ነገር ከራስ ተግባር ጋር ሊቃርን ይችላል፡፡ ሌላው ላይ የተሰነዘረ ትችት የራስን የተግባር ፖለቲካ የመመዘንና የማቃናት ኃላፊነት ላይኖርበት ይችላል፡፡ ፖለቲከኛነት በትርፍ ጊዜ መሥራት እንደ እሚወዱት ተግባር (ሆቢ) ወይም እንደ አመልም እየሆነ መጥቷል፡፡ ለአንዳንዶች ፖለቲካ ምርጫ ሲመጣ ሞቅ ሞቅ አድርገው ለሥልጣን የሚዋደቁበት፤ ምርጫ ሲያልፍ ደግሞ ነሸጥ ሲያደርጋቸው መግለጫ ብጤ እያወጡ ዕረፍት የሚያደርጉበት መድረክ ነው፡፡ አንዳንዶች በአንድ ፓርቲ ውስጥ ረግተው የማይቆዩ፣ ከአንድ ፓርቲ እያፈነገጡ ሌላ ጋር እየገቡ ወይም በሌላ ስብስብ ሌላ ፓርቲ አቋቁመዋል፣ አደር ካሉ በኋላ እንደገና ወደ ማፈንገጥ የሚመሰሉ ተዟዛሪ (ዘላን) ፖለቲከኞች ዓይነት ናቸው፡፡ ብሔርተኛ አንጓላይነትን ከኢትዮጵያዊ ወገንተኛነት ጋር ለማግባባት የሚታገሉ እንዳሉ ሁሉ፣ ኢብሔርተኛ ነኝ በሚል አቋማቸው ውስጥ ሥውር ብሔርተኝነትም ተሸሽጎ የሚጎስማቸውም አሉ፡፡ ከእነአካቴው ብሔርተኝነታቸው ከኢትዮጵያዊነት ጋር አልኳኋን ያላቸውንም እናገኛለን፡፡ በኢትዮጵያ ግቢ ውስጥ የሚላወስ ብሔርተኛ እንጓላይነትና ከኢትዮጵያዊነት ጋር አልግባባ ያለ ብሔርተኛነት እንቆቅልሻዊ አቋም ሲያራምዱም እናስተውላለን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው የመሬትን (የአካባቢን) ባለቤትነት ከብሔር ጋር አዛምደው፣ ‹‹ባለቤት›› ካሉት ብሔር ውጪ የሆነን በባይተዋርነት ማንጓለልን ተገቢ አድርገው የያዙ ሰዎች፣ በሌላ ጎን ፈረንጅ አገር ለመሄድና ዜግነት አግኝቶ ከአገሬው ሰው እኩል (በዜግነት የሚገኝ) መብትን ለመቃመስ ይጓጓሉ፡፡ በአውሮፓና በአሜሪካ ውስጥ የዜግነት መብት ጨብጠው በእኩል ዜግነት ቤት ገዝተው ሀብት አፍርተው ያሉ ብሔርተኞች፣ እነሱ በሌላ አገር ያገኙትን የእኩል መብት ኢትዮጵያውያን በአገራቸው እንዳያገኙት ይበጠብጣሉ፡፡
አሁን እየበረታ በመጣው የአገር ፍቅር ውስጥም፣ የሆነ የሥምረት ውልቃት እናገኛለን፡፡ የ1960ዎች ትውልድ ተደቁሶ በሕጋዊ መንገድም ሆነ በሕገወጥ መንገድ ወደ ውጪ መሰደድ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዛሬ ድረስ አገር ቤት ውስጥ ባሉ ወጣቶች አካባቢም ሆነ፣ በውጭ አገር ውስጥ በትምህርትና በሥራ ገበታ ላይ ባሉ የአገር ልጆች ዘንድ፣ አገራችንን ኢትዮጵያን እንወዳለን ባይነት በአያሌው አለ፡፡ ነገር ግን፣ ‹‹የውጭ ዜግነት አልፈልገም…፣ ትምህርቴን ጨርሼና ጥቂት የሙያ ብስለትና ዶላር ቋጥሬ አገሬ መግባት ነው የምፈልገው›› የሚል ሰው እመሀላቸው ቢገባ፣ የሰውየውን አቋም ከ‹‹ዞረበት አገር ወዳድነት›› ወይም ከጤና ማጣት የሚቆጥሩት ጥቂት አይደሉም፡፡
