
ከ 5 ሰአት በፊት
ኢትዮጵያ ወደ ሕዋ የላከቻቸው ሳተላይቶች ሥራ ማቆማቸውን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጆኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ገለጸ።
ለመሬት መልከታ ሥራ ወደ ሕዋ የተላኩት ሳተላይቶች ሥራቸውን ያቆሙት የአገልግሎት ጊዜያቸው በመጠናቀቁ መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ አብዲሳ ለቢቢሲ እንደገለጹት ወደ ሕዋ የሚላኩ ሳተላይቶች የቆይታ ጊዜ (ሕዋ ላይ የሚቆዩበት) ቀድሞ የሚታወቅ መሆኑን እና ኢትዮጵያ ያመጠቀቻቸው ሳተላይቶች የአገልግሎት ጊዜያቸው ቀድሞ ይታወቅ እንደነበረ ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያ የሆነችውን Ethiopian Remote Sensing Satellite – 01 (ETRSS – 01) የተሰኘች 70 ኪሎ ግራም የምትመዝን ሳተላይት ታኅሣሥ 10/2012 ዓ. ም. ከቻይና ማምጠቋ ይታወሳል።
ይህች ሳተላይት ለግብርና፣ ለማዕድን፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለአየር ንብረት ጥበቃ እና ለመልከዓ ምድር ጥናት የመረጃ አገልግሎትን ስትሰጥ ቆይታለች።
- የተባበሩት መንግሥታት 35 ሠራተኞቹ ጋዛ ውስጥ እንደተገደሉበት ገለጸ22 ጥቅምት 2023
- በሃዲያ ዞን ሁለት ሆስፒታሎች ለወራት ደሞዝ ባለመከፈሉ ሐኪሞች ሥራ ማቆማቸውን ገለጹ24 ጥቅምት 2023
- በአሜሪካ የፖሊስ አዛዥ ልጅ፣ ሁለት ፖሊሶችን አቁስሎ በፖሊሶች እየታደነ ነው24 ጥቅምት 2023
ከዚህ ሳተላይት መምጠቅ ከአንድ ዓመት በኋላ ተመሳሳይ አገልግሎት የምትሰጥ ET-Smart-RSS ሌላ ሳተላይት ማምጠቋ ተዘግቦ ነበር።
አቶ አብዲሳ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ያመጠቀቻት የመጀመሪያዋ ETRSS – 01 የመሬት ምልከታ ሳተላይት ወደ ሕዋ የተላከችው ለሁለት ዓመት ተኩል አገልግሎት እንድትሰጥ ዲዛይን መደረጓን አመልክተዋል።
ይሁን እንጂ ሳተላይቷ ከተቀመጠላት የአገልግሎት ጊዜ ለተጨማሪ ዘጠኝ ወራት አገልግሎት መስጠቷን ይገልጻሉ።
ሳተላይቶቹ መጨረሻቸው ምን ይሆናል?
