የአየር ጥቃት የተፈጸመበት የአልዛህራ ሰፈር

24 ጥቅምት 2023, 07:09 EAT

አል ዛህራ ከጋዛ መናገሻዎች አንዷ ነበረች።

ጋዛ አሉኝ ከምትላቸው ዩኒቨርስቲዎች ‘የፍልስጥኤም ዩኒቨርስቲ እና ኡማህ ዩኒቨርስቲ’ በዚህች ሰፈር ነው የሚገኙት።

በአንድ ወቅት ጋዛ በጥሩነት ከምትጠቅሳቸው ሰፈሮች አንዷ ነበረች።

አሁን ያ ሁሉ ታሪክ ሆኗል።

አል ዛህራ ወደ ፍርስራሽ ክምርነት ተቀይራለች።

የእስራኤል የአየር ጥቃት የነበሯትን ሕንጻዎች አውድሞታል።

እስራኤል በፈጸመችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 25 የመኖሪያ ሕንጻዎች ወደ ፍርስራሽነት ክምርነት ተቀይረዋል።

በአየር ጥቃቱ ቤቷን ያጣችው ኡሙ ሳሊም አል ሳፊን ስለደረሰባት ነገር ስትናገር ምርር ብላ እያለቀሰች ነው።

ከቀናት በፊት ከምሽቱ 2̄፡30 ላይ ነበር የእስራኤል ጦር ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ የሰጣቸው።

በነገታው ከጥዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽት ድረስ ሰፈሩ ላይ የቦምብ ናዳ አዘነቡበት ትላለች።

ትኖርበት በነበረው ሕንጻ 20 የሚሆኑ ቤተሰቦች ይኖሩ ነበር። አሁን የመጠጊያ ያለህ እያሉ ነው።

“እኛ ሰላማዊ ሰዎች ነን። በቤታችን ውስጥ በሰላም እየኖርን ነበር። ለምን በቦምብ ይደበድቡናል? ምን አደረግን?” ስትል በጥቃቱ ቤቷን ያጣችው ኡሙ መሐመድ የተባለች ሌላ ሴት ታስረዳለች።

በአል ዛህራ ላይ የተፈጸመው የአየር ጥቃት ወደ 5 ሺህ የሚሆኑ ፍልስጥኤማውያንን ቤት አልባ አድርጓል። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የጋዛ ነዋሪዎች በተፈናቀሉበት ሁኔታም ተጨማሪ መፈናቀሎች ሊኖሩ እንደሚችሉም የጠቆመ ነው።

በአየር ጥቃቱ ቤታቸውን ያጡ ነዋሪ

“ይህ የዘር ማጥፋት ነው” ይላል ሌላኛው ቤቱን በዚህ ጥቃት ያጣው አቡ ራሚ።

አንዳንድ ቤተሰቦች ከቤታቸው ባለመውጣታቸው በፍርስራሾች ውስጥ መቀበራቸውን ይናገራል።

በፍርስራሾች ክምሮች ውስጥ ሕይወትን መታደግም ሆነ አስከሬናቸውን መልሶ ማግኘት አልተቻለም።

አምቡላንሶችም ሆኑ የድንገተኛ አደጋ ጊዜ ሠራተኞች ከፍርስራሾች ስር ሰዎችን ለማውጣት የሚያስችላቸው መሳሪያ የላቸውም እንዲሁም ወደ አካባቢውም መድረስ አልቻሉም።

“የነበረንን ነገር አጥተናል። ሁሉም ወድሟል” ሲሉም አየር ጥቃቱ ያደረሰባቸውን ውድመት ለመመልከት እና የቀረ ንብረት ካለ ለመፈለግ የተመለሱ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አንዳንዶቹ ልብሶቻቸውን በአንሶላ ጠቅልለው፣ ያገኟቸውን ትራሶች፣ ፍራሾች እና ብርድ ልብሶች ተሸክመው መጠጊያ ፍለጋ ሄደዋል።

በፍርስራሾቹ ውስጥ ንብረታቸውን ለማግኘት የሚያደርጉትን ፍለጋም መሃል ላይ ማቋረጥ ነበረባቸው።

የቢቢሲ ዘጋቢዎች በስፍራው ላይ እያሉም አንድ የከተማዋ ነዋሪ ከእስራኤል ጦር ማስጠንቂያ እንደተሰጠ ተናገረ።

ከቀሩት ትልልቅ ሕንጻዎች ውስጥ አንዱ በአየር ጥቃት ሊመታ እንደሆነ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል። እናም ነዋሪዎች በአፋጣኝ ስፍራውን ለቃችሁ ውጡ ተብሏል አለ።

