October 23, 2023 

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥም ቢሆን በጋዜጠኞችና በመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ላይ የሚኖር ተጠያቂነት ሕጋዊ ስርዓትን የተከተለ ሊሆን ይገባል ሲል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት አሳሰበ።

ምክር ቤቱ ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ፤ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትና ጋዜጠኞች ላይ ከሕግ አግባብ ውጪ አስሮ የማቆየትና ለስርጭት የተዘጋጀ የህትመት ውጤትን የማገድ ድርጊቶች እንደተፈጸመባቸውና፤ በዚህም ሳቢያ ተቋማቱ የዕለት ተዕለት ሥራዎቻቸውን ለመስራት መቸገራቸውን” ከደረሱት ሪፖርቶች መገንዘቡን ገልጿል፡፡

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 29 ንዑስአንቀፅ4 ላይ በግልፅ እንደተመለከተው “ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች፣ ሃሳቦች፣ አመለካከቶች በነፃ መንሸራሸራቸውን ለማረጋገጥ ሲባል ፕሬስ በተቋምነቱ የአሰራር ነፃነትና የተለያዩ አመለካከቶችን ለማስተናገድ ችሎታ እንዲኖረው በሕግ ጥበቃ ይደረግለታል” እንደሚል ያስታወሰው ምክር ቤቱ፤ ቢሆንም ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በአገሪቱ ሕግ መሠረት ተመዝግበውና ፍቃድ አውጥተው የሚሰሩ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ጋዜጠኞችና የህትመት ውጤት በጸጥታ ሃይሎች ከሕግ አግባብ ውጪ መታገታቸው እንዳሳሰበው ገልጿል፡፡

እንደ አብነትም በኢትዮ ሃበሻ አሳታሚ ድርጅት በየሳምንቱ እየታተመ የሚሰራጨው ጊዮን መፅሄትና ዋና አዘጋጁ ነሃሴ 19/2015 በፖሊስ በቁጥጥር ስር ውለው ከአንድ ሳምንት በሃላ ዋና አዘጋጁ ያለ ክስ መለቀቁን በማስታወስ መፅሄቱ ከአንድ ወር ከ 15 ቀን በላይ አለመለቀቁን አንስቷል።

በተጨማሪም የትርታ ኤፍ ኤም 97.7 የፕሮግራም ዳይሬክተርም ጳጉሜ 5/2015 ከመኖሪያ ቤቱ በጸጥታ ሃይሎች ከተወሰደ በሃላ ከአንድ ወር ከ20 ቀናት በላይ ክስ እንዳልተመሰረተበትና ፍርድ ቤትም ሊቀርብ አልቻለም ሲል ገልጿል።

በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ ቁጥር 1238 አንቀጽ 85 /7 “በየጊዜው የሚወጣ ህትመት ከመሰራጨቱ በፊት በጸጥታ አካላት የሚሰጥ የእገድ ትዕዛዝ የትዕዛዙ መነሻ የሆነውን አንቀጽ ወይም አንቀጾች፣ የህትመቱን ቅፅ፣ ጽሁፉ የወጣበትን እትም መገለጽ አለበት። እገዳውም ለሥርጭት በተዘጋጁ ህትመቶች ላይ ብቻ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡” ሲል በግልጽ መደንገጉንም ምክር ቤቱ አስታውሷል።

“ሆኖም ጊዮን መጽሄት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋለበት ጊዜ አንስቶ በአዋጁ መሰረት ተመርምሮ የጋረጠው አደጋ ስለመኖሩ ያልተረጋገጠ ሲሆን፤ ለፍርድ ቤትም በ48 ሰዓት ውስጥ የቀረበ ክስ የለም፡፡” ሲል ገልጿል።

በሌላ በኩል በመገናኛ ብዙሃን አማካይነት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ወይም አካል በወንጀል ሥነ-ሥርዓት የሕግ ድንጋጌዎች መሠረት ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ በዓቃቤ ሕግ አማካኝነት ለፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለበት በመገናኛ ብዙኃን አዋጁ በግልጽ ቢደነገግም፤ የትርታ ኤፍ ኤም ጋዜጠኛ ግን ከአዋጁ ተቃራኒ በሆነ መልኩ ለሳምንታት ያለ ክስ በእስር ላይ ይገኛል።” ብሏል።

የወንጀል ድርጊቶች ከመፈጸማቸው በፊት መከላከል ተፈጽሞ ሲገኝም አፋጣኝ ፍትሐዊ እርምጃዎችን በሕግ አግባብ የመውሰድ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ የተጣለባቸው የጸጥታ አካላት፤ ጋዜጠኞችን አስሮ መረጃ መሰብሰብና አስሮ ለቀናት ክስ አለመመስረት እንዲሁም የህትመት ውጤትን ከስርጭት ማገድ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማቱ ሥራቸውን በነጻነት እንዳያከናውኑ የሚያስተጓጉል ተግባር መሆኑንም አንስቷል፡፡

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥም ቢሆን በጋዜጠኞችና በመገናኛ ብዙሃን ተቀማት ላይ የሚኖር ተጠያቂነት፤ በሕጉ አግባብ ብቻ መከናወን ይኖርበታል ብሎ እንደሚያምንም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ምክር ቤት በመግለጫው አመላክቷል፡፡

“ይህ አለመሆኑ ግን አገሪቱ በአለም አቀፍ ደረጃ ያላት ገጽታ ላይ ጥላ የሚያጠላ ሆናል፡፡” ያለው ምክር ቤቱ፤ “ላለፉት አምስት ዓመታት የፍትህ አካሉ የተለያዩ ማሻሻያዎች እየተደረጉበት ያለ ቢሆንም፤ ጋዜጠኞችንና ተቋማቱን በተመለከተ በሕጉ አግባብ ተደጋጋሚ የመብት ጥሰቶችን ለማስቀረት ያለመቻሉ ምክር ቤታችንን በእጅጉ ያሳስበዋል፡፡” ብሏል።

ችግሩ እንዲፈታም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መርማሪ ቦርድ ጉዳዩን በማሳወቅ ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡

በመሆኑም መንግሥት የወንጀል ተግባሮችን የመከላከል፣ የመመርመር እና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ የፍትሕ ሥርዓቱ በአስቸካይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌ ውስጥም ቢሆን በጋዜጠኞችና በመገናኛ ብዙሃን ተቋማቱ ላይ የሚፈጸሙ የመብት ጥስቶችን በሕጉ አግባብ ብቻ እንዲመራ በማድረግ፤ ሕገ ወጥ የወንጀል ድርጊቶችን በተቻለ ፍጥነት በማረም ሕገ መንግሥታዊ ግዴታውን እንዲወጣ ምክር ቤቱ በመግለጫው ጠይቋል፡፡