October 22, 2023

አንዳንድ ጉዳዮች – መሳይ መኮንን

ከምዕራብ ጎጃም የሚሰማው አስደማሚ ነገር ነው። የአብይ ሰራዊት የደረሰበት ምት አከርካሪው እንዲሰበር አድርጎታል። ከፍኖተ ሰላም እየተንደረደረ ወደ ቋሪት የሚገባው የአብይ አህመድ ጦር ከሚሸሸው የሚማረከውና የሚሞተው ቁጥሩ ከፍተኛ ነው። በማዕከላዊና ደቡብ ጎንደርም ተመሳሳይ መረጃ ነው እየመጣ ያለው። ይህ ሰራዊት ለአብይ አህመድ የስልጣን ጥማት ሲባል በዚህ መጠን መርገፉ እጅግ ያስቆጫል። ሰውዬው እንደሆነ የትንኝ ነፍስ እንኳን ያጠፋ አይመስለውም። ሚሊዮናችን በተጨማሪነት ሊማግድ ተዘጋጅቷል። ሰሞኑን የሰራዊቱን ሞራል ይጠግናል ያለውን የመሳሪያ ትርዒት በአደባባይ ያሳያል። ከወዲሁ በአንዳንድ ተቋማት ጀምሮታል። ትርጉም የለውም። ኢሊት ብሎ አብይ ያንቆለጳጰሰው ኮማንዶ ጦሩ ወገብ ዛላው ከተመታ በኋላ ዓለም ላይ ያለውን መሳሪያ ታጥቀህ ብታዘምት ጦርነቱን አታሸንፍም። የቋሪት አርሶ አደር በክላሽ፥ ጀነራል መድፍ እየማረከ ነው። ልብ ገዝቶ ማስታጠቅ አይቻል ነገር?!

አብይ አህመድ ባህርዳር ላይ የተከለው የሞግዚት አስተዳደር የሚሰጠው መግለጫ ጥሩ ኮሜዲ ይወጣዋል። በዙ 23 ፥ በታንክና በሚሳየል ተከቦ፥ ከባህር ዳር 10 ኪሎሜትር መውጣት ያልቻለው አረጋ ከበደ የሚሉት ጉዳይ አስፈጻሚ ክልሉ ተረጋግቷል፡ ሰዓት ዕላፊውን አሻሽለናል፡ የምትል ብጣሽ መግለጫ ዛሬ ሰጥቷል። አብይ አህመድ ከህወሀቶች ከቀሰማቸው ነገሮች አንዱ ሀሞታቸው የፈሰሰ፡ በአፍቅሮተ ነዋይ አቅላቸውን የሳቱ፡ በሆድና በህሊና መሀል ድንበር የሌላቸው፡ ለመብላት የሚኖሩ፡ እጅግ ደካማ ሰዎችን በባትሪ ፈልጎ ማግኘትን ነው። እነዚህ ክብረቢስ፡ ህሊና ቢስ፡ አቅመ ቢስ፡ ሰዎች የሚወልዷቸው ልጆቻቸው ያሳዝናሉ። የአባት እዳ ለልጅ ባይተርፍ ጥሩ ነው። አሁን አማራ ክልል የትኛውን ስንዝር መሬት መቆጣጠር ተችሎ ነው እንዲህ ዓይነት ፊሽካ መንፋት የተፈለገው? የስነልቦና ግንባታ መሆኑ ነው? የካድሬ መንጋውን ለማረጋጋት ነው? እውነቷ ሩቅ አይደለችም። መግለጫ እየሰጠህ ከቢሮህ ሳትወጣ ፋኖዎች እጅ ትገባለህ። ይህ በቅርብ የምናየው እውነት ነው።