የአየር ጥቃት የተፈጸመበት የአልዛህራ ሰፈር

በአል ዛህራ ውስጥ ለተፈጸሙት የአየር ጥቃቶች ዒላማ ስለተደረጉ ስፍራዎች ቢቢሲ የእስራኤል መከላከያን አስተያየት ጠይቆ ነበር።

ሐማስ ባደረሰው “አረመኔያዊ ጥቃት” ምላሽ “የሐማስ ወታደራዊ እና አስተዳደራዊ ስፍራዎችን በማፈራረስ የኃይል ምላሽ እየሰጡ” መሆኑ ተገልጿል።

“ሐማስ በእስራኤል ወንዶች፣ ሴቶች እና ሕጻናት ላይ ሆን ብሎ ከሚሰነዝረው ጥቃት በተለየ መልኩ የእስራኤል መከላከያ ዓለም አቀፍ ሕግን በተከተለ መልኩ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ተጨባጭ ጥንቃቄዎችን ያደርጋል” የሚል ምላሽ ሰጥቷል።

ሕንጻዎች የፈራረሱባት አል ዛህራ ሰፈር የተገነባችው በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ ነው። የቀድሞው የፍልስጥኤም ፕሬዝዳንት ያሲር አራፋት የኒትዛሪም የሰፈራ መንደር እንዳይስፋፋ ለማድረግ ነበር ሰፈሯ እንድትገነባ ያዘዙት።

የከተማዋ ሕንጻዎች እና መንገዶች በአንጻራዊነት አዲስ እና ዘመናዊ የሚባሉ ነበሩ። ወደ 60 የሚጠጉ የመኖሪያ ትልልቅ ሕንጻዎችን የነበሯት ሲሆን፣ ወደ አስር ሺህ የሚጠጉ ነዋሪዎች ሰፈርም ናት። የሕዝብ ተቋማት፣ የዩኒቨርስቲዎች እና የትምህርት ቤቶችም ማዕከል ነበረች።

የአል ዛህራ ከተማ ወታደራዊ ዘመቻዎች የማይደረጉባት እና ከዚህ ቀደምም በተደረጉ ጦርነቶች ዒላማ እንዳልነበረችም ሐምዛ የተባለ ነዋሪ ይናገራል።

የአልዛህራ ሰፈር ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት
የምስሉ መግለጫ,የአልዛህራ ሰፈር ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት

በዚህም ምክንያት ከሌሎች ስፍራዎች የተፈናቀሉ በርካቶች መሸሸጊያ አድርገዋት ቆይተዋል።

ግጭቱ ሲጀርም የአል ዛህራ ነዋሪዎች በሌሎች አካባቢ የሚኖሩ ዘመዶቻቸውን አለንልላችሁ አሉ። ቤታችን ይበቃል። ሰፊ ነው አሉ። ዘመዶቻቸውንም ማስተናገድ ጀመሩ። እያንዳንዱ ቤተሰብም ሁለት ወይም ሦስት ቤተሰቦችን ተቀበሉ።

ያልተጠበቀው ሆኖ ቤታቸው በአየር ጥቃት ሲወድም ነዋሪዎቹም፣ እንግዶቻቸውም ያለ መጠለያ ቀሩ። ቤታቸው በጥቃቱ ያልፈረሰባቸውም ቢሆኑ እንኳን ቀያቸውን ለቀው ተሰደዋል።

ነገ የቦምብ ጥቃቱ ተረኛ እንሆናል በሚል ፍራቻም ላለመመለስ ወስነዋል። ሐምዛ በአሁኑ ወቅት በዘመድ ቤት ተጠልሎ የሚገኝ ሲሆን፣ ሁኔታውንም “ሰብዓዊ ጥፋት” ሲል ነው የሚገልጸው።

የእስራኤል “ማስጠንቀቂያ ጥቃቱ ሊፈጸም ደቂቃዎች ሲቀሩት እንደሚነገር” ለቢሲ ተናግሯል።