October 22, 2023 

42ኛ ዓለም አቀፍ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ

ባለ 33 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ የመግለጫው ሙሉቃል እንደሚከተለው ነው

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ለ42ኛ ጊዜ ባደረገው መደበኛ ስብሰባው ተወያይቶ የደረሰበትን የመፍትሔ አቅጣጫና የጉባኤውን የመጨረሻ የአቋም መግለጫ ከዚህ ቀጥሎ ቀርቧል፡፡

1. በጉባኤው መጀመሪያ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ሃይማኖትን በጽናት ስለመጠበቅ፣ ኢትዮጵያዊ ማንነትንና ባህልን እንዳያደበዝዝ፣ ትውፊትና ሥነ ምግባር እንዲጸና ጠንክረን መሥራት እንዳለብን፣ ካህናትና ምእመናን እንደፈትልና ሰም ተዋሕደው መኖርና በአስተዳደራዊ ጉዳይ እየተፈተነ ያለው አንድነታችን በውይይትና በዕርቅ ስለመፍታት፣ ስለዘመናዊ አሠራርና ለሰላምና ለአንድነት ቅድሚያ ስለመስጠት የሰጡትን አባታዊ መመሪያ ጉባኤው በሙሉ ድምጽ ተቀብሎታል፤

2. በመቀጠልም ብፁዕ አቡነ አብርሃም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባሕርዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ያሳለፍነው ዓመት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እጅግ አብዝታ የተፈተነችበት፣ በፈተናውና በደረሰው መከራ ያዘነችበት፣ ቢሆንም የደረሰብን ፈተና፣ ስደት፣ ሞት፣ መፈናቀልና ልዩ ልዩ ጸዋትወ መከራ በቃላት ተገልጾ የማያልቅ ሲሆን ይህንን እያሰብን ቆዛሚዎች ሳንሆን ከፈተናው የተማርነውም እንደወርቅ ተፈትነን ነጥረን በመውጣት ለሦስት ሺህ ዘመናት ጸንታ የቆየችውንና የታሪክ ባለቤት የሆነችውን ቅድስት ቤተክርስቲያናችንና ርትዕት ሃይማኖታችንን ለትውልድ ለማስተላለፍ፣ የውስጥ አንድነታችን ማጠናከርና የሌሎች አካላት ዓላማ አስፈጻሚዎች ሆኖ አለመገኝትን አስምልከተው የሰጡትን አባታዊ መመሪያ ጉባኤው በሙሉ ድምጽ ተቀብሎታል፤

3. በተጨማሪም ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በአገራችን ኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖት ጠል ሰዎች እየተበራከቱ መምጣት፣ በቤተ ክርስቲያን ያላቸውን ጥላቻ ማንንም ሳይፈሩ በሚዲያዎቻቸው ማወጅ፣ የላካቸው ወይም በርቱ ባይ ያለ እስኪመስል ድረስ ያለስሟ ስም ያለታሪኳ ታሪክ የሚለጥፉና ተባባሪዎቻቸው የሚፈጽትን አደገኛና መርዘኛ አካሄድ ተረድተን ሲኖዶሳዊ መዋቅራችንንና አንድነታችንን አጠናክረን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መጠበቅና ለትውልድ ማሻገር ውዴታችን ሳይሆን ግዴታችን መሆኑን አምነን እና ተቀብለን ለመፈጸም፣ ለተግባራዊነቱም ሙሉ ኃላፊነቱን ለመውሰድ ቃል እንገባለን፤

4. ብፁዕ ሥራ አስኪያጁ እስከ አሁን የመጣንበትንም መንገድ ስንመረምር ስለበጎ ነገር ተናግረን ከሠራነው ይልቅ ያልሠራነው መብለጡ፣ በቃልም በግብርም ተግተን ባለማስተማራችን መሆኑን በመግለጽ ከገባንበት ችግርና መከራ ልንወጣ የምንችለውም በስክነት በመወያየት በመሆኑ፤ እየተመካከሩ ይሠሩ የነበሩ አባቶቻችን አርኣያ በማድረግ፤ በፈተና ወጀብ ውስጥ እያለፉም ቢሆን ዘመን ተሻጋሪ ሥራ በመሥራት ስለሆነ የዓለም ሥልጣኔ ጫፍ ላይ በደረሰበት ዘመን የምንገኝ በየደረጃው ኃላፊነት ያለብን አገልጋዮች ዓለምን እየቃኘን በመሥራት ፈታኞች ሳንሆን የፈተናዋ መድኃኒቶች ለመሆንና ለቤተ ክርስቲያችን ሁለንተናዊ ማንነቷ ቅድሚያ ሰጥተን ለመሥራትና ለማስፈጸም ቃል እንገባለን፤