እዚህ ሁሉ ትችት ውስጥ የገባሁት እኔ ራሴ በሰብዕና ሥምረት መፋለስ ውስጥ ነኝ፡፡ አስተሳሰቤ እንደ ዕድሜ ጎልምሷል፣ ስሜቴ ከመስከንም በላይ ሰክኗል፡፡ ይህንን ቅዝቃዜ ይዤ ትናንት የነበርኩበትን የራሴን ጮርቃ የሕዝብ ፍቅርና ለሕዝብ ዓላማ ራስን የመስጠት ቁርጠኝነት ቁልቁል ለማየት ግን አቅም የለኝም፡፡ ከ1960ዎች የትግል ልምዴ አንስቶ እስካሁን በተጓዝኩባቸው የሃምሳ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ለኢትዮጵያ ፖለቲካና ለኢትዮጵያ ኑሮ መሻሻል ምን አስተጽኦ አደረግሁ ብዬ ስጠይቅ ሁለመናዬን የሚያጠምቀኝ ኃፍረት ነው፡፡ ‹‹እናንተ የ1960ዎች ትውልዶች ከፋም ለማም በጊዜያችሁ የአቅማችሁን አዋጣችሁ፣ እኛ ደግሞ በእናንተ አስተዋፅኦ ላይ እያከልንና የጠመመውን እያቀናን፣ በግማሽ ምዕት ዓመት ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያን እዚህ ዕርከን ላይ አደረስን›› ብሎ አብዮት አደባባይ ላይ ለመናገር የሚደፍር አንድም ሰው ወይም ቡድን ያለ አይመስለኝም፡፡
የኢትዮጵያ የ50 ዓመታት ጉዞ በመዳፋት፣ በእንዘጭ እምቦጭ፣ በደንበር ገተር ሁሉ የተሞላ ዕርምጃ ነው፡፡ ፖለቲካችንና ልሂቅነታችን በተፋልሶዎች፣ በዳር ተመልካችነትና በሌላው ላይ ጣትን በመጠቆም በመጠመዱ፣ ዓለማዊ-አካባቢያዊና አገራዊ መረጃዎችን ትኩስ በትኩስ እያሰባሰቡና ፈርጆች እያሲያዙ የመመርመርና የማንጠር፣ በውጤቱም የፖለቲካችንን ግንዛቤና አካሄድ የማቃናት የኅብረተሰብን አመለካከት የመሞረድና የማበልፀግ ሥራ አልሠራም ለማለት ይቻላል፡፡ በዚህም ምክንያት ከመከራ ልምድና ከጥፋት በመማርና በመታረም ረገድ አገራዊ ጉዟችን እጅግ ጎስቋላ ሆነ፡፡ በአዲስ ግንዛቤ ህሊናን እያለሙ፣ የከሰረውን የብሔር ፖለቲካ ድጋፍ የማራገፍ ሥራ በመጉደሉም፡-
- አናቋሪነቱና አጋዳይነቱ በዓመታት ልምድ የማይደበቅ የሆነበት ብሔርተኛነት፣ በዚህ የክስረት ደረጃውም ላይ ሆኖ እስከ ሃይማኖት አመራር ያሻቀበ አሙለጭላጭነት የመፍጠር አቅም ሲያገኝ ታየ፡፡
- ከብሔርተኛ አገልጋይነት ሙሽት ሊወጡና ወደ ኅብራዊ ፖለቲካ ሊሻገሩ ይችሉ የነበሩ ብዙ ሰዎች ብሔርተኝነት መክሰሩን ካወቁ በኋላም መላቀቅ ተስኗቸው ሁለመና ቅስቀሳውና ተግባሩ ጥላቻና በቀል ወደ ሆነ ጭፍንነት ሊያሽቆለቁሉ ቻሉ፡፡
