October 24, 2023 

“የኢትዮጵያዊነት ማስክ” ካጠለኩ ዳግም የኢትዮጵያን ህዝብ ለማማለል እችላለሁ የተበላ እቁብ ከመሆን የዘለለ አይደለም፣ 

በነዓመን ዘለቀ

“ቱሪስት ብላ?” ወይንም “ማሞ ሌላ ወታወቂያው ሌላ” እንበለው? ። ነውረኛ ከሃዲው ፣”ታላቅ ትርክት” በሚል ዛሬ ባስተላለፈው ባዶ የቃላት ጋጋታ ፣ “የኢትዮጵያዊነት ማስክ” ካጠለኩ ዳግም የኢትዮጵያን ህዝብ ለማማለል እችላለሁ ከሚል፣ የህዝብን የማሰብና ወደ ኋላ አዙሮ የማየት አቅም የለውም ከሚል የተለመደ በህዝብ ላይ ካለው ንቀትና፣ የራሱን ድንቁርና ፣ የቀን ቅዠቶች እንደ ትልቅ እዋቂነት መቁጠር አባዜው ተጨማሪ ማሳያ ነው። የተበላ እቁብ ከመሆን ግን የዘለለ አይደለም፣ የዚህ ከሃዲ ግፈኛ እንቶ ፈንቶ የሚገዛ ኢትዮጵያዊ ዜጋ (ከደንዙዞች ፓርላማ አባላትና ከብልጽግና ካድሬዎች ውጭ ካለ) አንገት የሌለው፣ አዙሮ ማየት የማይችል ወይንም የዋሃን ብቻ ናቸው።

ባለፉት ሰባት፣ ስምንት ወራት ውስጥ አብይ አህመድና የኦሮሚያ ብልጽግና በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የፈጸማቸውን ዘርፈ ብዙና ግዙፍ ክህደቶች ጥቂቶቹን ብቻ መለስ ብለን ብንቃኝ፣ ዛሬ በአዲስ አበባ፣ በአማራ ክልል በህዝብ ላይ እየተፈመ ያሚገኘው ግፍና መከራ ቆም ብሎ ማሰብ ብቻ በቂ ነው’’። ሽመልስ አብዲሳ በተደጋጋሚ እንደነገረን “ኢትዮጵያን በእኛ አምሳል እንፈጥራለን፣ እኛን የምትመሰል ኢትዮጵያን እውን እናደርጋለን” ከሚል እብሪት የተወጠረው የአብይ አህመድ ኦሮሞያ ብልጽግና፣ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ኣባቶች ላይ የተፈጨሙ የመብት ረገጣዎችና ወንጀሎች፣ ማንም ተጠያቂ ያለሆነባቸው ጥቃቶች፣ ድበዳብዎች፣ ግድያዎች(የሻሸመኔን ጨምሮ) ፣ በአዲስ አባባ ዙሪያ ሸገር በሚባለው ‘አዲስ ከተማ” 110,000 የድሃ ቤቶች አፍርሰው ከ500፣ 000 በላይ አማራ፣ ጉራጌ፣ ጋሞ ድሆችን “በህገ ወጥ ግንባታ” ሰበብ እጅግ አረመኔያዊ በሆነ ሁኔታ ማፈናቀል፣ በአማራ ህዝብ ላይ ጦርንት ከፍቶ ህዝቡን በጦርነት እሳት መለብለብ፣ በሰሜኑ ጦርነት የደቀቀን ክልል ህዝብ ማሳደደ፣ በድሮን መደብደብ፣ ንጿንን መጨፍጨፍ፣ በገበሬ ማሳ በከባድ መሳሪያ አረር መደብደብ፣ ስልጣኑን ያጸናውን ፋኖን ማሳደድ፣ መግደል፣ ከ100,000 በላይ የአማራ ክልል ተወላጆችን በማንነታቸው በጅምላ አስሮ ፣ እጅግ አስከፊ ኢ-ሰብአዊ ሁኔታ፣ በአዲስ አበባ በገላን፣ በአዋሽ አርባ ከሰውነት በታች ሆነው እንዲሰቃዪ፣ ሰቆቃ መፈጸም፣ በረጅም እስር እንዲማቅቁ ማድረግ። ተዘርዝሮ እያልቅም።