5. በሀገራችን ኢትዮጵያ በአራቱም ማዕዘን በገጠማት የእርስ በርስ ጦርነትና የሰላም እጦት ምክንያት የቤተ ክርስቲያናችን ህልውናና የዜጎች በሰላም ወጥቶ የመግባት ጉዳይ ከስጋትም አልፎ አደጋ ላይ መውደቁና በየዕለቱ ሞት ማስከተሉ ዓለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ በመሆኑም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የሕይወት መገኛ የሰላም ምንጭ እንደመሆኗ መጠን ቅዱስ ሲኖዶስ ሰለሀገራችን፣ ስለቤተ ክርስቲያናችንና ስለ ዜጎች ሰላም በአጽንኦት መክሮና ዘክሮ ከሚመለከተው ባለድርሻ አካል ጋር ጠንካራ ውይይትና ምክክር በማድረግ ለሰላም ያላትን ሚና በግልፅ እንዲታወቅ ይደረግ ዘንድ ጉባኤው አበክሮ ያሳስባል፡፡

6. “ወኩን መሃይምነ እስከ ለሞት” “እስከ ሞት ድረስ የታመንክ ሁን” ተብሎ እንደተጻፈው ስለቤተ ክርስቲያናቸው ደማቸውን ያፈሰሱ አካላቸው ያጎደሉና በሰማዕትነት የሞት ዋጋ የከፈሉ ኦርቶዶክሳውን በጣም ብዙ እንደሆኑ፤ የተፈጸመው ድርጊትም ከኢትዮጵያዊነት ሥነ ምግባር አንጻር ከባድ ጭካኔ የተመላበት እጅግ አሳዛኝና ዘግናኝ ድርጊት መሆኑን ከየአህጉረ ስብከቱ ከቀረበው ሪፖርት መረዳት ተችሏል፡፡ በመሆኑም ስለ ሃይማኖታቸውና ስለ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው እስከሞት ድረስ ዋጋ ለከፈሉ አገልጋዮችና ምእመናን በሰማዕትነት በየዓመቱ በዚህ ዐቢይ ጉባኤ “የዝክረ ሰማእትነትን ቀን” ተብሎ እንዲታሰቡ ለትወልድ የሚዘከሩበት ሐውልተ ስመዕ እንዲቆምላቸው በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ያገኝ ዘንድ ጉባኤው በአንድ ድምጽ ያሳስባል፡፡

7. ባሳለፈንው ዓመት በተፈጠረው ወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ችግር በተለይም ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን፣ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅና ብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊ ከመላው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመሆን ሊቃውትን፣ ማኅረ ካህናትና ምእመናንን በተሎጽ፣ በምኅላ፣በትምሀርተ ወንጌልና በአባታዊ መመሪያ በአንድነት በማስተባበር፣ ባለሙያዎችን በማሳተፍ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት፣ ልዕልና፣ ሕልውና መብትና ጥቅም እንደጠበቅ የተደረገው በታሪክ የሚዘከር ታላቅ መንፈሳዊ ተጋድሎ አርአያነት ያለው ነው፤ ይሕ መንፈሳዊ ተጋደሎ ለወደፊቱም ተጠናክሮ እንዲቀጥል እኛም እንደቀድሞው ሁሉ የአባቶቻችንን ትእዛዝ ለማስፈጸም ቃል እንገባለን፤

