October 23, 2023 – Konjit Sitotaw

3ኛው ዙር የአባይ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር በካይሮ ተጀመረ

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት እና አለቃቀቅ ደንቦችና መመሪያዎች ዙሪያ በኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን መካከል የሚደረገው 3ኛው ዙር የሦስትዮሽ ድርድር በግብጽ መዲና ካይሮ ተጀምሯል።

በድርድሩ ባልተፈቱ የቴክኒካል እና የሕግ ማእቀፍ ጉዳዮች የተሻለ ውጤት ላይ ለመድረስ ትኩረት እንደሚያደርግ አምባሳደር ስለሺ በቀለ(ዶ/ር) በማህበራዊ ትስሰር ገፃቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በ2015 በመሪዎች ደረጃ የተፈረመው የመርሆች መግለጫ ስምምነት መሰረት ድርድሩን በፍትሃዊና ምክንያታዊ አጠቃቀም መርህ መሰረት ውጤት ላይ ለመድረስ ትሰራለችም ሲሉም አምባሳደር ስለሺ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በነሃሴ ወር 2015 ላይ የግድቡ ተደራዳሪ የቴክኒክ ባለሙያዎች በግብጽ ካይሮ ተገናኝተው የተወያዩ ሲሆን፤ ኹለተኛው ዙር የቴክኒክ ባለሙያዎች ውይይት ደግሞ በመስከረም ወር በአዲስ አበባ መካሄዱ ይታወሳል፡፡

በዚህም መሰረት በኹለተኛው ዙር ውይይት ላይ ሦስተኛው የአገራቱ ድርድር ጥቅምት ወር ላይ በግብጽ ካይሮ እንዲካሄድ ስምምነት ላይ መደረሱን ተከትሎ፤ ድርድሩ ዛሬ በግብጽ መዲና ካይሮ ተጀምሯል፡፡