ፕ/ር ጋቢሳ ኤጄታ ሽልማቱን ከጆ ባይደን ሲቀበሉ
የምስሉ መግለጫ,ፕ/ር ጋቢሳ ኤጄታ ሽልማቱን ከጆ ባይደን ሲቀበሉ

ከ 3 ሰአት በፊት

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ብሔራዊ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ዘርፍ ሜዳልያ በዋይት ሀውስ ካበረከቱላቸው አንዱ ተመራማሪው ፕ/ር ጋቢሳ ኤጄታ አንዱ ናቸው።

ሽልማቱ የተሰጠው ባጠቃላይ ለ21 አሜሪካውያን ተመራማሪዎች ነው።

በሳይንስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የሚሰጥ ሽልማት ነው።

ከዘንድሮው ተሸላሚዎች መካከል አነስተኛ ገቢ ባላቸው አገራት ንጹህ የመጠጥ ውሃ በማቅረብ እንዲሁም በረሃን የሚቋቋሙ ዕጽዋት በማብቀል የላቀ ውጤት ያስመዘገቡ እንደሆኑ ባይደን ተናግረዋል።

“የምኖርበትን መንገድ የሚያሻሽሉ ግኝቶች ናቸው የተካተቱት። እንደ ካንሰርና ፓርኪንሰንስ ያሉ ሕመሞችን ለማከም አስተዋጽኦ ያበረከቱም ይገኙበታል” ብለዋል።

ኢትዮጵያዊ-አሜሪካዊው ፕ/ር ጋቢሳ የተሸለሙት በዕጽዋት ዘረ መል ምኅንድስና ሲሆን፣ የበረሃን የአየር ንብረት የሚቋቋሙ ዝርያዎች በማግኘታቸው ሽልማቱ ተበርክቶላቸዋል።

ይህ ግኝት የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጥ ነው ተብሏል።

ፕ/ር ጋቢሳ በአሜሪካ ኢንዲያና በሚገኘው ፕሪዲዩ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪ ናቸው። በዩኒቨርስቲው የዓለም አቀፍ ምግብ ዋስትና ክፍል ዋና ዳይሬክተር ናቸው።

በዕጽዋት ማርባት፣ በዕጽዋት ዘረ መል እንዲሁም ዓለም አቀፍ ግብርና ታዋቂ ናቸው።

ተሸላሚዎቹ በግኝታቸው ለሳይንሳዊ እመርታ መንገድ መክፈታቸውን ጆ ባይደን በዋይት ሀውስ ንግግራቸው ጠቅሰዋል።

“ሁላችሁም ተሸላሚዎች ስለ ጀግንነታችሁ እናመሰግናለን” ብለዋል።

ከተሸላሚዎቹ መካከል ከተለያዩ አገራት አሜሪካ የሄዱ ሳይንቲስቶች እንደሚገኙበት በመጥቀስም “አሜሪካ የሚገልጻት አንድ ቃል ቢኖር ዕድሎች ነው” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

ከእነዚህ ሳይንቲስቶች መካከል አንዱ ፕ/ር ጋቢሳ ኤጄታ ናቸው።

ፕ/ር ጋቢሳ ተወልደው ያደጉት ኢትዮጵያ ነው። በዓለም በዘረ መል ምርምር አሉ ከሚባሉ ባለሙያዎች ዋነኛ ተጠቃሽ ናቸው።

ፕ/ር ጋቢሳ ከዚህ ቀደም የዓለም ምግብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በዋናነት ምርምር የሚያደርጉት በማሽላ ላይ ነው።

አሜሪካ በሳይነስ ዘርፍ የመሪነት ሚና እንደምትጫወት ባይደን ተናግረዋል። ተሸላሚዎቹ የዚህ አካል እንደሆኑም በንግግራቸው ጠቅሰዋል።

“እዚህ የተገኛችሁት ተሸላሚዎች አሜሪካውያን ውጤት ሳይገኝ የሚረቱ ወይም ጥረት የሚያቆሙ እንዳልሆኑ ማሳያ ናችሁ” ሲሉ ባይደን በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ገልጸዋል።

ፕ/ር ጋቢሳ የዕጽዋት ዘረ መል፣ የዘረ መል ለውጥና ዘር ሐረግ በሚያጠናው ዘርፍ (Plant Genetics) ነው ምርምር የሚያደርጉት።

ሽልማቱ የተበረከተላቸው ድርቅ መቋቋም የሚችል የማሽላ ዝርያ በማዋቀር ነው።

“ለሚሊዮኖች የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጥ ግኝት ነው” በሚል በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።

ፕ/ር ጋቢሳ ኤጄታ ሽልማቱን ከጆ ባይደን ሲቀበሉ

በሳይንስና ፖሊሲ ዘርፍ እንዲሁም በምጣኔ ሀብት ማሻሻል ረገድ ፕ/ር ጋቢሳ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ለአርሶ አደሮች የተሻለ ሁኔታ መፍጠር የቻለ እንደሆነ ተገልጿል።

“አገራትን የሚያጠናክርም ነው” በማለት ስለ ምርምራቸው በዋይት ሀውሱ የሽልማት ሥነ ሥርዓት ተገልጿል።

እአአ በ2009 ‘ወርልድ ፉድ ፕራይዝ’ የተሸለሙት ማሽላን በማዳቀል ድርቅ እና አረም የሚቋቋም ለማድረግ ባደረጉት ምርምር ነበር።

ይህ ጥናታቸው ከሰሃራ በታች ባሉ አገራት በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለመመገብ ማስቻሉን ፕሪዲዩ ዩኒቨርስቲ በድረ ገጹ ላይ አስፍሯል።

“ውጤት መር ምርምር በማድረግ ነው የሚታወቁት። በታዳጊ አገራት ከ500 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን የሚመግበውን ማሽላ ድርቅ የሚቋቋም ማድረግ ችለዋል” ይላል ድረ ገጹ።

ማሽላ በምርት ወቅት ሊገጥመው የሚችለውን ችግር በመፍታት የተመጣጠነ ይዘት እንዲኖረው እንዲሁም ድርቅና ቅዝቃዜንም እንዲችል በማድረግ ምርምራቸው ይታወቃል።

ማሽላው ከአረም በተጨማሪ የዕጽዋት ሕመምን መቋቋም የሚችልም ነው።

ዘረ መላቸው የተሻሻለ የማሽላ ዓይነቶችን በአሜሪካ እንዲሁም በአፍሪካ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተመራማሪው አስችለዋል።