8. ለዘለዓለማዊ ክብር የሚያበቃውን መልካሙን ገድል ለመፈጸም የታመኑ አገልጋችና የቤተ ክርስቲያን ልጆች ለማብዛት የዓለማው በጽናት ማስተማርና ከፊት መቅደም የእኛ የመንጋው ጠባቂዎች ተቀዳሚ ተግባር ስለሆነ በጥቂት ዓላማቢሶች በተፈጸመው አሳፋሪና ጸያፍ ግብር ተሸርሽሮ የተሰበረው የምእመናን ልብ በመንፈሳዊና ጥበብ ደግሞ በመጠገን ለሃይማኖቱና ለቤተ ክርስቲያኑ “ዐምዳ ወድዳ” ሁኖ የሚቆም ትውልድን ማብዛት በእጅጉ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ መሠረት ዘመንና ጊዜ በፈጠረው ከንቱና ርብ በሌለው የተባረዘውን ትውልድ ከሁሉ ለሚበልጥ ቅዱስ ዓላማ በመንፈሳዊ ሕብረት ጸንተው እንዲቆሙ የሚያስችል ሐዋርያዊ ሥራ አስፈላጊ በመሆኑ ከማዕከል እስከ ጠረፏ ቤተ ክርስቲያን በወጥነት በጥናት የተደገፈ ሐዋርያዊ ተልዕኮና ልዩ ሥምሪት መከናወን እንዳለበት ጉባኤው ያምናል፡፡ ስለሆነም ቅዱስ ሲኖዶስ የሃሳቡን ጠቃሚነት መርምሮ መፍትሔ ይሰጥበት ዘንድ ጉባኤ በአክብሮት ይጠይቃል፡፡

9. በየአህጉረ ስብከቱ በወቅታዊ ጉዳይ ከእምነት ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ማንኛውንም ችግር ለመፍታት ከመንግሥት ጋር በመነጋገር ዘላቂ መፍትሔ የሚያስገኝ የዲፕሎማሲ ሥራ እንዲሠራ ጉባኤው በአንድ ልብ በመስማማት ይጠይቃል፡፡ እኛም በየድርሻችን የሚጠበቅንንም ለመፈጸም ቃል እንገባለን፡፡

10. ያለቀኖና በሢመተ ጵጵስና የተፈጸመው የቀኖና ጥሰት የቤተ ክርስቲያን ክብረ ልዕልና የተዳፈረ ከመሆኑም በላይ የካህናትንና የምእመናን አንድነት የከፋፈለ በጸጋ እግዚአብሔር የከበሩ አባቶቻችን የኖላዊነቱን ቀንበር ለመሸከም ፈልገው ሳይሆን ተፈልገው፣ ጠይቀው ሳይሆን ተጠይቀው፣ አስገድደው ሳይሆን ተገደው፣ የሚገቡትን ኃላፊነት ለክብረ ሥጋና ለምድራዊ ፍላጎት ታስቦ የተፈጸመ ሲመተ ጵጵስናው ችግሩ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን የተፈታ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ እንደተጠበቀ ሆኖ በድጋሜ በትግራይ የተፈጸመውም ኢ-ቀኖናዊ ሢመት፣ በእናት ቤተ ክርስቲያን ቀኖናዊ ሥርዓት መሠረት የመጨረሻ ዘላቂ መፍትሔ በቅዱስ ሲኖዶስ ቢሰጠውም አፈጻጸሙ ውጤታማ ሆኖ ወደ ቀደመ አንድነታችን እንድንመሰል እንዲደረግ ጉባኤው በአጽንዖት ይጠይቃል፤

11. ከላይ በተጠቀሰው በሀገራችን እና በቤተ ክርስቲያናችን ዙሪያ በደረሰው ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ችግር ምክንያት ቤተ ክርስቲያን ለገጠማት ወቅታዊ መከራና ችግር የተደረገውና እየተደረገ ያለው ድጋፍ እንዲቀጥል ጉባኤው ያሳስባል፤

12. ሰብከተ ወንጌል የቤተ ክርስቲያናችን ዓቢይ ተልእኮ በመሆኑ በሀገር ውስጥና በባላት ሐዋርያዊ የተልእኮ ጸጋ፣ የዘመናት መሠረት በማድረግ በውጭ አህጉር ቋንቋዎች የመስጠቱ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ በተለይም ስብከተ ወንጌልን ለሰላምና ለአንድነት፣ ለቤተ ክርስቲያን ሕልውና፣ መብትና ልዕልና በተገቢው መንገድ እንዲሰጥ፣ የምእመናን ቁጥር እንዲበዛ፣ ያሉት አንዲጸኑ ተገቢው ስልትና ማስፈጸሚያ እንዲኖር፣ ለሰባክያን ተገቢው ሥልጠናና ድጎማ እንዲደረግ ጉባኤው በአጽንዖት ይጠይቃል፤

