
24 ጥቅምት 2023, 07:06 EAT
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ በሃዲያ ዞን ውስጥ በሚገኙት ሾኔ እና ሆመቾ ሆስፒታሎች ውስጥ የሚሠሩ የጤና ባለሙያዎች ደሞዛቸው በመቋረጡ በከፊል እና ሙሉ በሙሉ የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ለቢቢሲ ገለጹ።
በዞኑ በሚገኘው ሾኔ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ሐኪም የሆኑት ዶ/ር መሐመድ አሕመድ፣ ባለፈው ዓመት ደሞዝ እየተቆራረጠ ይከፈላቸው እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ላይ መደበኛ ደሞዛቸው ሙሉ በሙሉ ከተቋረጠ ወራት መቆጠሩን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“የተቆራረጠ የደሞዝ ክፍያ ነበር። በመሀል የአንድ ወር ይከፈል ነበር። አሁን ግን የነሐሴ፣ የመስከረም እና የጥቅምት አልተከፈለንም” ብለዋል።
የሕክምና ባለሙያዎች ላቀረቡት ጥያቄ ምላሽ ባለመገኘቱ ሆስፒታሉ ለተወሰኑ ቀናት እንደተዘጋም አክለዋል።
“ሆስፒታሉ መዘጋቱ አግባብነት ባይኖረውም፣ የመጨረሻ ባለሙያው የወሰደው አማራጭ ነው” ሲሉ ዶ/ር መሐመድ ተናግረዋል።
ምላሽ እንዲሰጣቸው የሚመከታቸውን አካላት ሲጠይቁ “የበጀት ጉድለት” አለ የሚል መልስ እንደተሰጣቸው ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።
ያለ ደሞዝ ኑሮን ለመግፋት የተገደዱ የአካባቢው ተወላጅ የሕክምና ባለሙያዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው ቤት በመሄድ እንደሚመገቡ የሚናገሩት ዶክተሩ፣ የትምህርት ቤት ክፍያ መክፈል ተቸግረው ልጆቻቸው ወደ ቤት እንደሚመለሱም በሐዘን ገልጸዋል።
“የቤት ኪራይ መክፈል አቅቷቸው ተባረው ቤተሰቦቻቸው ጋር ሄደው የሚኖሩ አሉ” ሲሉም ያለውን ችግር ገልጸዋል።
“መንግሥት ባለበት አገር ሦስት ወር ደሞዝ ሳይከፈለን በዚህ የኑሮ ውድነት መኖር እንዴት ይቻላል? የሆስፒታሉ መዘጋት የሚቆረቁረው ካለ መጥቶ እንዲጠይቀን እንፈልጋለን” ብለዋል።
- አዲስ አበባ ውስጥ የሕክምና ባለሙያዎች ሥራ አጥነት አለ?17 ጥቅምት 2023
- በኢትዮጵያ በሺህ የሚቆጠሩ ሐኪሞች ለምን ሥራ አጥ ሆኑ?25 ጥር 2022
- “ሀኪሙ ትግሉን አቀጣጠለው እንጂ የሚታገለው ለታካሚው ነው”18 ግንቦት 2019
“ሳንበላ ሳንጠጣ እንዴት ነው ሰው የምናክመው?”
ሌላኛው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የሾኔ ሆስፒታል ሐኪም፣ በትርፍ ሰዓት ክፍያ እና ደሞዝ መቋረጥ ምክንያት ኑሯቸውን መምራት እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
ለሕብረተሰቡ ሲሉ ሥራ ላይ ሆነው ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ እንደቆዩ የሚናገሩት ሐኪሙ፣ “በተደጋጋሚ ያቀረብነው ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ የሥራ ማቆም አድማ ለማድረግ ተገደናል” ብለዋል።
“ደሞዝ ከተከፈለን ሦስተኛ ወራችን ነው። ከሰባት ቀናት በፊት እየሠራን ነበር ጥያቄያችንን ስናቀርብ የቆየነው። ለሦስት ቀናት የድንገተኛ አገልግሎትን ክፍት አድርገን ነበር ሥራ ያቆምነው። ያኔ ባለሥልጣናት መጥተው አነጋገሩን። ሳንበላ ሳንጠጣ እንዴት ነው ሰው የምናክመው? አልናቸው” ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ “የበጀት እጥረት አለ” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ገልጸው “ከዚያ ግን እንደሚከፍሉን ነገሩን። ግን አልከፈሉንም። እኛም ሙሉ በሙሉ ሥራ አቆምን” በማለት ሁኔታውን ገልጸዋል።
