
24 ጥቅምት 2023, 07:47 EAT
ከፈረቃው ውጭ የነበረ አንድ አብራሪ እሑድ ምሽት 83 ሰዎችን አሳፍሮ ሲበር የነበረ የመንገደኞች አውሮፕላን ለመከስከስ በመሞከር ተከሰሰ።
ግለሰቡ 83 ሰዎችን ለመግደል በመሞከር ክስ ቀርቦበታል።
ተጠርጣሪው በአላስካ አየር መንገድ አውሮፕላን ውስጥ ከፓይለቶቹ ጀርባ ተቀምጦ እንደነበር አየር መንገዱ ገልጧል።
የፖሊስ መዝገብ እንደሚያሳየው ተጠርጣሪው ስሙ ጆሴፍ ዴቪድ ኤመርሰን ሲሆን ዕድሜው ደግሞ 44 ነው።
80 መንገደኞች የተሳፈሩበት አውሮፕላን ከዋሺንግተን ግዛት ወደ ካሊፎርኒያ እያቀና ነበር።
ነገር ግን በረራው ወደ ፖርትላንድ ኦሬገን እንዲሆን ተደርጎ ተጠርጣሪው ያለምንም ግርግር በቁጥጥር ሥር ውሏል።
አላስካ አየር መንገድ በለቀቀው መግለጫ እንዳለው ከሥራ ፈረቃ ውጭ የነበረው አብራሪ ከፓይለቶቹ ጀርባ ተቀምጦ የነበረ ሲሆን “ሞተሩን ለማጥፋት ሞክሮ አልተሳካለትም።”
የአላስካ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር 2059 ሠራተኞች ክስተቱን ወዲያውኑ ለአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ አሳውቀዋል።
ከአየር ትራፊክ መቆጣጠሪያ ጋር በነበረው ግንኙነት አንዱ አብራሪ “አንድ ግለሰብ ሞተሩን ለማጥፋት እየሞከረ ይገኛል፤ ነገር ግን አሁን ምንም ዓይነት አደጋ እያደረሰ አይደለም” ብሎ ሲናገር ይሰማል።
“ሲመስለኝ በቁጥጥር ሥር ውሏል” የሚለው ፓይለቱ አክሎ “እንዳረፍን ወዲያውኑ ፖሊስ እንዲመጣልን እንፈልጋለን” ሲል ተሰምቷል።
በሆራይዘን ኤር የሚመራው በረራው በሥፍራው ሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ 11፡25 ተነስቶ ምሽት 1፡30 ሳን ፍራንሲስኮ ማረፍ ነበረበት።
ነገር ግን በረራው ወደ ኦሬገን እንዲያቀና የተገደደ ሲሆን ምሽት 1፡18 ተነስቶ ወደታቀደለት መዳረሻው አምርቷል።
- ፀረ – ሴማዊነት ምንድን ነው? ፀረ – ጽዮናዊነትስ?23 ጥቅምት 2023
- የጋዛን ሰፈር ወደ ፍርስራሽ ክምርነት የቀየረው ጥቃት24 ጥቅምት 2023
- በፍልስጥኤማውያን ላይ የተባባሰው የእስራኤላውያን ሰፋሪዎች ጥቃት24 ጥቅምት 2023
ከመንገደኞች መካከል አንዷ አብሪ ጋቬሎ ለኤቢሲ ኒውስ እንደተናገረችው መንገደኞች ስለተፈጠረው ነገር የሚያውቁት አልነበረም።
ነገር ግን በድንገተኛ ሕክምና ምክንያት አውሮፕላኑ ሊያርፍ መሆኑ ከመንገደኞች መስተንግዶ ክፍል መስማታቸውን ትናገራለች።
የፖርትላንድ ፖሊስ፣ ኤፍቢአይ እና የአላስካ አውሮፕላን ምርመራ ከፍተዋል።
ኤፍቢአይ ባወጣው መግለጫ ጉዳዩን መመርመር መጀመሩን ገልጦ “ከዚህ ክስተት ጋር በተያያዘ ሌላ ምንም ዓይነት ስጋት እንደሌለ ለመንገደኞች ልናስረግጥ እንወዳለን” ብሏል።
ከግድያ ሙከራ በተጨማሪ ተጠርጣሪው ኤመርሰን 83 የሰው ልጅ አደጋ ላይ የሚጥል ተግባራት በመፈፀም እንዲሁም አውሮፕላን አደጋ ላይ ለመጣል በመሞከር ተከሷል።
ባለሥልጣናት ተጠርጣሪው መች ችሎት ፊት እንደሚቀርብ ያሉት ነገር የለም።
ሰኞ ዕለት የፌዴራል አቪየሽን አስተዳደር ለአሜሪካ አየር መንገዶች በላከው መመሪያ “ክስተቱ አሁን ዓለም ላይ እየሆነ ካለው ጋር የሚያያዘው ነገር የለም” ብሏል።