
24 ጥቅምት 2023, 09:34 EAT
እስራኤል በሰሜን ጋዛ ለምታደርገው ወታደራዊ ዘመቻ አካባቢያቸውን ለቀው ወደ ደቡባዊ ጋዛ እንዲሸሹ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ፍልስጥኤማውያን ወደ ቀያቸው እየተመለሱ እንደሆነ የተባበሩት መንግስት አስታወቀ።
በደቡብ ጋዛ በገጠማቸው አስከፊ ሁኔታ ምክንያትም ወደ ቤታቸው መመለስ መጀመራቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከፍተኛ ባለስልጣን ተናግረዋል።
እስራኤል 1.1 ሚሊዮን የሰሜን ጋዛ ከተማ ነዋሪዎች ለደህንነታቸው ሲሉ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ባለፈው ሳምንት ማስጠንቂያ ሰጥታ ነበር።
የተባበሩት መንግስታት ባለስልጣን እንደገለጹት ከሆኑ የሸሹት ዜጎች በደቡብ ጋዛ መጠለያ፣ ምግብ እና የመጠጥ ውሃ ለማግኘት መቸገራቸውን ተናግረዋል።
በሐማስ የሚመራው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እስራኤል በደቡብ ጋዛ በሰነዘረችው የአየር ጥቃት በአንድ ቀን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸው አስታውቋል።
የእስራኤል ጦር በጋዛ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሐማስ ወታደራዊ ዒላማዎችን መምታቱን ተናግሯል።
ጦሩ በምድር ከሚያደርገው ወታደራዊ ዘመቻ በፊት የአየር ጥቃቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።
ጥቅምት 7 ሐማስ በፈጸመው ጥቃት ቢያንስ 1400 ሰዎች ሲገደሉ 222 የሚያህሉትን አግቶ ወስዷል።
ይህንን ያልተጠበቀ ጥቃት ተከትሎ እስራኤል እየፈጸመችው ባለው የማያባራ የአየር ጥቃት በጋዛ ሰርጥ ብቻ ከ5 ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን የጋዛ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገልጿል።
እስራኤል ጋዛ ሰርጥን ሙሉ በሙሉ በመዝጋት ከበባ እንዲደረግ ያዘዘች ሲሆን፣ በጋዛ ‘ኤሌክትሪክ፣ ምግብ፣ ነዳጅ መግባት ከልክላለች።
ከቅዳሜ ጀምሮ በተወሰነ ደረጃ በግብጽ በኩል በሚገኘው የራፋህ ማቋረጫ በኩል ጥቂት የእርዳታ መኪኖች እንዲገቡ ፈቅዳለች።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዳስታወቀው ከ1.4 ሚሊዮኑ የጋዛ ነዋሪ ወደ ሁለት ሦስተኛው በፍርሃት ወይም መኖሪያቸው ስለወደመ ቤታቸውን ጥለው ለመሸሽ ተገደዋል።
- በሃዲያ ዞን ሁለት ሆስፒታሎች ለወራት ደሞዝ ባለመከፈሉ ሐኪሞች ሥራ ማቆማቸውን ገለጹ24 ጥቅምት 2023
- የጋዛን ሰፈር ወደ ፍርስራሽ ክምርነት የቀየረው ጥቃት24 ጥቅምት 2023
- በፍልስጥኤማውያን ላይ የተባባሰው የእስራኤላውያን ሰፋሪዎች ጥቃት24 ጥቅምት 2023

የቢቢሲው ጋዜጠኛ ራሽዲ አቡአሎፍ እንዳለው በደቡብ ጋዛ የምትኘው ዃን ዩኒስ ከተማ ከ600 ሺህ እስከ 700 ሺህ በሚደርሱ ተፈናቃዮች ተጨናንቃለች።
በርካቶቹም በሆስፒታሎች እና ሬስቶራንቶች ውስጥ ተጠልለዋል። መንገድ ላይ ለመተኛት የተገደዱ መኖራቸውንም አስታውቋል።
የተባበሩት መንግስታት የፍልስጥኤም ስደተኞች ኤጀንሲ ዳይሬክተር ቶማስ ዋይት ለቢቢሲ እንደተናገሩት አብዛኞቹ ተፈናቃዮች በቀን 1 ሊትር ውሃ እና አንድ ወይም ሁለት ዳቦ ብቻ በመመገብ ኑሯቸውን ለመግፋት ተገደዋል።
የሰብዓዊ ቀውሱ መባባስ እና በደቡብ ጋዛ የሲቪሎች መኖሪያ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት “አንዳንድ ሰዎች ወደ ሰሜን እንዲመለሱ አድርጓል” ብለዋል።
“ነዋሪዎቹ በሰሜን ያለውን ቤታቸውን፣ ሥራቸውን፣ ሕይወታቸውን ትተው ወጥተዋል። ደቡብ ጋዛ ሲደርሱ መጠለያ ለማግኘት እየታገሉ ነው፣ የምግብ እጥረት አለ። ብዙ ሰዎች የማይጠጣ ውሃ ለመጠጣት ተገደዋል። በደቡብ ጋዛ ያለው ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ነው” ብለዋል።
ተፈናቅሎ በዃን ዩኒስ የሚኖረው ሪያድ ጃባስ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደገለጸው “ከጋዛ ከተማ ተባረርን። ዃን ዩኒስ ጥቃት የለም ቢሉም ጋዛ ውስጥ ጥቃት የማይፈጸምበት አካባቢ የለም” ብሏል።