“ከቀናት በፊት ደሞዝ ነው ብለው ገንዘብ አስገብተውልን ነበር። የገባልን ሙሉ ደመወዝ አይደለም። የደሞዛችንን 84 በመቶ ነው የከፈሉን። ሦስቱን ወር የገፋነው ተበድረን ነው” በማለትም ሐኪሙ አስረድተዋል።
የተሰጣቸው ደሞዝ ሙሉ እንዳልሆነም ጠቅሰው “ይህንን ምን እናድረገው? ምን በልተን እንሥራ? ነው ጥያቄያችን። ሦስት ወር ሙሉ ደመወዝ አልተከፈለንም። ቁርስ፣ ምሳ ደብተር ላይ እየፈረምን ነው የምንበላው። እስካሁንም የቆየነው በዱቤ የሚመግቡን ሰዎች ስለታገሱን ነው” ብለዋል።
“አሁን ሆስፒታሉ የ24 ሰዓታት አገልግሎት አይሰጥም”
ሌላኛው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ እና በዚያው ሃዲያ ዞን ውስጥ በሚገኘው ሆመቾ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የሚሠሩ የሕክምና ባለሙያም የሥራ ማቆም አድማ ላይ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
ባለሙያው፣ የሠራተኛ ክፍያ መቋረጥን ተከትሎ በመቱት አድማ ሆስፒታሉ የ24 ሰዓት አገልግሎት መስጠት ካቆመ 10 ወራት ተቆጥረዋል ብለዋል።
“አሁን ሆስፒታሉ የ24 ሰዓታት አገልግሎት አይሰጥም። የትርፍ ሰዓት ክፍያ ስለማይከፈለን እየሠራን ያለነው እንደ ሆስፒታል ሳይሆን እንደ ሌላ የቢሮ ሠራተኛ በቀን ለስምንት ሰዓታት ብቻ ነው” ብለዋል የሕክምና ባለሙያው።
ጨምረውም “ሌላው ቀርቶ ምሳ ሰዓት ላይ ወላድ እናት ብትመጣ እንኳን አገልግሎት የሚሰጥ የለም። ተኝቶ የሚታከም ሕመምተኛም በሆስፒታሉ አገልግሎት አያገኝም። ወደ ሌላ ሆስፒታል ነው ሪፈር የሚጻፍለት” ብለዋል።
የሚመለከታቸው አካላት ለጤና ባለሙያዎች ጥያቄ መልስ መስጠት እንዳልቻሉም ይናገራሉ። የዞን እና የከተማው መስተዳደር የበጀት እጥረት እንዳለ በተደጋጋሚ ማንሳታቸውን የሕክምና ባለሙያው ጠቅሰዋል።
“ተገልጋይ ሲንገላታ ይሄን መቅረፍ አለመቻላቸው በጣም ነው የሚገርመኝ” ብለዋል የሕክምና ባለሙያው።
“ነሐሴ ላይ 70 በመቶ ደሞዝ ይግባላችሁ ተባለ። እባካችሁ በዓልን ተበድረን ነው እያሳፍን ያለነው ብለው ያለቀሱ እናቶች አስታውሳለሁ። ምንም ማድረግ አንችልም ብለው መስከረም አጋማሽ አካባቢ የነሐሴውን 70 በመቶ አስገቡ” ሲሉ ገልጸዋል።
“እኛ ብቻ ሳንሆን ሕብረተሰቡም ችግር ላይ ነው ያለው። እኛ ስምንት ሰዓቱን የምንሠራው ቢያንስ ትንሽ ከረዳናቸው በሚል ነው። አሁን ላይ የመንግሥት ሠራተኛ ሆኖ ኑሮን መግፋት ከባድ ሆኖ ሳለ ጭራሽ ለሠራነው ሥራ ደመወዝ አለመከፈሉ መንግሥት ባለበት አገር ግራ የሚያጋባ ጉዳይ ነው” ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸዋል።
እሳቸው ብቻቸውን ስለሚኖሩ በቤተሰብ እርዳታ ሕይወታቸውን እየገፉ እንደሚገኙ በማመልከት “ቤተሰብ ያላቸው ደግሞ የቤት እቃቸውን መሸጥ እንደጀመሩ ሰምቻለሁ። ቴሌቭዥን፣ ጂፓስ፣ አልጋ እየሸጡ ኑሮን ለመግፋት እየሞከሩ ነው። በመሆኑም የሚመለከተው አካል በአስቸኳይ መልስ እንዲሰጠን እንፈልጋለን” ብለዋል።
ደሞዝ ሙሉ በሙሉ በሚገባበት ሁኔታ እንኳን ኑሮ ከባድ በሆነበት በዚህ ወቅት ለወራት የደሞዝ እና የክፍያ መቋረጥ ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ የገለጹት ሐኪሙ “ሞራልም ይነካል” ሲሉ ስሜታቸውን ገልጸዋል።
ሐኪሞቹ እንደገለጹት ከሆነ እነዚህ ሁለት ሆሰፒታሎች በድምሩ ከ800 በላይ ሠራተኞች አሏቸው።
ቢቢሲ የጤና ባለሙያዎቹ ላቀረቡት ቅሬታ ከዞኑ የጤና ቢሮ እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ ስልካቸው ባለመነሳቱ አልተሳካም።