በኦሮሚያ በሚፈጸሙ እገታዎች ሕዝቡ እያማረረ ነው።
ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀው አስተያየታቸውን የሰጡን በምስራቅ ሸዋ ዞን የአደአ ወረዳ ጊጬ ጋራ-ባቦ ቀበሌ ነዋሪ በየሰበብ አስባቡ ተስፋፍቷል ያሉት የእገታ ተግባር አሁን አሁን የነዋሪዎች ዋነኛ ስጋት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ አስተያየት ሰጪው በቅርቡ ከዚሁ ቀበሌ አንድ ሰው ተገድለው ሌሎች ሶስት በሌሊት ታግተው ተወስደው በነፍስ ወከፍ መቶ ሺህ ብር ከፍለው መውጣታቸውንም አመልክተዋል፡፡
ሌለው በምእራብ ሸዋ ዞን አደዓ በርጋ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አስተያየት ሰጪ በወረዳው ጃሎ ከሚባል አከባቢ በቅርቡ እንኳ በአንድ ሌሊት የተወሰዱ 10 ሰዎች ገደማ ከመቶ ሺህ እስከ አንድ ሚሊየን ተጠይቀው ከፍለው መውጣታቸውን ገልጸዋል፡፡
ከዚሁ ዞን ደንዲ ከተባለ ወረዳ ቤተሰብ ደጋግሞ እንደታገተባቸው ገልጸው አስተያየታቸውን የሰጡን የጊንጪ ከተማ ነዋሪ የእገታ ተግባራቱ እየተለመደ በመምጣቱም የህብረተሰቡን የመንቀሳቀስ መብቱ አደጋ ውስጥ ከቶታል ብለዋል።
አያይዘውም “የታጠቁ አካላት ትንሽ መሸት ሲል ታጥቀው ወደ ሰው ቤት ይገባሉ፡፡ የሚወስዱት ከብት ወይም ሌላ ንብረት አይደለም፡፡ ከቤተሰብ አባላት አንዱን ይዘው ይሄዱና ትንሽ ቆይተው ስልክ በመደወል ገንዘብ ይጠይቃሉ፡፡ አንድ ሰው እስከ 500 ሺህ ብር ይጠየቃል፡፡” ሲሉ ለDW ተናግሯል።
አስተያየት ሰጪው በዚህ አከባቢ በተለይም ከኦሎንኮሚ ከተማ ወደ በቾ በሚወስደው መንገድ ፍንጫአ-ቦሬቲ በሚባል ቀበሌ ችግሩ የከፋ ነው፤ ይህን ተግባር የፈሩ አርሶአደሮች መተዳደሪያ እርሻቸውን ትተው ወደ ከተማ እየፈለሱ ነው ብለዋል፡፡
ሌላው ከሰሜን ሸዋ ዞን ሰላሌ ደራ ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪም “የእገታው መክፋት አሁንም ችግር ውስጥ ከቶናል፡፡ ገንዘብ አለው ተብሎ የሚገመት ሁሉ ይታገታል፡፡“ ማለታቸውን DW ከአዲስ አበባ ዘግቧል።