
ከ 4 ሰአት በፊት
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ባለው የሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ሲደረግ የነበረው የሦስተኛው ዙር ድርድር ማክሰኞ ማምሻውን በካይሮ መጠናቀቁን ኢትዮጵያ እና ግብፅ አስታወቁ።
ወደ መጠናቀቁ በተቃረበው ታላቁ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት እንዲሁም የውሃ አለቃቀቅ ደንቦችን እና መመሪያዎችን በተመለከተ የሦስትዮሽ ድርድር ባለፉት ሁለት ቀናት ግብፅ ካይሮ ላይ ሲካሄድ ቆይቷል።
ይህ የአሁኑ ድርድር ስምምነት ላይ ባልተደረሰባቸው የቴክኒካል እና የሕግ ማዕቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ የተሻለ ውጤት ላይ ለመድረስ ትኩረት የሚያደርግ መሆኑ ቀድሞ ተገልጾ ነበር።
የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ልዑካን መሪ አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በኤክስ (ትዊተር) ገጻቸው ላይ ሦስተኛው ዙር ድርድር ማክሰኞ ማምሻውን መጠናቀቁን ገልጸው፣ ቀጣዩን ድርድር በታኅሣሥ ወር አዲስ አበባ ላይ ለመቀጠል ከስምምነት መደረሱን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ የግብፅ የውሃ ሃብት እና የመስኖ ሚኒስቴር የሱዳን ልዑካንም ተሳታፊ ሆነው ለሁለት ቀናት የዘለቀው ድርድር ትናንት ማክሰኞ ጥቅምት 13/2016 ዓ.ም. መጠናቀቁን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ተደራዳሪ አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) “ድርድሩ መጠነኛ መሻሻል እና መግባባት” ታይቶበታል ብለዋል።
የግብፅ የውሃ ሃብት እና መስኖ ሚኒስቴር ቀጣዩን ድርድር በአዲስ አበባ ለማድረግ ከስምምነት ከመደረሱ ወጪ በድርድሩ የተገኘ ውጤት ስለመኖሩ ያለው ነገር የለም።
- አሜሪካ እስራኤልን ለመከላከል ምን ልታደርግ ትችላለች?ከ 5 ሰአት በፊት
- የጡት ካንሰርን እንዴት ማሸነፍ እንደሚቻል ምሳሌ የሚሆኑት ኢትዮጵያዊት እናትከ 4 ሰአት በፊት
- ጡረታ ከወጡ በኋላ አሁንም ሥራቸው ላይ የሚገኙት በጎ ፈቃደኛው ትራፊክ ፖሊስከ 5 ሰአት በፊት
ኢትዮጵያ ለ12 ዓመታት ገደማ ስትገነባው የቆየችው እና የካቲት 2014 ዓ.ም. በተወሰነ ደረጃ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የጀመረው ግዙፍ ግድብ ከግብፅ እና ከሱዳን ጋር ሲያወዛግባት ቆይቷል።
ለዓመታት ያህል በኢትዮጵያ፣ በግብፅ እና በሱዳን መካከል የሦስትዮሽ ድርድር ሲካሄድበት የቆየው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተመርቶ ውይይት ተደርጎበት ነበር።
በሦስቱ አገራት መካከል የነበረው የሦስትዮሽ ድርድር አፍሪካ ኅብረትን ጨምሮ በተለያዩ አሸማጋዮች እልባት እንዲያገኝ ቢሞከርም ሊቋጭ አልቻለም፤ አሁንም በእንጥልጥል ላይ ይገኛል።
ግብፅ በግድቡ ግንባታ ምክንያት ከአባይ ወንዝ የማገኘው የውሃ ድርሻ ይቀንስብኛል በማለት ከግድቡ ውሃ ሙሌት ጋር ተያያይዞ አሳሪ ስምምነት ሳይደረስ ሙሌት መከናወን የለበትም በሚል ስትሞግት ቆይታለች።
ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ግብፅ የቅኝ ግዛት ውሎችን ሙጥኝ በማለት ኢ-ፍትሃዊ እና አግላይ የሆነው ስምምነት ተቀባይነት እንዲያገኝ ጫና እያደረገች ነው በማለትም ትወቀሳለች።
ኢትዮጵያ በ2015 በመሪዎች ደረጃ በተፈረመው የመርሆች ስምምነት መሠረት አሁን የተጀመረው ድርድር በፍትሃዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም መርህ መሠረት ውጤት ላይ ለመድረስ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጻለች።
በአምስት ዓመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረው እና በአፍሪካ ትልቁ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫው የሕዳሴ ግድብ ግንባታው ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የወታበት ሲሆን፣ ሥራው ከ90 በመቶ በላይ ደርሶ ወደ መጠናቀቁ ተቃርቧል።