የመሬት ምልከታ የሚያደርጉ፣ ለቴሌቪዥን ሥርጭት አገልግሎት የሚውሉ የኮሚዩኒኬሽን ሳተላይቶች፣ የመገናኛ ሰዓት (ጂፒኤስ) ጠቋሚ የሆኑ ሳተላይቶች፣ የአየር ሁኔታን የሚከታተሉ እንዲሁም ለወታደራዊ እና ለስላል ተግባራት ጥቅም ላይ የሚውሉ የተለያዩ ዓይንት ሳተላይቶች አሉ።
ኢትዮጵያ ወደ ሕዋ ልካቸው የነበሩት ሳተላይቶች የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች መሆናቸውን የሚገልጹት ኃላፊው “ልክ እንደ ተልዕኳቸው የተለያየ ተግባር አላቸው። የኮሚኒኬሽን ሳተላይቶች እስከ 15 ዓመት አገልግሎት እየሰጡ ሊቆዩ ይችላሉ። እነዚህ ሳተላይቶች ወደ 36 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር ርቀው ነው የሚቀመጡት። በዚህ ቦታ የመሬት ስበት አነስተኛ ስለሆነ ብዙ ዓመት ያገለግላሉ።”
“የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች ግን ከመሬት በቅርብ ርቀት ሲለሚጓዙ ዕድሜያቸው አጭር ነው። የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ሳተላይት ከመሬት የነበራት ርቀት 628 ኪሎ ሜትር ብቻ ነበር። በዚህ ርቀት የመሬት ስበትን ለመቋቋም ሳተላይቷ ኃይል ስለምታወጣ ዕድሜዋ ያጥራል። ሳተላይቶች ኃይል ሲጨርሱ መልዕክት መላክም ሆነ መቀበል ያቆማሉ” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጆኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ እንደሚሉት ተልዕኳቸው የሚለያይ ዓይነታቸው የተለያየ ሳተላይቶች መኖራቸውን በመግለጽ፣ አገልግሎታቸው ያበቁት ሳተላይቶች ሁለት እጣ ፈንታ ይኖራቸዋል።
ገሚሱ በዲዛይናቸው ወቅት በአግልግሎት ዘመናቸው ማብቂያ ወቅት ፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ እንዲወድቁ ይደረጋል። የተቀሩት ደግሞ ሕዋ ላይ እንዲቀሩ ይደረጋል።
“ሕዋ ላይ የሚቀሩት በረዥም ጊዜ እየተበታተኑ ወደ ጥቃቅን ነገር ይቀየራሉ። ከዚያ ተበታትነው ይቀራሉ። አሁን ላይ በሕዋ ውስጥ ከፍተኛ የስብርባሪ ክምችት አለ። ይህም በሌሎች እየሰሩ ባሉ ሳተላይቶች ላይ ችግር ሊሆኑ ይችላሉ” በማለት ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያ የላካቻቸው ሳተላይቶች በረዥም ጊዜ በራሳቸው ተሰባብረው እንዲጠፉ የሚሆኑ ናቸው። “በ15 እና 20 ዓመት ወደ ጥቃቅን ስብርባሪ ተቀይረው ይጠፋሉ።”

“የኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሳተላይት ለሦስት ዓመት ገደማ ሠርታለች፣ ብዙ መረጃ ልካለች፣ አገልግላለች። ከየትኛውም በላይ ሳተላይቷን በመቆጣጠር፣ መረጃ በመሰብሰብ እና መረጃ በመተንተን ልምድ አካብተናል” ብለዋል ዳይሬክተሩ።
ETRSS – 01 ከተገኘው መረጃ በመነሳት የሐዋሳ ሐይቅ ብክለት ላይ ጥናት መደረጉን እንዲሁም የቱሪዝም መተግበሪያዎችን ለማልማት ጥቅም ላይ መዋሉን ገልጸዋል።
ETRSS – 01 መልዕክት የመላክም ሆነ የመቀበል አቅሟ በጣም እየደከመ በመሄዱ ከሌሎች አገራት ሳተላይቶች መረጃ እየተቀበሉ መሆኑን የገለጹት አቶ አብዲሳ፣ በዚህም ምክንያት የሚፈጠር ክፍተት አይኖርም ብለዋል።
በቀጣይ ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ ለተመሳሳይ ዓላማ የሚውል ሌላ የበለጠ የጥራት ደረጃ ያለው ሳተላይት ለማምጠቅ ዝግጅት ላይ መሆኗን አቶ አብዲሳ ተናግረዋል።
ከመሬት ምልከታ ሳተላይት በተጨማሪ ኢትዮጵያ የኮሚዩኒኬሽን ሳተላይት የማምጠቅ ፍላጎት እንዳላት አቶ አብዲሳ ለቢቢሲ ጨምረው ተናግረዋል።
የኮሚዩኒኬሽን ሳተላይት ለማምጠቅ “የአዋጭነት ጥናት አካሂደን አዋጭነቱን ተመልከተናል። ፍላጎቱም አለ። ከፋይናንስ አንጻር የኮሚዩኒኬሽን ሳተላይት የሚያስፈልገው ወጪ ከፍተኛ ስለሆነ ፋይናንሱ በሚገኝበት ወቅት አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል ዝግጅት አለን” ብለዋል።