ቅዳሜ የእስራኤል ጦር በጋዛ ከተማ በበተናቸው በራሪ ወረቀቶች ላይ ከዋዲ ጋዛ ወንዝ ወደ ደቡብ የማይሄድ ማንኛውም ሰው “የሽብርተኛ ድርጅት ተባባሪ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል” ሲል አስጠንቅቋል።
የተባበሩት መንግስታት በሳምንቱ መጨረሻ ምግብ ፣ ውሃ እና ህክምና ቁሳቁስ የጫኑ 34 መኪናዎች መግባታቸውን በደስታ ቢቀበልም፤ ነዳጅን ጨምሮ የጋዛን ፍላጎት ለማሟላት በቀን በመቶዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ የእርዳታ መኪናዎች እንደሚያስፈልግ ዋይት አስጠንቅቀዋል።
“ከግጭቱ በፊት ጋዛ በቀን ወደ 455 የሚጠጉ የጭነት መኪናዎች ትቀበል ነበር። ስለዚህ የሎጂስቲክስ ሥራውን ለማሳደግ ብዙ መንገድ ይቀረናል።”
“በጋዛ ለሦስት ቀን የሚበቃ ነዳጅ ብቻ ይቀረናል። እስራኤል ወደ ጋዛ እንድትገባ መፍቀድ ካልቻለች የእርዳታ ሥራችን ይቆማል። የውሃ ማጣሪያዎች እና ሆስፒታሎች ሥራ ማቆም ይጀምራሉ” ሲሉ አክለዋል።
የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በ 13 የህዝብ ሆስፒታሎች ውስጥ ያሉት ጄነሬተሮች ነዳጅ እየጨረሱ መሆኑን አስታውቋል። አሁንም ቢሆን 130 ሕፃናትን በሕይወት ለማቆየት የሚረዱ ኢንኩቤተሮችን ጨምሮ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ሕይወት አድን አገልግሎቶችን ብቻ እየሠሩ መሆናቸውን አሳውቋል።
እስራኤል ነዳጅ ቢገባ ሊሰረቅ እና ሐማስ ለወታደራዊ አገልግሎት ሊጠቀምበት እንደሚችል በመግለጽ እንዳይገባ ከልክላለች።
የእስራኤል የመከላከያ ሚኒስቴር እሑድ እንዳስታወቀው ሐማስ “1 ሚሊየን ሊትር የነዳጅ ክምችት ” አለው። ቡድኑን “ለተቸገሩት [ነዳጅ] ለመስጠት ፈቃደኛ ካለመሆኑም በላይ የሽብር ዋሻዎቹን ለማብራት፣ ለሮኬት ማስወንጨፊያዎች እና ለራሳቸው ቤት” ተጠቅሞበታል ሲል ከሷል።
የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት ባለፉት ቀናት በጋዛ 320 ዒላማዎችን መምታቱን አስታውቋል። ከነዚህ መካከል “የሐማስ አሸባሪዎችን የያዙ ዋሻዎች፣ በደርዘን የሚቆጠሩ የማዘዣ ጣቢያዎች… ወታደራዊ እና የቅኝት ቦታዎች” ይገኙበታል” ብሏል።
በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በተጋሩ ቪዲዮዎች እስራኤል በጋዛ ባደረሰችው ተከታታይ ጥቃቶች ሰማይ ምድሩ ሲያበራ አሳይተዋል።
በጋዛ ከተማ የሚገኘው የአል-ቁድስ ሆስፒታል ዳይሬክተር ለቢቢሲ እንደተናገሩት በተቋሙ 100 ሜትር ርቀት ላይ 10 ጥቃቶች ተሰንዝረዋል። በሆስፒታሉ 500 ታካሚዎች እና ሌሎች 1,500 ሰዎች ተጠልለው ይገኛሉ።
ሰኞ ከሰአት በኋላ የጋዛ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በ24 ሰዓታት ብቻ 182 ህጻናትን ጨምሮ 436 ሰዎች መገደላቸውንና ጠቅሷል። አብዛኛዎቹ ግድያዎች የተፈጸሙት በደቡብ ጋዛ መሆኑን ገልጿል።
ሐማስ የድንበር ተሻጋሪ ጥቃትን ተከትሎ እስራኤል እየፈጸመችው ባለው የሌት ተቀን የአየር ጥቃቶች የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 5,087 መድረሱንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
አሐዙ በጋዛ ከተማ በአል አህሊ አረብ ሆስፒታል በደረሰ ፍንዳታ የተገደሉ 471 ሰዎችንም ያጠቃልላል። ለጥቃቱ ሐማስ የእስራኤልን የአየር ድብደባን ተጠያቂ ሲያድርግ ቴል አቪቭ በበኩሏ ፍንዳታው በፍልስጥኤም እስላማዊ ጂሃድ የተተኮሰ ሮኬት የፈጠረው ነው ብላለች።
የዩናይትድ ኪንግደምም ፍንዳታው “በሚሳኤል ወይም ከጋዛ ወደ እስራኤል በተተኮሰ ሚሳኤል የተከሰተ ሊሆን እንደሚችል” ገልጾ የአሜሪካ፣ የፈረንሳይ እና የካናዳ መደምደሚያ ይህንኑ የእስራኤል ሃሳብ አስተጋብቷል።
ከጥቅምት 7 ጀምሮ ከጋዛ 7 ሺህ ገደማ ሮኬቶች በሐማስ እና በሌሎች ቡድኖች ወደ እስራኤል መተኮሳቸውን ገልጿል። ከእነዚህ ውስጥ 550 የሚያህሉት ጋዛ ውስጥ መውደቃቸውን አስታውቋል።