ከእዳ ወደ ምንዳ ወይስ ከእዳ ወደ እዳ ? ( በምንሊክ ሳልሳዊ )
በአማራው ትግል በፋኖ ጀግንነት ነፍስ ውጪ ነብስ ግቢ ላይ ያለው የብልፅግና አገዛዝ የሕዝብን ጥያቄ በስልጠና እና በሰልፍ የሚፈታው ይመስል ሲደክም እያየነው ነው። የሐገርን ሐብት ለብክነት ከመዳረግ ውጪ ስልጠና እና ሰልፍ ምንም ፋይዳ የለውም። ብልፅግና አንድም ቀን ለዘላቂ መፍትሔ ሲሰራ ታይቶ አይታወቅም።

ሐገር ሰላም አታለች፣ ሕዝብ በኑሮ ውድነት እና በስራ ማጣት እየተሰቃየ ነው፣ ዜጎች ከቦታ ቦታ ተዘዋውሮ ለመስራት አዳጋች ነው፣ ስጋትና ውጥረት አገሪቱ ከመውረር አልፈው በየአቅጣጫው የጦርነት ቀጠናዎች በርክተዋል። የዚህ ሁሉ ችግር መንስኤው ብልፅግና ነው። ለችግሮች መፍትሔ መፈለግ ዳገት የሆነበት አገዛዝ በስልጠና ጊዜ ማባከኑ ሳያንስ ሰልፍ ለማድረግ ደፋ ቀና እያለ ነው። ከአሁን ቀደም መፍትሔ ባላመጡ ስራዎች ላይ ተጠምዶ አገርንና ሕዝብን ለጉስቁልና እየዳረገ ነው።
ሕዝቡ ከጫፍ እስከ ጫፍ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የማሕበራዊ ጥያቄዎች አሉት። ይህንን ጥያቄ መመለስ ያለበት አገዛዝ ሀይል መጠቀምን አቁሞ አስቸኳይ መልስና መፍትሔ ይስጥ ወይንም የመፍትሔ ለሚሰጥ አካል ስልጣኑን ይልቀቅ። በስልጠናና በሰልፍ የሕዝብ ችግርን መፍታት አይቻልም ፤ በሚዲያ ፕሮፓጋንዳ ፣ በውሸት ተስፋ ዲስኩር አሊያም በአጀንዳ የሕዝብ ችግር አይፈታም ። ብልፅግና የራሱንም የትውልዱንም ጊዜ በማባከን ስራ ላይ ተጠምዷል ፤ ግጭትና አጀንዳ መጥመቅ ይቁም። ምንዳ ሳይሆን እዳ የተሸከመው ሕዝብ ጦርነት ሰልችቶታል። #MinilikSalsawi