13. ለሚዲያና ለሕዝብ ግንኙነት ሥራ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እሰከ አሁን ከተደረጉት ጥረቶች የበለጥ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ በየአህጉረ ሰብከቱ ተገቢው ትኩረት ተስጥቶት እንዲሠራ እኛም በያለነበት ሥራ ኃላፊነት በዚህ ዘመናዊ ኃይል ተብሎ በሚጠራው ዘርፍ፣ በማኅበራዊ ሚዲያና በዋና ዋና ሚዲያያዎች ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በጉልህ በመግለጽ፣ ጥቃቶችን በማጋለጥ፣ ሰፊ ትሥሥር ለመሥራት ቃል እንገባለን

14. ከቀረቡ ሪፖርቶች እንደታየው በርካታ ኦርቶዶክሳውያን ሥልጣነ ክህነት በድቁና፣ በቅስና መዐርገ በየደረጃው እንደተሰጡ ታውቋል ይሁን እንጀ ለዚህ ምሥጢረ ቤተ ክርስቲያን ልዩ ትኩረት በመስጠት በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና መሠረት ከብዛት ይልቅ ጥራት ላይ አንዲተኮር አጥብቆ በመሥራት ክብረ ክህነት እንዲጠበቅ ጉባኤው በጥብቅ ያሳስባል፤

15. በልማቱ መስክ በብዙ አህጉረ ሰብከት እንደተገለጸው ለቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ ተልእኮ፣ ለአግላጋይ ካህናት፣ ለአብነት ትምሀርት ቤቶች፣ ለገዳማትና የቤተ ክርስቲያንን ገቢ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የተጠናና በዘመኑ የታገዘ ሥራ እንዲሠራ እኛም በኩላችንን ኃፊነት ለመወጣት ቃል እየገባን ለልማት ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጠ ጉባኤው ያሳስባል፤

16. የልማትና የይዞታ ማስፋፋት፣ ይዞታን የማስከበር፣ ለነባር ይዞታዎች ሕጋዊ ማረጋገጫ ማግኝት አዳዲስ የልማትና የመንፈሳዊ አግልግሎት መስጫ ቦታዎች ለማግኝት እየተደረገ ያለውን ጥረት ጉባኤው አድንቆ ለተግባራዊነቱ የሚጠበቀውን ሁሉ ለማድረግ ጉባኤው ቃል ይገባል፤

17. ገዳማትንና ገዳማዊ ሕይወትን ለማጠናከር የተደገሩ ጥረቶችን ጉባኤው ያደንቃል፣ በተለይም የቅዱን መፍለቂያ፣ የመንፈሳዊ ሕየወት ምሰሶ፣ በቁሳዊ አስተሳሰብ ለሚጠፋው ዓለም መንፈሳዊ ፈውስ የሚመነጫባቸውን ገዳማት ከሀገር ውስጥ አልፎ በውጭው ዓለም ለማዳረስ በአውሮፓና በአሜሪካ፣ በላቲንና በአረቡ ዓለም የሚደረገውን ጥረት ጉባኤው በሙሉ ድምጽ በመደገፍ ሁሉም የሚጠበቅበትን ለመወጣት ቃል ይገባል፡፡

18. አብነት ትምህርትን ቤቶችን የማጠናከርና አዳዲስ አብነት ት/ቤቶችን የማደራጀት ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጉባኤው በማሳሰብ በተለይ በአዲስ መልክ የሚቋቋሙ ኮሌጆችና በሥልትና በጥናት እንዲደራጁ፣ በመንፈሳዊ ዕውቀት፣ በማኅበራዊ አገልግሎት፣ በአስተዳደር፣ በሂሳብ፣ በሕግ፣ በልማት፣ በጤና እና በሌሎች ቤተ ክርስቲያን በምትፈልጋቸው የሙያ ዘርፎች የሚያሰጥባቸው ሆነው እንዲቋቋሙ፣ ነባር የአብነት ትምህርት ቤቶችን መሠረት አድርገው እንዲቋቋሙ፣ ለተግባራዊነቱም የሚጠበቅብንን ለማድረግ ቃል እንገባከን፤