አብይ ከእዳ ወደ ምንዳ የምትል የቴሌቪዥን ቲያትር አዘጋጅቶ ተመልከቱ የሚል ማስታወቂያ እያስለፈፈ ነው። ከህዝብ ጋር የተጋባው እልህ ብስለት ማጣቱን ጨምሮበታል። የዚህ ሰው ወሬ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የበረከተውን የሀሰተኛ ነቢያቶችን አስደንጋጭ የሃይማኖት መድረኮችን የሚያስንቅ ነው። አንዷ ሰሞኑን ነቢይ ነኝ ብሎ ለሚቀፍል ጎረምሳ ምን እንደምትፈልግ ስትነግረው ”አውሮፕላን” ስትለው ነበር። ነቢይ የተባለው ቀፋይ ሰሞኑን አውሮፕላኑ ከእጅሽ ይገባል ይላታል፥ እልልታውና ጩኸቱ ከአደራሹ ይደምቃል። ማህበራዊ ሚዲያ ላይ በሚለቀቁ ቪዲዮች መሰል መጃጃሎችን ብዙ አያቻለሁ። የሰውነቱን ያደፈ ላብ በሶፍት ጠርጎ ተቀባውና ትፈወሳለህ የሚልም ጀብራሬ ተመልክቼአለሁ። የባንክ ደብተራችሁን አምጡ ብሎ በየአካውንታቸው በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ በአስማት አስገብቼአለሁ ብሎ ምዕመኑን ያሳበደና ያስጨፈረ ሀሰተኛ ነቢይ አንድ ወቅት መነጋገሪያ እንደነበረ አስታውሳለሁ። ያበዱትና የዘለሉት ባንካቸው ሲሄዱ ቤሳ ቤስቲን የለም። አብይ አህመድ የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የሚጫወተው ይሄንኑ ነው። እንደ አብይ ሀሰተኛ ነብይ የለም። እዳ፥ ምንዳ፡ እያለ ቅብጥርጥር ያለ ባዶ ዲስኩር ያንበለብላል። የልጅ ነገር፡ ሀገር በቲኔጀር እጅ ወድቃ ጉዷ ፈላ?!

ግርማ ሰይፉ የተባለ በኢዜማ የብልጽግና ፓርቲ ተጠሪ ሰሞኑን ሪፖርተር ላይ እሪ እምቧ ሲል ሰማሁት። ባርነትን ሲያሽሞነሙነው አይኑ እንኳን አይርገበገብም። ስለፓርቲ ምንነት፡ ስለፖለቲካ እናትና አባቱ ማንነት፡ ኢዜማ ከራስ ጠጉሩ እስከ እግር ጥፍሩ እንዴት ፈጣሪ ተጨንቆና ተጠቦ እንደሰራው ሲናገር ትንሽ ማፈር እንኳን አይታይበትም። የኢንቨስትመንት ኮሚሽነር መሆን ለሱ የዓለም መጨረሻ ነው። ተመችቶታል። የኢትዮጵያ ህዝብ አፈር ደቼ ቢግጥ ለሱ ምኑም አይደለም። በየዓመቱ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚያቀርበውን የጽህፈት መሳሪያዎች የሚነጥቀው ሌላ አካል እስካልመጣ ድረስ አብይ የሚሉት ሰው የኢትዮጵያን ህዝብ በድሮን ቢጨፈጭፍ ምንም ማለት አይደለም። ቅዳሜ ዕለት ኢሳት ቢሮ ሄዶ ለጋዜጠኞች ስልጠና ሲሰጥ እንደነበርም ሰማሁ። አበበ ቦጋለ በሚባል የብልጽግና ተወካይ የሚመራው የኢሳት ሚዲያ ሰሞኑን ለቀጠራቸው ”ጋዜጠኞች” ነው ግርማ ሰይፉ የግማሽ ቀን ስልጠና የሰጠው። ይህቺ ሀገር እኮ የጉድ ሀገር ናት። አሁን ግርማ በምን እውቀቱና ልምዱ ነው ለጋዜጠኞች ስልጠና የሚሰጠው? የጆሮአችን ግድግዳ ጠንካራ ባይሆን ኖሮ አልቀን ነበር። አይ ኢሳት?! የህዝብ አይንና ጆሮ እንዳልነበር የብርሃኑ ነጋ፡ የግርማ ሰይፉና የአበበ ቦጋለ መጋለቢያ ፈረስ ሆነህ አረፍከው?!!