ጋዛን እና ግብጽን የሚያዋስነው የራፋህ ድንበር
የምስሉ መግለጫ,ጋዛን እና ግብጽን የሚያዋስነው የራፋህ ድንበር

22 ጥቅምት 2023

በግብጽ ዋና ከተማ ካይሮ በፍልስጤም ዙርያ የመከረው ጉባኤ ያለ ውጤት ተበተነ።

ጉባኤው ያለ ውጤት የተበተነው የአውሮፓ ልኡካን አረብ አገራት ሐማስን እንዲያወግዙ በመጠየቃቸው ነው።

በዚህ ጉባኤ አንድም የእስራኤል ባለሥልጣን አልታደመም።

የአውሮፓ ኅብረት እና አረብ አገራት በጉባኤው ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

የሰላም ጉባኤው የጋራ የአቋም መግለጫ ለማውጣት ስምምነት ባይደርስም ግብጽ በተናጥል የአረብ አገራትን ይሁንታ ያገኘ መግለጫ አውጥታለች።

የመግለጫው ጭብጥ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለፍልስጤማዊያን ጉዳይ ተገቢውን ትኩረት እንዳልሰጠ የሚያትት ነው።

በጉባኤው የተገኙት ሁሉም የዓረብ አገራት ፍልስጤማዊያንን በግዳጅ ለማፈናቀል የሚደረገውን ሙከራ በጽኑ አውግዘዋል።

የግብጹ አልሲሲ ፍልስጤማዊያን ራፋህ ድንበርን ተሻግረው ወደ ግብጽ እንዲፈናቀሉ የተወጠነውን ሐሳብ አገሬ በፍጹም አትፈቅደውም ብለዋል።

የአልሲሲን ሐሳብ የደገፉት የሳኡዲ ውጭ ጉዳይ ምኒስትር ፈይሰል ቢን ፈርሃን አል ሱኡድ ፍልስጤማዊያንን የማፈናቀሉ ሐሳብ ረብ የለሽ ብለውታል።

የፍልስጤሙ መሐመድ አባስ በበኩላቸው እኛ ፍልስጤማዊያን ከመሬታችን ተገፍተን እንደንፈናቀል አንሻም። ምንም ይምጣ ምን በመሬታችን ሆነን እንቀበላለን ብለዋል።

የአባስ አስተዳደር በዌስት ባንክ እንጂ በጋዛ ቁጥጥር የለውም። የጋዛ ሰርጥን የሚያስተዳድረው ሐማስ ነው።

የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ፍልስጤማዊያን ወደ ሲናይ በረሃ በግድ ለማፈናቀል መታሰቡን ወቅሰው ለችግሩ መፍትሄው እነሱን ማፈናቀል ሳይሆን ነጻ የፍልስጤም አገር መፍጠር ነው ብለዋል።

የካይሮው ጉባኤ የተጀመረው 20 የሰብአዊ እርዳታ ምግብና ቁሳቁስ የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች በራፋህ ድንበር ማለፋቸውን ተከትሎ ነበር።

የጋዛ ነዋሪዎች ሰብአዊ እርዳታ ሲቀርብላቸው ከጦርነቱ ወዲህ የትናንቱ ለመጀመርያ ጊዜ ነው።

ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በቀን ወደ ጋዛ 500 የሰብአዊ እርዳታን የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ይገቡ ነበር።

በጋዛ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ነዋሪ ሕይወቱን የሚገፋው በተባበሩት መንግሥታት በኩል በሚቀርብ የምግብ እርዳታ ነበር።

ትናንት በራፋህ ድንበር በኩል ወደ ጋዛ የገባው እርዳታ በተባበሩት መንግሥታት የሚታደል ሲሆን በትምህርት ቤቶች ለተጠለሉ ፍልስጤማዊያን ይሰጣል።

በተባበሩት መንገሥታት ትምህርት ቤቶች የተጠለሉ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ፍልስጤማዊያን ይገኛሉ።

ወደ ጋዛ ትናንት ካቀኑት ከባድ ተሽከርካሪዎች መካከል አንደኛው የሬሳ ሳጥን መጫኑን በዚያ የምትገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ ታዝባለች።

የረድኤት ተሽከርካሪዎችን መግባት ተከትሎ ባይደን እሰራኤልና ግብጽን እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታትን አመስግነዋል።

የእስራኤል መከላከያ ይህ እርዳታ ደቡባዊ ጋዛ ለሚገኙ ብቻ የሚሰጥ ይሆናል ብሏል።

ሰሜን ጋዛ የሚገኙ ፍልስጤማዊያን ጨርቄን ማቄን ሳይሉ በፍጥነት ወደ ደቡብ ጋዛ በመሸሽ ሕይወታቸውን እንዲያድኑ የእስራኤል መከላከያ በተደጋጋሚ አሳስቧል።

የእስራኤል መከላከያ በቀጣይ በሚወስደው እርምጃ ሐማስን ከምድረ ገጽ እንደሚያጠፋ ዝቷል።

ኤኤፍፒ የዜና ወኪል በስም ያልጠቀሳቸው የአረብ ዲፕሎማቶች ለጉባኤው ያለ ውጤት መበተን የአውሮፓ አገራት የአረብ መሪዎች ሐማስን በማያሻማ ሁኔታ ማውገዝ አለባቸው በማለታቸው ነው።

የአረብ ተወካዮች ይሁንታን የሰጡትና ግብጽ በተናጥል ባወጣቸው መግለጫ የዓለም መሪዎች የፍልስጤምን ችግር ማባበል እንጂ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት ፍላጎት የላቸውም የሚል ጠንካራ ወቀሳን ያቀርባል።

በሰላም ጉባኤው ጠንከር ያለ ንግግር ያደረጉት የዮርዳኖስ ንጉሥ፣ ‘በፍልስጣሚያን ዙርያ የዓለም ዝምታ ይረብሻል፤ እኛ ከዝምታው የተረዳነው ነገር ቢኖር የፍልስጤማዊያን ሕይወት ከእስራኤላዊያን ሕይወት ያነሰ ተደርጎ እንደሚወሰድ ነው’’ ብለዋል።

የዩኬ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጃምስ ክሌቨሪ ከእስራኤል ባለሥልጣናት ጋር በጦርነቱ የዓለም አቀፍ ሕግ የሚከበርበትና የንጹሐን ሕይወትን መታደግ በሚቻልበት ሁኔታ ተነጋግረናል ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ የሰብአዊ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

ሐማስ በመብረቃዊ ጥቃት 1ሺህ 400 ሰዎችን ወደ እስራኤል ኪቡትዝ ቀበሌ ገብቶ ከገደለ በኋላ እንዲሁም በበረሃ የሙዚቃ ድግስ ላይ ሰዎችን ገድሎና ሌሎችን አግቶ መውሰዱነት ተከትሎ እስራኤል እየወሰደች ባለችው ወታደራዊ ጥቃት ከ4ሺህ በላይ ፍልስጤማዊያን ተገድለዋል።

ከነዚህ ብዙዎቹ ሕጻናትና ሴቶች ናቸው።