ያን ሁሉ ያልተቆጠበ ድጋፍ፣ ፍቅርና ፣ አመኔታ ለሰጠው ኢትዮጵያዊ ብሄረተኛ፣ ለአማራው ህዝብ፣ ለድሃው የኢትዮጵያ ህዝብ የዚህ የበሻሻ ደላላና የኦሮሚያ ብልጽግና ካድሬዎች የበላይነትና ጨፍላቂነት ለማረጋገጥ፣ የምስራቅ ኦሮሞ ኢምፓየር የቀን ቅዠት እውን ለማድረግ ባለፉት ጥቂት አመታት፣ በተለይም ከየካቲት 2015 ጀምሮ ለኢትዮጵያ ህዝብ የደገሱለት ማሸማቀቅ፣ ማፈናቀል፣ መጨፍጨፍ፣ በገዛ ከተማው ፣ በገዛ ሀገሩ እንደ ውሻ ማሳደድ፣ ቤቱን ማፍረስ፣ ቤተ እምነቱን ማፍረስ ፣ እምነቱን፣እሴቱን ባንዲራውን መድፈር። በአድዋ ክብረ በአል፣ በቅርቡ በተድረገው የመስቀል በአል የተፈጸሙ የህዝቡን ማንነት፣ ክብርና ፣ ምልክቶች ለመንጠቅ፣ ለማራከስ፣ መብቱንና ይገልጸኛል ፣ ይወክለኛል የሚለውን ምልክት፣ ለመንጠቅ፣ ለመጨፍለቅ በፌደራል ፓሊሶችና በአዲስ አባባ ፓሊሶች የተፈጸሙትን ማስታወስ ብቻ ደምን የሚያፈሉ ናቸው። በኑሮ ውድነት እንዲቆራመድ፣ በአንጻሩ ደግሞ እነሱ አልጠግብ ባይ ሆነው ሲተፉ እያደሩ ህዝብ ኑሮ አልገፋ ብሎት የምድር ሲአል በሆነባት የዛሬ ኢትዮጵያ እስከፊ፣ አስነዋሪና፣ መራር ሃቆች እንደሆኑ ጠንቅቆ ለሚያውቀውና ለሚኖርበት ፣ ያሸማቀቀው፣ ያሳደደው፣ ያፈናቀለውን፣ በየእስር ቤቱ ያጎረው ኢትዮጵያውያንን ለማማለል አይኑን በጨው ታጥቦ ኑ “ታላቅ ትርክት” አዳምጡ ብሎ በተለመደ ድፍረት ይሰብካል፣ ይህ ጉድ የማልቅበት ነውረኛ ይጠቅመኛል ሲል በሚያነሳው ሲያሻው ደግሞ ውርውሮ በሚጥለው “የኢትዮጵያዊነት ካባ” ዳግም ሊያጭበረብር ይጋጋጣል ።

“ሰላም” ና “ፍቅር” እውን የሚሆኑት በሰብካ ሊሆን አይችልም። ሰላም የሚረጋገጠው ፍትህ ሲሰፍን ነው፣ እኩልነት፣ የዜጎች ነጻነት ሲረጋገጡ ብቻ ነው፣ እውነተኛ ሰላም ፣ ዘላቂ ሰላም የሚሰፍኑት ይህ የበሰበሰ የብሄር/የዘውግ ፓለቲካ ተወግዶ ኢትዮጵያ የሁሉም ዜጎች እኩልነት፣ በየትኛውም አካባቢ ፣ ቦታ ሄደው ሁለንተናዊ መብቶቻቸው የሚከበርባት፣ ደህንነታቸው ፣ ሰላማቸው የሚረጋገጥባት የመዋቅራዊና የህገ መንግስታዊ ለውጦች ሰደረጉ ብቻ ነው። በነዓመን ዘለቀ