የዶላሩ ፍጥጫ
መሰንበቻውን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) ከስልጣን መነሳታቸው ሲነገር ቆይቷል ። የ ዮሐንስ መነሳት እንደተሰማ – የሲንቄ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ ነዋይ መገርሳ መሾማቸው ሲነገር በኢንቨስትመንት ማህበረሰቡ ካምፕ ፌሽታ ነግሶ ነበር።
ምክንያቱም ዮሐንስ በአብዛኛው ብድር ከመስጠት ቆጠብ ብለው ቁጥጥር ላይ ያተኩራሉ – የባንኩን ኢሜጅ ለመገንባት ይሯሯጣሉ እንጂ የባንኩን የፖሊሲ ባንክነት ከለር አጥፍተውታል – የሚሉ ትችቶች ሲሰነዘሩባቸው ቆይቷልና ነው።
የ ዶ/ር ዮሐንስ መነሳት መነገር የጀመረው በዶ/ር ዮሐንስ እና በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ መሀከል መረር ያለ አለመግባባት መፈጠሩን ተከትሎ ነው ። በእርግጥም አቶ አህመድ ዶ/ር ዮሐንስን አሰናብተው አቶ ነዋይን ለመሾም እየተዘጋጁ እንደነበር ከከፍተኛ ባለስልጣናት ሰርክል የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ነገር ግን በሁለቱ ሲኒየር ሜሪት ቤዝድ ተሿሚዎች መሃከል የተነሳውን አለመግባባት ማጠንጠኛ – የውጭ ምንዛሪ እጥረት የእግር እሳት የሆነበት የአቶ አህመድ ሽዴ ገንዘብ ሚኒስቴር – ከዶ/ር ዮሐንስ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ዶላር ለመውሰድ ማቀዱ ነው ። ዶ/ር ዮሐንስ ይህንን እቅድ ባለመቀበላቸው አለመግባባቱ መጋሙን መረጃዎች ያመለክታሉ ።
አቶ አህመድ በአቋማቸው በመፅናታቸው ዶ/ር ዮሐንስ መልቀቂያ አስገብተው ሁሉ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ ።
የተነሳው ከራር አለመግባባት ያሳሰበው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ቦርድ ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ምኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወስዶታል ። ጠቅላይ ምኒስትሩ ጠልቃ በመግባት አለመግባባቱን አብርደው ሹምሽሩን ማስቀረታቸውን መረጃዎች አመልክተዋል ።
ፕሬዝዳንቱ ዶ/ር ዮሐንስ ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ጋዜጠኞች በተገኙበት በቦታቸው መኖራቸውን አረጋግጠዋል።
በመጨረሻም ዶ/ር ዮሐንስ እንዲህ አሉ – ከአራት አመት በፊት የባንኩ የተበላሸ የብድር ምጣኔ ከ40 በመቶ በላይ ደርሶ ነበር ፤ አሁን ግን ይህንን የተበላሸ የብድር መጠን ወደ 7.1 በመቶ ማውረድ ተችሏል ፤ ይህም ለልማት ባንክ ከተቀመጠው የተበላሸ ብድር ምጣኔ ጣሪያ 15 በመቶ አንፃር ሲታይ ከፍተኛ አፈጻጸም ነው በማለት ጋዜጠኞችን ፊትለፊት እያዩ ተናግረዋል።
የእንኳን ደስ ያልዎ መልካም ምኞት መግለጫ ሲቀበሉ የቆዩት አቶ ነዋይ መገርሳ በአሁኑ ሰአት ቢሯቸው ይገኛሉ ! ሁሉም ነገር ወደ ነበረበት ተመልሷል።
WZ news / ውድነህ ዘነበ
