የሰፋሪዎች ጥቃት እየተባባሰ ነው

24 ጥቅምት 2023, 07:10 EAT

አቤድ ዋዲ ለቀብር እየተዘጋጀ ነበር አንድ መልዕክት የደረሰው።

ምስሉ ከጓደኛው ነበር ደረሰው። በምስሉ ላይ ጭምብል ያጠለቁ ሰዎች ይታያሉ። መጥረቢያ፣ ነዳጅ እና የእንጨት መጋዝ ይዘዋል። በእብራይስጥ እና በአረብኛ ደግሞ መልዕክት ሰፍሮበታል።

“በቁስራ መንደር ላላችሁ አይጦች በሙሉ እየጠበቅናችሁ ነው። ምንም አናዝንላችሁም” ይላል ጽሑፉ።

“የበቀል ቀን ደርሷል።”

ዋዲ የቁስራ ነዋሪ ነው። መንደሯ በሰሜን ዌስት ባንክ ትገኛለች። ለናብሉስ ደግሞ ቀረብ ያለች መንደር ናት።

በዕለቱ አራት ፍልስጤማዊያን ሊቀበሩ ዝግጅት እየተደረገ ነበር። ሦስቱ የተገደሉት እስራኤላዊያን ሰፋሪዎች ከአንድ ቀን በፊት ቁስራ ገብተው በአንድ ቤተሰብ ላይ በፈጸሙት ጥቃት ነው።

በዚህ ምክንያት የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ የእስራኤል ጦር ጣልቃ ገብቶ አራተኛውን ገደለ።

በቀጣዩ ቀን የቁስራ ነዋሪዎች 30 ደቂቃ ወደሚርቀው ሆስፒታል በመሄድ አስከሬን ለመረከብ ዕቅድ ይዘዋል። ይህን ለማድረግ ግን በእስራኤል ሰፋሪዎች መንደር ማለፍ አለባቸው።

ይህ ደግሞ አይደለም አሁን ሠላም በሚባልበት ጊዜ ጭምር ግጭት የሚፈጥር ነው። የሐማስን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል ወደ ግጭት በማምራቷ ነገሮች ተባብሰዋል።

ዋዲ መልዕክቱን ካየ በኋላም መለባበሱን ቀጠለ። ሆስፒታል ማቀዝቀዣ ውስጥ ወደ ቤት መመለስ ያለባቸው አራት አስከሬኖች ተቀምጠዋል። በደረሰው ዛቻ ሊረበሽ አልፈለገም። ብዙ ብዙ ነገር ሰምቷል።

አቤድ ዋዲ
የምስሉ መግለጫ,አቤድ ዋዲ

ከጥቂት ሰዓታት በኋላ አክራሪ እስራኤላዊያን ሰፋሪዎች የቀብር ሥነ ሥርዓቱን ለመረበሽ መፈለጋቸውን ግን አላወቀም። ወንድሙ እና የወንድሙ ልጅ እንደሚገደሉም አላወቀም።

“አንድ ወይም ሁለት ቀን ብንዘገይ ምን ጥሩ ነገር ይፈጠራል?” ይላል ዋዲ ቁስራ የሚገኘው የቤተሰቦቹ ቤት ግቢ ውስጥ ቁጭ ብሎ።

“በቀጣዩ ቀንስ ሰፋሪዎቹ አካባቢውን ይለቁ ነበር?”

