ሊ ሻንግፉ

ከ 4 ሰአት በፊት

ቻይና ለሁለት ወር ከአደባባይ ጠፍተው የነበሩት የመከላከያ ሚኒስትር ሊ ሻንግፉን ከሥልጣናቸው አነሳች።

ሚኒስትሩ ከሥልጣናቸው ለምን እንደተነሱ የተሰጠ ኦፊሴላዊ ምክንያት የለም፤ ምትካቸው ማን ሊሆን እንደሚችልም ምንም አልተባለም።

በቅርቡ በርካታ የቻይና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከሥልጣናቸው የተነሱ ሲሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኪን ጋንግ ይጠቀሳሉ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እና መከላከያ ሚኒስትሩ የብሔራዊው ምክር ቤት አባልነታቸውም ተሰርዟል።

የቻይና ከፍተኛ ሕግ አውጭ የሆነው ብሔራዊ የሕዝብ ኮንግረስ ቋሚ ኮሚቴ የሁለቱን ግለሰቦች ከሥልጣን መወገድ ማፅደቁን ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሲሲቲቪ ዘግቧል።

ቤጂንግ በያዝነው ሳምንት የውጭ ሃገራት መከላከያ ሚኒስትሮች ስብሰባን የምታስተናግድ ሲሆን የራሷ መከላከያ ሚኒስትር ግን የላትም።

ሮይተርስ ባለፈው ወር እንደዘገበው ሚኒስትሩ ከንብረት ግዢ ሙስና ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው ምርመር እየተካሄደባቸው ነበር።

መከላከያ ሚኒስትሩ ለመጨረሻ ጊዜ በአደባባይ የታዩት በአውሮፓውያኑ ነሐሴ 29 ከአፍሪካ ሃገራት ጋር ባካሄዱት ስብሰባ ላይ ነበር።

ሊ ሻንግፉ ሥልጣን የያዙት ባለፈው መጋቢት ነው።

የኤሮስፔስ ኢንጂነሩ ጄኔራል ሊ የሥራ ዓለምን የተቀላቀሉት የሳተላይትና ሮኬት ውንጨፋ ማዕከል ነው።

ያለምንም ግርግር የቻይና ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ እርከንን ወደላይ ወጥተው ነው መከላከያ ሚኒስትር ለመሆን የበቁት።

በአውሮፓውያኑ 2018 የመከላከያ ሠራዊት የግምዣ ዕድገት ክፍል ኃላፊ ሳሉ ቻይና ከሩሰያ በገዛቻቸው ወታደራዊ አውሮፕላኖች እና መሣሪያዎች ምክንያት በዩናይትድ ስቴትስ ማዕቀብ ተጥሎባቸው እንደነበር ይታወሳል።

በያዝነው የአውሮፓውያኑ ዓመት መባቻ ሲንጋፖር በነበረ አንድ ስብሰባ ላይ የአሜሪካ አቻቸው ሎይድ ኦስቲንን አላገኝም ሲሉ አሻፈረኝ ብለዋል።

ሊ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኪን የፕሬዝደንት ዢ ጂንፒንግ ቀኝ እጅ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል።

ኪን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነታቸው የተነሱት ባለፈው ሐምሌ ሲሆን ሥልጣን ላይ የቆዩት ለሰባት ወራት ብቻ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩም በምን ምክንያት ከሠልጣን እንደተወገዱ ግልፅ ባይሆንም ዎል ስትሪት ጆርናል ምንጮቹን ዋቢ አድርጎ የአሜሪካ አምባሳደር ሳሉ ከትዳራቸው ውጭ ግንኙነት ጀምረው ነበር ሲል ዘግቧል።

ሁለት የኒውክሌር ጦር መሣሪያ አስተዳደር ባለሥልጣናት ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ነው በርካታ ሰዎች ከመንበራቸው ሊነሱ እንደሚችል የተወራው።

የሕዝባዊ ነፃ አውጭ ግንባር [ፒኤልኤ] ሮኬት ኃይል መሪ የነበሩት ጄኔራል ሊ ዩቻዎ እና ምክትላቸው “ከአደባባይ ከጠፉ” በኋላ ከመንበራቸው መነሳታቸው ተሰምቷል።