የቆሰሉትን ፖሊሶች በመልካም ጤንነት ላይ ናቸው
የምስሉ መግለጫ,የቆሰሉትን ፖሊሶች በመልካም ጤንነት ላይ ናቸው

24 ጥቅምት 2023, 08:08 EAT

በአሜሪካ ቴነሲ ግዛት፣ ናሽቪል ከተማ አንድ የፖሊስ አዛዥ ልጅ፣ ፖሊሶችን አቁስሎ በፖሊሶች እየታደነ ነው።

ጆን ድሬክ ጁኒየር የተባለው ወጣት አባቱ የናሽቪል ከተማ ፖሊስ አዛዥ ናቸው።

‘’ጆን ድሬክ ጁኒየርን ያለበትን የሚያውቅ ይጠቁመን፤ ልጁ መሣሪያ የታጠቀ ሞገደኛ ነው፤ ራሳችሁን ጠብቁ’’ የሚል አደራ ለሕዝብ አስተላልፏል፤ ፖሊስ።

በመሸሽ ላይ ያለው የ38 ዓመቱ ጆን ድሬክ ጂኒየርን ያለበትን ለጠቆመ 2ሺህ 500 ዶላር ጉርሻ እንደሚሰጥም የከተማዋ ፖሊስ ቃል ገብቷል።

ጆን ድሬክ ጂኒየር ሽሽት ከመጀመሩ በፊት ሁለት የናሽቪል ከተማ ፖሊሶችን ተኩሶ ክፉኛ አቁስሏል።

ሁለቱን ፖሊሶች ያቆሰላቸው ባለፈው ቅዳሜ ከናሽቪል ወጣ ብላ በምትገኝ ላ ቨሪን በምትባል አካባቢ ነው።

ሴት ፖሊስ አሽሊ ቦሌይጃክ እና ሌላኛው ባልደረባዋ ግሪጎሪ ከርን በተተኮሰባቸው ጥይት ቆስለዋል።

ሁለቱ ፖሊሶች በቴነሲ ግዛት የፖሊስ ባልደረባ ከሆኑ ሦስት ዓመት እንኳ አልሆናቸውም።

ሁለቱ ፖሊሶቹ የተሠረቀ ተሽከርካሪ ጉዳይን ለመመርመር በአንድ መደብር ደጅ ላይ ሳሉ ነበር የተተኮሰባቸው።

ተጠርጣሪው ጆን ድሬክ
የምስሉ መግለጫ,ተጠርጣሪው ጆን ድሬክ አባቱ ፖሊስ አዛዥ ናቸው

የከተማዋ ፖሊስ አዛዥ የሆኑትና ልጃቸው እየታደነባቸው ያለው አባት ጆን ድሬክ በልጃቸው ሁኔታ እጅግ መደንገጣቸውና ማዘናቸውን ተናግረዋል።

የተጠርጣሪው አባት እንዳሉት ከልጃቸው ጋር የነበራቸው ግንኙነት ”እጅግ የተመጠነና በረዥም ጊዜ አንዴ የሚሆን” ነበር።

ልጃቸው በተደጋጋሚ በወንጀል ድርጊት የሚሳተፍና ከዚህ ቀደምም ፍርደኛ እንደነበር መስክረዋል።

በዚህ ሞገደኛ ተፈላጊ የተተኮሰባቸው ሁለት ፖሊሶች አንዷ ትከሻዋ ላይ ሁለተኛው ደግሞ ክንዱ ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

አንዷ ፖሊስ መጠነኛ እርዳታ ተደርጎላት ቅዳሜ ከሆስፒታል ወጥታለች። ሌላኛው ፖሊስ በመልካም ጤንነት ላይ ቢሆንም አሁንም በሆስፒታል ክትትል እየተደረገለት ነው።

የናሽቪል ከተማ ከንቲባ ፍሬዲ ኦኮኔል ‘ለተጠርጣሪው አባት ዋና ፖሊስ አዣዥ ዴሪክ ሐዘኔን እገልጻለሁ፤ ልጆቻችንን በመልካም ሥነ ምግባር ለማሳደግ ምንም ያህል ብንጥርም አንዳንዴ ያፈነግጣሉ፤ ለልጆች እኩይ ባሕሪና የሕይወት ምርጫ ቤተሰብ ኃላፊነት ሊወስድ አይችልም’’ በማለት ከከተማዋ ፖሊስ አዛዥ ጎን እንደሚቆሙ ይፋ አድርገዋል።

ለቆሰሉት የፖሊስ አባላትም ጤንነትን ተመኝተዋል።