19. በገንዘብ (ፋይናንስ)፣ እና በንብረት አያያዝና አጠቃቀም፣ በቁጥጥር ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ መሥራት የቤተ ክርስያንን ሁለንተናዊ ተልእኮ በሚገባው መጠንነ እንዲያድግ ዋናው አስተዋጽኦ በመሆኑ ይሕንን ዘርፍ በዘመናዊ አሠራር፣ የሙያና የአመራር ብቃት በተገቢው ሥልትና መመሪያ፣ በወጥነት ተግባራዊ ማድረግ ከሁሉም በላቀ ትኩረት እንዲሰጠው ጉባአው እያሳሰብ በዚህ መስክ ቅዱስ ሲኖዶስ ተገቢውን ውሳኔ ቢሰጥበት እኛ በተግባር ለመፈጸም ቃል እንገባለን፡፡

20. የወጣቶችን የሰንበት ተምሀርት ቤት መስፋፋት በተለይም በማደራጃ መምሪያ በኩል ተዘጋጅቶ ወደ እንቅሰቃሴ እየገባ በሚገኘው የሰ/ት/ቤቶች ሥርዓተ ትምህርት ዙሪያ ለአጠቃላይ ዓለም አቀፍ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተሳታፊዎች የቀረበው ማብራሪያ እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅና መመሪያ ጉባኤው በሙሉ ድምጽ ተቀብሎ፤ ሥርዓተ ትምህርቱ ተግባራዊ እንዲሆን የቀረበው ጥሪ ተቀብለን ለተግባራዊነቱ የበኩላችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን፡፡ ከዚሁ ጋር ወደፊት የሚቀርቡት ማስተማሪያዎች የወጣቱን ሥነ ምግባር ያማከለ ከቁማርና ከሱስነ የሚጠበቅ እንዲሆን ጉባኤው በጥብቅ ያሳስባል፡፡

21. የቤተ ክርስቲያንንን ዓለም አቀፍ ተደራሽነት የበለጠ ለማጠናከር፣ በውጭ በዝርወት ያሉ ምእመናንን በመንፈሳዊ ሕይወት እንዲበረቱ ለማድረግ፣ የውጭ አህጉረ ሰብከት እያደረጉ ያለው ጥረት በእጅጉ የሚስደነቅ ነው ስለዚህ ለውጭው ዓለም አገልግሎት ትኩረት ተሰጥቶ መተዳደሪያ ደንቡ ጸድቆ አገልግሎቱ በተገቢው መንገድ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጉባኤው ጥሪውን ያቀርባል፡፡

22. በውጭ አህጉረ ሰብከት በሀገራችን የሚደርሰውን መከራና ስደት ለመላው ዓለም በማስተጋባት የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔን በየቋንው በመተርጎም ዓለም እንዲያውቀው በማድረግ፣ ሰልፍ በመውጣት የተደገውን ሁሉ ጉባኤው ከልብ በማመስገን ለወደፊቱም ተጠናክሮ አንዲቀጥል ጉባኤው በጥብቅ ያሳስባል፡፡

23. የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በተግባር እንዲፈጸም አስፈጻሚ አደረጃጀቱን በሚገባ የማጠናከር ሥራ በተለይም ዋና ዋና የአስተዳደር ማእከላት ሆኑ ጠቅላይ ቤተ ክህነትና አህጉረ ሰብከት እንዲሁም በየደረጃው ያሉበመንፈሳወውያን ተቋማት ሁሉም በሚገባ እንዲጠናከሩ ጉባኤው በአጽንዖት ያሳስባል፤

24. በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ከ90 ቨበመቶ በላይ ኦርቶዶከስውያን በሚገኙበት ሕይወትን እያጠፋ፣ ቅርስን እያወደመ፣ አገልግሎትን እያደናቀፈ ያለ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን ተግባራዊ የሆነ ድምጽ እንድታሰማ ጉባኤው በጥብቅ ያሳስባል፤