- ያንን ያህል ርቀት ተንከባለውም ከሕዝብ ድጋፍ የሚያፈታና ኃይላቸውን በብልህ ፖለቲካ የሚበዝብዝ የፖለቲካ ሥራ በመጉደሉ ዓይናችን ሥር ግዙፍ ጦርን መደገስ ተቻላቸው፡፡
- ከብሔርተኛነት/ከጎጠኝነት የተነሳሳና ቂም በቀልን የሚያጦፍ ጦርነት ምን ያህል ጥፋትና ዕልቂት እንደሚያስከትል ከታየ በኋላም፣ ብሔርተኛ አራጅነትና አስጨፍጫፊነት ገና አልተሸማቀቁም፡፡ አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች ውሎ ያደረ አራጅነት በኩራት ቀጥሏል፡፡
- እናም የዘቀጠ ብሔርተኛነት፣ በዘቀጠ ቅጣቱ የራሱን መቀበሪያ በመማስ ፈንታ ትኩስ ብሔርተኝነትን አዋልዷል/አራብቷል፡፡ ‹‹ብሔርተኛነት አይሰለቅጠውም… የት ሄዶ ከማንም ጋር ተላምዶ ይኖራል›› ሲባልለት የነበርን የአማራ ብሔረሰብ በብሔርተኛ ጥቃት አቆራምዶ ትኩስ ብሔርተኛ ሲያደርገው አየን፡፡ አዲሱ ብሔርተኝነት በአንደበት ብቻ ሳይገደብ፣ ጨለምተኛ የፖለቲካ ሥዕል ታቅፎ ጠመንጃ ለማንጣጣት በቃ፡፡
- በዚህ አኳኋን እዚያና እዚህ የቀጠለው ሰላም የነሳ የብሔርተኛ አዙሪት፣ ከልምድ ተምሮ የብሔርተኛ ካቴናን እየበጣጠሱ የመውጣትን ዕድልና የተጀማመረ መፍጨርጨር በደንበር ገተር በወለም ዘለም እንዲጓተት እያደረገው ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ፖለቲካ በምክነቱ ለተጠቃቀሱት የተጓዳሉና ሳይከናወኑ ለቀሩ ተግባራት ተጠያቂነት አለበት፡፡ የሚያሳዝነው ደግሞ ተጠያቂነቱን ፖለቲካችን ያወቀውም አይመስልም፡፡ ብሔርተኝነትን ቁልቁል ሲያዩና ሲተቹ የነበሩ ፖለቲከኞች፣ በአሁኑ ደረጃ ላይ እንኳ፣ ይህ ሁሉ ዝርክርኮሽና ጥፋት የእኛ ድክመትና ስንፍና ውጤት ነው ወደ ማለት የዞረ ሂስ በራሳቸው ላይ ሲያደርጉ አይታዩም፡፡ አሁንም ጥፋቱን ወደ ሌላ ሲጠቁሙና ሌላውን ሲወቅሱ ነው የሚታዩት፡፡ ራስን ለመውቀስም የሚያስችል የፖለቲካ ግምገማ በአንደበታቸው አጠገብ ሽው ያለም አይመስልም፡፡ አንዳንዶቹ ቡድኖች ዘንድ ያለው የፖለቲካ ድህነት ለዚህ ዓይነት ትዝብትም የማይመች ነው፡፡ በአንዳንድ መድረኮች ላይ የአመራር አባሎቻቸው ሲናገሩት የሰማነው ነገር የኢትዮጵያን እውነታ ቅጥ አምባር ስለመረዳታቸውም የሚያጠራጥርና የሚያስደነግጥም ነው፡፡ አስደንግጦም (ለአነጋገሬ ይቅርታ ይደረግልኝና) በአሁናዊው የዓለማችንና የቀጣናችን ዓውድ አገራችን ምን ያህል ፈተና እንዳለባት ለማጤን፣ ከኢዜማው ብርሃኑ ነጋ የቅርብ ትንታኔያዊ ንግግር የቻሉትን ያህል ቢቋደሱ የሚያስብል ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡