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰብዓዊነት ቢሮ ከሐማስ ጥቃት በኋላ በዌስት ባንክ 75 ፍልስጥኤማዊያን በእስራኤል ፖሊሶች ወይንም ሰፋሪዎች ተገድለዋል። በሰፋሪዎች የሚፈጠረው ዕለታዊ ግጭት ከሦስት ወደ ስምንት አድጓል።

በፍልስጤም የስደተኞች መጠለያ ታብያ ላይ በተሰነዘረ የአየር ጥቃት 12 ሰዎች ተገድለዋል ሲሉ የፍልስጥኤም ባለሥልጣናት ተናግረዋል። የእስራኤል ፖሊስ ደግሞ አንድ ባልደረባው መገደሉን አስታውቋል።

የተባበሩት መንግሥታት እንዳስታወቀው የተያዙት ግዛቶች “ከቁጥጥር ውጭ” ይሆናሉ የሚል “ትልቅ ስጋት” አለ።

በዌስት ባንክ የሚኖሩ ፍልስጥኤማውያን ነዋሪዎች እንደሚሉት ዓለም ትኩረቱ ሁሉ ወደ ሲሆን እስራኤላውያን ሰፋሪዎች ወደ ተለያዩ መንደሮች ገብተው ማባረር፣ አልፎ ተርፎም የፍልስጥኤም ሠላማዊ ዜጎችን እየገደሉ ነው።

ከቪዲዮ በተገኙ መረጃዎች ወይም ከዐይን እማኞች እንደተሰማው ቢያንስ ባለፉት ሦስት አጋጣሚዎች ሰፋሪዎቹ ጥቃት ለመፈጸም የወታደር ልብስ ይለብሳሉ አሊያም ከእስራኤል ጦር ጋር አብረው ይሆናሉ።

ጭምብል ለብሰው በቁስራ ነዋሪዎች ላይ ሲተኩሱ
የምስሉ መግለጫ,ጭምብል ለብሰው በቁስራ ነዋሪዎች ላይ ሲተኩሱ

በቁስራ የሞቱት ሦስት ሰዎች ከመንደሩ ወጣ ብሎ በሚገኝ ቤት ውስጥ ያሉ የአንድ ቤተሰብ አባላት ላይ የደረሰባቸውን የሰፋሪዎች ድንጋይ ውርወራ ለመከላከል በሄዱበት መገደላቸውን በርካታ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሰፋሪዎቹ ሊከላከሏቸው በመጡ የፍልስጥኤማውያን ላይ ተኩስ ከፍተው ሦስቱን ገደሉ። ሃሰን አቡ ሶሩር (ዕድሜ 16)፣ ኦባይዳ አቡ ሶሩር (ዕድሜ 17) እና ሙሳብ አቡ ረዳ (ዕድሜ 25) ሲገደሉ በርካቶችን አቆሰሉ። የ21 ዓመቱ ሞአዝ ኦዴህ ደግሞ በኋላ ላይ ከወታደሮች ጋር በተፈጠረ ግጭት ተገድሏል።

ከቆሰሉት መካከል በቤቱ ይኖሩ የነበሩ አባት እና የስድስት ዓመት ሴት ልጃቸው ናት። አባት ፊታቸውን ልጅ ደግሞ ሆዷ ላይ በጥይት ተመትተው እንደነበር በአካባቢው በሚገኝ ክሊኒክ የሚሠሩ ሁለት ሰዎች ተናግረዋል።

በክሊኒኩ ከሚሠራው አሚር ኦዴህ ከተጎጂዎቹ የሁለቱ የአጎት ልጅ ነው። የ17 ዓመቱ ኦባይዳ መጎዳቱን ለመንገር አባቱ ሳይድ ኦዴህን ዘንድ ደወለለት።

አሚር በሰጠው ቃለ ምልልስ “ልጅህ ቀላል ጉዳት ደርሶበታል አልኩት። መርዶውን በስልክ ልነግረው አልደፈርኩም” ብሏል።

ሳይድ በፍጥነት ወደ ህክምና ማዕከሉ ደረሰ። “ልጄ መጎዳቱን ቢነግሩኝ ወዲያው ላየው የሚያስችለኝ መንገድ አልነበረም” ሲል አይኑ በእንባ ርሶ ሁኔታውን አስታውሷል።

ሰይድ ኦዴህ

“ልጄን ማየት እንደምፈልግ ነገርኳቸው። ወደ ክፍሉ ስገባ በፈጣሪ ቸርነት በሰማዕትነት መሞቱን አየሁ” ብሏል።

በማግስቱ የአራቱም የቀብር ሥነ ሥርዓት ሊደረግ ታቀደ። አቤድ ዋዲ ጭንብል አትልቀው መጥረቢያ እና መጋዝ የያዙት ሰዎችን ምስል ከአዕምሮው በማውጣት አስከሬኑን ከሆስፒታል ወደ ቁስራ የማምጣት ስነ ስርዓቱን ተቀላቀለ።

መኪኖቹ እና አምቡላንሶች የናቡስ – ራማላህ መንገድ ይዘው ሲጓዙ በጽንፈኛ የእስራኤል ሰፋሪዎች ድንገተኛ ጥቃት ተሰነዘረባቸው።

ሰፋሪዎቹ መኪናቹን በድንጋይ መቷቸው። ለቀብር ከወጡት የተወሰኑትም ድንጋይ በመወርወር ምላሽ ሰጡ። በዚህ ወቅት እስራኤላውያን ሰፋሪዎች እና ወታደሮች መተኮስ ጀመሩ።

በተፈጠረው “ግርግር እና የጥይት እሩምታ” አብድ ዋዲ ወንድሙን ኢብራሂምን እና ወንድሙን ልጅ አህመድን ከጎኑ አጣቸው።

የፋታህ ንቅናቄ አባል የሆነው ኢብራሂም 63 ዓመቱ ሲሆን ልጁ ደግሞ 24 ዓመቱ ነው። የተወሰነውን ግጭት የሚያሳይው የቪዲዮ ላይ አህመድ እና ሌሎች ሰዎች ከጥይቱ ሲሸሹ ይታያሉ። ብዙም ሳይቆይ አህመድ በጥይት ተመትቶ ሲወድቅ ይታያል።

“የወንድሜ ልጅ ሆዱ ላይ ሁለት ጊዜ እና አንገቱ ላይ ደግሞ አንድ ጊዜ በጥይት እንደተመታ ነግረውኛል። ወንድሜም ወገቡ ላይ በጥይት ተመትቷል” ሲል ዋዲ ተናግሯል።

“በእኛ የቀብር መኪኖች ውስጥ ምንም አይነት መሳሪያ አልነበረም። ብዙውን ጊዜ የፍልስጤምን ባንዲራ መኪናዎች ላይ እናውለበለብ የነበር ቢሆንም ባንዲራችንን እንኳን አላወጣንም። ምክንያቱ ደግሞ ፍርሀቱ ስለነበረ ነው።”

የቁስራ ነዋሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ፍርሃት በመንደሩን ዘልቋል። በአካባቢው የወይራ ምርት የሚሰበሰብበት ወቅት ቢሆንም ሰፋሪዎች ይተኩሳሉ በሚል ፍርሃት ገቢ የሚያገኙበትን ምርት ለመሰብሰብ ወደ መንደሩ ዳርቻዎች ማቅናት እንዳቆሙ ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ እንደሚያመለክተው ከሐማስ ጥቃት በፊትም ቢሆን በዚህ ዓመት የእስራኤላውያን ሰፋሪዎች ጥቃት ጨምሯል።

በየወሩ ከ 100 በላይ ክስተቶች ሪፖርት ሲደረጉ ከጥር እና ነሐሴ ባሉት ወራት ደግሞ ወደ 400 የሚጠጉ ሰዎች ከመሬታቸው ተፈናቅለዋል።

የእስራኤል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆነ ቢሴሌም ለቢቢሲ እንደገለፀው ከሐማስ ጥቃቱ በኋላ “ትኩረት ሁሉ ጋዛ እና ሰሜን እስራኤል ላይ በመሆኑ ሰፋሪዎች የተቀናጀ ጥረት በማድረግ በዌስት ባንክ መሬት ለመያዝ በተደራጀ መልኩ ተንቀሳቅሰዋል።”

ከሐማስ ጥቃት በኋላ ባሉት የመጀመሪያዎቹ ስድስት ቀናት ቢያንስ 46 የተለያዩ ክስተቶችን መመዝገቡን አስታውቋል። በዚህም ሰፋሪዎች በዌስት ባንክ የፍልስጥኤማውያንን ንብረት ማውደምን ጨምሮ አካላዊ ጥቃት እና ዛቻ አድርሰዋል ብሏል።

አብድል ዋዲ

“ባለፈው ሳምንት በሰፋሪዎች ዛቻ ስለደረሰባቸው ብዙ እንስሳት አርቢ ቤተሰቦች ተሰደዋል” ሲሉ የድርጅቱ ቃል አቀባይ ሮይ የሊን ተናግረዋል።

“ነዋሪዎቹ ለቀው እንዲወጡ ቀነ ገደብ በመስጠት ይህን ካላደረጉ ጉዳት እንደሚደርስባቸው እየነገሯቸው ነው። አንዳንድ መንደሮች ሙሉ በሙሉ ባዶ ሆነዋል” ብለዋል።

ከነዚህ መንደሮች አንዷ በራማላህ አቅራቢያ የምትገኘው ዋዲ አል-ሲቅ ናት።

ቀደም ሲል 200 የሚጠጉ የፍልስጥኤም ቤዱዊን ማኅበረሰቦች ይኖሩባት ነበር።

“ለወራት ከሰፋሪዎች ትንኮሳ እና ጥቃት ሌት ተቀን እየገጠመን ነበር። ከጦርነቱ ወዲህ ግን ጥቃቶቹ ጨምረዋል” ሲል የ48 ዓመቱ የዋዲ አል-ሲቅ አርሶ አደር አብዱል ራህማን ካብና ተናግሯል።

ብዙዎቹ ወታደራዊ ልብስ የለበሱና ወደ 60 የሚጠጉ ሰፋሪዎች ጥቅምት 9 ማኅበረሰቡን ማጥቃታቸው አሁን በስደት ላይ ያሉ ሦስት ነዋሪዎች ተናግረዋል።

“በመሳሪያ አጠቁን። ሁሉንም አስፈራሩ። ከዚያም ከበጎቻችን ጋር እንድንወጣ አንድ ሰዓት ሰጡን። ካልሄድን እንገድላችኋለን ብለው አስፈራሩን” ሲል ካብና ተናግሯል።

ነዋሪዎቹ ለመሸሽ ከ10 ኪሎሜትር በላይ በእግራቸው እንደሄዱ የ35 ዓመቱ አካባቢው ነዋሪ አሊ አራራ ተናግሯል።

“ሰፋሪዎቹ ከቤታችን ሁሉንም ነገር ዘርፈዋል። ልጄ በጣም ፈርታ ነበር። ከመደብደብ ባለፈ ምንም ነገር አልተውልንም።”

ጭምብል የለበሱ እስራኤላዊያን አርሶ አደሮችን ሲያጠቁ
የምስሉ መግለጫ,ጭምብል የለበሱ እስራኤላዊያን አርሶ አደሮችን ሲያጠቁ

የዌስት ባንክን ግጭት የሚከታተለው ሌላኛው የእስራኤል የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን የሽ ዲን እና ቢ’ቴሌም እንዳሉት በዋዲ አል-ሲቅ የታየው ማስፈራሪያ እና የግዳጅ መፈናቀል ከጥቅምት 7 ጀምሮ ተደጋግሟል።

ባለፈው ሳምንት በካሜራ ከተቀረጹ አስደንጋጭ ክስተቶች አንዱ ተከስቷል።

በኬብሮን አቅራቢያ በምትገኘው አል-ቱዋኒ በተሰኘች የፍልስጤም መንደር የገባ አንድ ሰፋሪ ያልታጠቀ ፍልስጥኤማዊን ሆዱን ከቅርብ ርቀት በጥይት ሲመታው ታይቷል። ይህ ሲሆን አንድ የእስራኤል ወታደር ቆሞ እያየ ነበር።

ጥቃቱ የጀመረው ሁለት የታጠቁ ሰፋሪዎች ከአንድ ወታደር ጋር በመሆን ከመንደሩ ወጣ ብሎ በሚገኝ ቤት ላይ ጥቃት በመሰንዘራቸው ሲሉ የቤቱ ባለቤትን ጨምሮ ሦስት ነዋሪዎች ተናግረዋል።

“ሦስት እስራኤላውያን ወደ ቤቴ መጡ። መሳሪያ ታጥቀው ነበር። አንደኛው ደግሞ የጦሩን መለዮ ለብሶ ነበር” ሲል የ36 ዓመቱ ሙሳብ ራባይ ገልጿል።

ፍልስጥኤማውያን ከመኖሪያቸው ለቀው እንደማይወጡ የሚገልጽ የግድግዳ ላይ ጽሁፍ
የምስሉ መግለጫ,ፍልስጥኤማውያን ከመኖሪያቸው ለቀው እንደማይወጡ የሚገልጽ የግድግዳ ላይ ጽሁፍ

“ከሰፋሪዎቹ አንዱ ወደ ቤት ገብቶ ገፋኝና በጠመንጃው ጭንቅላቴን ደበደበኝ። ሊተኩስብኝ እንደሆነም ነገረኝ” ብሏል።

የራባይን የእርዳታ ጩኸት የሰሙ ጎረቤቶቹ ደረሱ። ከእነዚህ መካከል የአራት ልጆች አባት የሆነው ዛክሪሃ አድራ ይገኝበታል።

የአድራ የአጎት ልጅ በሆነው ባዝል የተቀረፀው ቪዲዮ እንደሚያሳየው፤ ራባይን ደበደበ የተባለው ሰፋሪ እና የእስራኤል ወታደር ከፍልስኤማውያኑ ጎረቤቶች በቅርብ ርቀት ቆመው ያሳያል።

ታጣቂው ሰፋሪ በድንገት ወደ አድራ ቀረበ ብሎ በጠመንጃው ከመታው በኋላ ሆዱን ላይ ተኮሰበት።

ይህ ሁሉ ሲሆን አድራ ምንም ስጋት በማይፈጥር መንገድ እጆቹን ወገቡ ላይ አድርጎ ይታያል።

እንደ ቤተሰቡ ከሆነ አሁን በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ የሚገኘው አድራ ሆስፒታል ይገኛል። “በህይወት ቢተርፍም፣ ጥይቱ በሆዱ ውስጥ ብዙ ጉዳት አድርሷል” ብሏል የአክስቱ ልጅ ባዝል።

በቤቱ ላይ ጥቃት የተፈፀመበት ሙሳብ ራባይ እንደሚለው ከሆነ በጥይት መምታቱ የመጣው በሰፋሪዎቹ ለቀናት ከተካሄደው ማስፈራራት እና የንብረት ውድመት በኋላ የመጣ ነው።

አቤድ ዋዲ፣ ከአጎቱ ልጅ አብደል ዋዲ (ከመሐል) እና አባቱ ባለፈው ሳምንት ከተገደለበት ሌላኛው ዘመዱ ማህሙድ ዋዲ ጋር
የምስሉ መግለጫ,አቤድ ዋዲ፣ ከአጎቱ ልጅ አብደል ዋዲ (ከመሐል) እና አባቱ ባለፈው ሳምንት ከተገደለበት ሌላኛው ዘመዱ ማህሙድ ዋዲ ጋር

“ከቅዳሜ ጀምሮ መሣሪያ ታጥቀው በመንደሩ ዙሪያ በቡልዶዘር ዛፎችን እያወደሙ ነበር። ሰፋሪዎቹ ጥቃት ከሰነዘሩ በሚል በመንደሩ ያሉት ወንዶች በፈረቃ ለጥቂት ሰዓታት ነበር የሚተኙት” ብሏል።

ቢቢሲ በዌስት ባንክ እና በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ የሰፋሪዎች ድርጅት ቅርጫፍ የሆነውን የሻ ካውንስል ስለጉዳዩ አስተያየት እንዲሰጥ ቢጠይቅም ፈቃደኛ አልሆነም።

በአካባቢው ሰፋሪዎችን የሚወክለው የቢኒያሚን ካውንስል ተጠባባቂ ኃላፊ ሞቲ ዮጌቭ በበኩላቸው “ጠብ ፈጣሪዎች የሰፋሪውን ማኅበረሰብ የማይወክሉ ናቸው። ካሉም እንደሌሎች ወንጀለኞች እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል” ብለዋል።

የእስራኤል ጦር እና የእስራኤል የፖሊስ ስለ ጉዳዩ አስተያየት እንዲሰጡ በተደጋጋሚ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ አልሰጡም።

ዶቭ ኬኒን የተባሉ የቀድሞ የእስራኤል ፖለቲከኛ እና አሁን የሠላም አቀንቃኝ በመሆን የሚያገለግሉት “በጣም የሚያሳዝነው ነገር በእነዚህ ጽንፈኛ ሰፋሪዎች ለሚፈጸመው ጥቃት የእስራኤል ጦር ምንም ዓይነት ምላሽ አለመስጠቱ ነው። ጥቃቱ እነዚህን የፍልስጥኤም ማኅበረሰቦች ለማስወገድ እና ከቤታቸው ለማስወጣት ዓላማ ያደረገ ነው” ብለዋል።

የብዙ ፍልስጥኤማውያን ስጋት በዌስት ባንክ ያለው ሁኔታ እየተባባሰ ይሄዳል የሚል ነው።

የእስራኤል ብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስትር ኢታር ቤን ጊቪር ባለፈው ሳምንት እንዳስታወቁት መንግሥት በዌስት ባንክ የሚገኙ ሰፋሪዎችን ጨምሮ የአገሪቱን ሠላማዊ ዜጎች ለማስታጠቅ 10 ሺህ ጠመንጃ ይገዛል።

ይህ እርምጃ በታጠቁ ሰፋሪዎች እና በጦሩ መካከል ያለውን ድንበር የበለጠ እንዳያጠበው ያሰጋል። የቁስራው አብዲ ዋዲ ስለሚገዙት 10 ሺህ ጠመንጃዎች ሰምቷል። “ለቁስራ ሰዎች ምንም ለውጥ አያመጣም” ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

ዋዲ በግቢው ውስጥ ተቀምጦ ነበር። ግቢው በወንድሙ፣ በወንድሙ ልጅ እና ባለፈው ሳምንት በተገደሉት ሌሎች አራት የመንደሩ ሰዎች ምስል ተሸፍኗል።

“በሰፋሪዎች እጅ ያለውን መሣሪያ ሁሌም እናየዋለን። ለረዥም ጊዜ ሲተኩሱብን ኖረዋል” ብሏል።

የሆነ ነገር መቀየሩንም ግን ይነገራል። ሰፋሪዎች የበለጠ ጠበኛ፣ የበለጠ አክራሪ የሆኑ ይመስላል። “የእርሻ ቤቶች እየተቃጠሉ ነው፤ የወይራ ዛፍ እየተቆረጠ ነው፤ መሬት እየተነጠቀ ነው” ብሏል።

“ይህ የእኛ መንደር ነው። ወደ ተለያዩ መንደሮች ብትሔዱም በእያንዳንዱ ሰው ላይ ቁጣ እና ህመም ታያላችሁ። መጨረሻው የት እንደሆነም አይታወቅም” ብሏል።