25. የቤተ ክርስቲያንን ታሪክና የአስተዋጽ በሚገባ በመጻፍና በማደራጀት ትውልድ እንዲረዳውና ሐሰተኛ ትርክቶችን መሻር አለብን፤ የቤተ ክርስቲያንን ሕጋዊ፣ ተቋማዊ፣ ሃይማኖታዊ ማኅበራዊ መብት ማስከበር፣ የሃይማኖት ነፃነትን ማስጠበቅ፣ ሥራ እንዲሠራ ከሕግ ባለሙያዎች ጋር በመሆን እንዲሠራ ጉባኤው በጥብቅ ያሳስባል፤

26. በእናት ቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ዋናኛ ችግር አባባሽና አጋፋሪ በመሆን በሐሰት አስመሳይ ደጋፊ በመሆን እያፋፉሙ ያሉ አጽራረ ቤተ ክርስቲያንን ማጋለጥ፣ በሕግ መፋረድ፣ እንዲታወቁ ዘመቻ ማድረግ ለዚህም ከሕግ ባለሙያዎች ጋር በመሆን በጥብቅ ሥራ እንዲሠራ ጉባኤው በጥንቅ ያሳስባል፤

27. አንዳችን ለአንዳችን በአንድነት ድምጽ መሆን በአንዱ ሀገረ ሰብከት ችግር ሲፈጠር ሌላውን እኩል መጮኽ፣ ሁሉም ለሁሉም ድምጽ መሆን ለሚመለከተው አካል ያለማቋረጥ መጮኽ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ በሀገር ውስጥ ሳንወሰን፣ ችግራችንን ለመላው ዓለም መስረዳት መቻል፤ ጠላቶቻችን መቼም ዝም አይሉምና፣ ዘዴና አካሔድ ይቀይራሉ አንጅ ጥቃታቸውን አያቆሙምና ለዚህ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንዲሠራ ጉባኤው ይጠይቃል፤

28. በዋናው ማእከል፣ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሚሰጡ መመሪያዎች፣ ደንቦች ውሳኔዎች እና ል ልዩ ትእዛዞች እስከ ታች ድረስ በማውረድ ለማስፈጸም ሁላችንም ቃል በመግባት ይኽ የተናበብና የተሰናሰለ አሠራር እንዲኖር የበኩላችንን ለመወጣት ቃል እንገባለን፤

29. ብፁዕ አቡነ ሙሴ የምዕራብ አውስትራልያ ሀገረ ሰብከት ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ሲኖዶስ አባል በሚመሩት ሀገረ ሰብከት ፓለቲከኞች እና የጎሣ ሐሳብ አራማጆች፣ ከክርስያን በማይጠበቅ የከፋ የጥላቸ ስበከት ቤተ ክርስቲያንን የብጥብጥና የክፍፍል ማእከል አድርገው እንደከፈሏት፣ ቦርድ በማቋቋም እየበጠበጧትን እንሆነ በሪፖርታቸው አጠንክረው ገልፀዋል፤ በዚህም ጉባኤው ብፁዕነታቸውን ያመሰግናል፤ በሌሎችም ክፍላተ ዓለም ይኽው የመከፋፈል ምንፈስ እነዳለ ይተመናል ስለዚህ ቅዱስ ሲኖዶስ በዚህ ጉዳይ ላይ አሐቲ ቤተ ክርስቲያንን ለመክፈልና የፒለቲካ መድረክ ለማድረግ በቤተ ክርስቲያን ስም ለሚንቀሳቀሱት ሀይሎች ላይ ይሰጥበት ዘንድ በጥብቅ እንጠይቃለን፡፡

30. በራያ አካባቢ የቤተ ክህነት ወረዳዎች በታሪክ፣ በቀኖና፣ በአስተዳደርና በትውፊት የማይታወቅ “መንበረ ሰላማ” የሚል ማደናገሪያ ፈጥረው በቡድን ተደራጅተው ምእመናን ሲያዉኩ የነበሩ አካላት በፈተሩት ችግር ካህናትና ምእመናንን የቤተ ክርስያንን አንድነት ለማስጠበቅ ያደረጉትን ጥረት እያደነቅን ጉዳዩ በቅዱስ ሲኖዶስ ተጨማሪ ድጋፍ እንዲያገኙ እናሳስባለን፡፡

