
ከ 1 ሰአት በፊት
የፌስቡክ እና ኢንስታግራም ባለቤት የሆነው ሜታ፣ ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀም ያለውን ጉዳት ግልጽ ባለማድረግ እንዲሁም በወጣቶች ዘንድ የአእምሮ ጤና ቀውስ በመፍጠር ተከሰሰ።
በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ይፋ የተደረገው ይህ ክስ የተመሠረተው በፌደራል ፍርድ ቤት ነው።
ተቋሙ ተጠቃሚዎችን “ለማጥመድ” ሱስ የሚያስይዝ አሠራር መዘርጋቱ ተገልጿል። በተያያዘም በማኅበራዊ ገጾቹ አማካይነት የሚደርሰውን “የከፋ አደጋ” ደብቋል በሚልም ነው ክሱ የተከፈተው።
ሜታ በክሱ “በጣም ከፍቶኛል” ብሏል።
ክሱ እንደሚለው፣ ሜታ “አሳሳች” አካሄድን በመከተል የተጠቃሚዎች ደኅንነት ጥበቃ ስምምነትን ጥሷል።
ተቋሙ ከ13 ዓመት በታች ያሉ ልጆችን መረጃ እንደሰበሰበ ተገልጿል። ይህም የልጆች የበይነ መረብ ደኅንነት ጥበቃ መርሕን ይጥሳል።
የኒው ዮርክ ዐቃቤ ሕግ ላቲሻ ጄምስ “እንደ ሜታ ያሉ ማኅበራዊ ገጾች ለወጣቶች የአእምሮ ጤና ቀውስ ሚና አላቸው። ተጠያቂ ሊደረጉ ይገባል” ብለዋል።
ከላቲሻ በተጨማሪ 33 ዐቃቤ ሕጎች ክሱ ላይ ፊርማቸውን አስፍረዋል።
ዘጠኝ የአሜሪካ ግዛቶች የየራሳቸውን ክስ አዘጋጅተዋል።
ክሱን የመሠረቱት ዐቃቤ ሕጎች የገንዘብ ካሳ እንዲሰጥ እና ፌስቡክ አደገኛ የተባለ አካሄዱን እንዲያቆም ነው ጥያቄያቸው።
ታዳጊዎች ለሰውነታቸው በጎ አመለካከት እንዳይኖራቸው የሚያደርግ የምሥል አርትኦትን እንደ ምሳሌ ተጠቅሷል።
የሜታ ቃል አቀባይ እንዳሉት ተቋሙ ከዐቃቤ ሕግ ጋር የሚስማማበት ነጥብ ለታዳጊዎች ደኅንነቱ የተጠበቀና አወንታዊ የበይነ መረብ አሠራር መኖር እንዳለበት ነው።
“ታዳጊዎችና ቤተሰቦቻቸውን ለመርዳት ከ30 በላይ አሠራሮች ዘርግተናል” ብለዋል።
- “ፌስቡክ ስከፍት የአባቴን አስክሬን አየሁት”11 የካቲት 2023
- ኬንያዊው ፌስቡክ ላደረሰበት የአእምሮ ቀውስ ክስ እንዲመሠርት ፍርድ ቤት ፈቀደለት7 የካቲት 2023
- አሰቃቂ ምስሎችን የሚያዩ ኢትዮጵያውያን እና ሌሎች የፌስቡክ ሠራተኞች ብሶት18 ጥር 2023
ቃል አቀባዩ ጨምረውም “በዘርፉ ካሉ ተቋማት ጋር ተባብሮ መሥራት ሲቻል ዐቃቤ ሕግ ይሄንን መንገድ መምረጡ አሳዝኖናል። ተባብሮ መሥራት ግልጽና ዕድሜ የሚመጥን ይዘት ለወጣቶች ማቅረብ ይቻላል” ብለዋል።
ሜታና ሌሎችም ማኅበራዊ ሚዲያዎች በአሜሪካ በመቶዎች የሚቆጠሩ ክሶች የአእምሮ ጤናን በማወክ በቤተሰቦችና ትምህርት ቤቶች ቀርበውባቸዋል።
በ2021 የተለያዩ ግዛቶች ዐቃቤ ሕጎች ምርመራ አድርገውበታል። ፍራንሲስ ሀውገን የተባለች የቀድሞ ሠራተኛ በአሜሪካ ምክር ቤት ቀርባ ምስክርነቷን ሰጥታለች። ክሶቹም ይህን ተከትለው ነው የመጡት።
ሜታ፣ ኢንስታግራም የአእምሮ ጤና ይጎዳል መባሉን አስተባብሏል።
በሜታ የጥናት ክፍል ኃላፊና የተቋሙ ምክትል ፕሬዝዳንት ፕራቲቲ ሬይቾሃዱሪ “ኢንስታግራም ለወጣት ሴቶች ‘መርዛማ’ ነው የሚለው የተሳሳተ ነው” ብለዋል።
የሠሩት ጥናት ወጣቶች ከባድ ሁኔታ ውስጥ ሲሆኑ ኢንስታግራም እንደሚጠቅማቸው እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
የፌስቡክ ዕድገት ከሥነ ልቦና ጉዳት ጋር የተሳሰረ እንዳልሆነ የሚጠቁሙ ጥናቶች አሉ።
ሆኖም ግን ወጣቶች ብዙ ሰዓት ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲያጠፉ የአእምሮ ጫና እንደሚፈጠር የሚጠቁሙም ጥናቶች አሉ።
በዩናይትድ ኪንግደም ሞሊ ራሰል የተባለችው ተማሪ ሕይወቷ ያለፈው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባለ አሉታዊ ይዘት ሳቢያ እንደሆነ ተገልጿል።