31. ጠባብ ብሔርተኝነትና ጎሠኝነትን በተግባር በመቃወም፣ ድክመትን ማረም፣ አብሮ የመሥራት ልምድን ማዳበር፣ ለሰላምን ለአንድነት ትኩረት ሰጥቶ መሥራት፣ ጥላቻን በማራቅና የቤተ ክርስቲያንን ክብርና ልዕልና ለመጠበቅ የሚገባንን ሁሉ ለመወጣት ቃል በመግባት፡፡

32. የሕገ ተፈጥሮና የሕግ ሁሉ ፍጻሜ በሆነው በቅዱስ መጽሐፍ አጥቆ የተከለከውና ከጥንት ጀምሮ በዓለም ላይ ለፍጥረታት ጥፋት ምክንያት የሆነው ርዕሰ ኃጣውእ ግብረ ሰዶማዊነት ኃጢአት ከወሬ መጽሐፍና ከድምጸ ዜና አልፎ በዓለማችንና በሀገራችን በከፍተኛ ደረጃ ያለከልካይ በየአደባባዩ ገሀድ ሆኖ ትውልድል የማጥፋ ሴራ በስፋት፣ እየተሠራበት እንደሆነ ማንኛውም ኢትዮያዊ፣ የሚውቀው ሐቅ ስለሆነ ይኽንን ዐቢይ ጉዳይ አጥብቆ ያወግዛል፤ ጉዳዩ በቅዱስ ሲኖዶስም ጠንካራ ውሳኔ እንዲያስተልለፍበት ጉባኤው በጥብቅ እናወግዛለን፣ ቅዱስ ሶኖዶስም ውሳኔ እንዲያሳርፍበት፤

33. ከብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ጀምሮ፣ ከተሰሙት ሪፖርቶች፣ በውይይት ከተገኘው ሐሳብ እንደተገነዘብነው በአሁኑ ጊዜ ለተፈጠሩ ችግሮች ሁሉም የድራሽውን መውድ እንዳለበት፣ ወደራሳችንና ወደልባችን ተመለስን በፈጣሪያችን ታዘን ያልፈጸምነው እንደሚበዛ፣ ከሠራነው ያላሠራነው እንደሚበልጥ፣ ለድክመታችን ተጠያቂዎቹ ራሳችን መሆናችንን እና ኃላፊነት መወሰድ እንደሚገባን አምነንበታል፤ ይሁን እንጅ ከውድቀት ለመነሣት፣ ካጠፋነው ጥፋት ለመዳን፣ ያልሠራነው ለመሥራት ሁነኛው መፍትሔ ንሥሓ በመሆኑ ሁላችንም በአባቶቻችን ትእዛዝና መመሪያ ንሥሓ ገብተን ተልእኮአችንን ለመፈጸም ቃል እንገባለን፡፡

ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና (ማቴ 18፡20) ብሎ ለቅዱሳን ሐዋርያት የሰጠውን ቃል ኪዳን ለእኛም አቆይቶ በመካከላችን የተገኘ ሞገስነ፣ ወክብርነ፣ ቀርነ መድኀኒትነ ውእቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ከባህርይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ ከባህርይ ሕይወቱ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ የተመሰገነ ይሁን!

ልዑል እግዚአብሄር አምላካችን የአባቶቻችን አምላክ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን፣ ቅዱስ አባታችንን፣ ብፁዓን አባቶቻችንን፣ አገላጋይ ካህናትና ምእመናንን ሁሉ ይጠበቅልን

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ፣ የቅዱሳን መላእክት፣ የቅዱሳን ሰማእታት፣ ቅዱሳን አበው፣ የቅዱሳት አንስት፣ የነቢያትና ሐዋርያት ጸሎትና ቃልኪዳን፣ የአበው በረከትና ጸሎት አይለየን፡፡

ጥቅምት 10ቀን 2016 ዓ/ም

አዲስ አበባ ፡ ኢትዮጰያ

(EOTC)