October 25, 2023

በደራ ወረዳ በሦስት ሳምንታ ውስጥ ከ300 በላይ ንጹሐን በሸኔ ታጣቂዎች ተገድለዋል ተባለ

(አዲስ ማለዳ) በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ቢያንስ ከ300 በላይ ሰዎች በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት በሽብርተኝነት በተፈረጀው “ኦነግ ሸኔ” ታጣቂ ቡድን መገደላቸውን፤ አዲስ ማለዳ ከአካባቢው ነዋሪዎች አረጋግጣለች፡፡

አንድ ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የደራ ወረዳ ነዋሪ፤ “በሦስት ሳምንታ ውስጥ ከ300 በላይ ንጹሐን በሸኔ ታጣቂዎች ተገድለዋል።” ያሉ ሲሆን፤ ይህ እርሳቸው ያላቸው ትክክለኛ መረጃ እንደሆነ በመግለጽ፤ የሟቾች ቁጥር ከዚህ ሊያሻቅብ እንደሚችል እርግጠኛ ሆነው ተናግረዋል፡፡

ኹኔታውን በቅርበት እየተከታሉ መሆኑን ያስረዱት እኚሁ ታማኝ ምንጭ፤ ከ80 በላይ የሟቾች ሥም ዝርዝር እንዳላቸውም ገልጸዋል፡፡

ሌሎች የወረዳው ነዋሪዎች በበኩላቸው ጥቃቱ የተከፈተው ከመስከረም 27/2016 ጀምሮ መሆኑን ገልጸው፤ እስካሁን (ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ) ድረስ ጥቃቱ እንዳቆመ አስረድተዋል፡፡

ባቡ ድሬ፣ አሙማ ገንዶ፣ ጁሩ ዳዳ፣ መንቃታ፣ ወሬ ገበሮና ሌሎችን ጨምሮ ከ20 በላይ ቀበሌዎች በታጣቂ ቡድኑ ቁጥጥር ሥር እንደሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል፡፡

በታጣቂ ቡድኑ የታገቱ ሰዎች እስከ 1 ሚሊዮን ብር እየተጠየቀባቸው እንደነበርና የከፈሉት እደተለቀቁ የገለጹት የዓይን እማኞቹ፤ ይሁን እንጂ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የተጠየቁትን ገንዝብ በመክፈል ያልቻሉ ታጋቾች እንደተገደሉ ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል፡፡

ጥቃት እየተፈጸበት ነው በተባለው ወረዳ ገና ቁጥራቸው በትክክል ያልታወቀ በርካታ ቤቶች እንደተቃጠሉ ከ10 ሺሕ በላይ ሰዎች እንደተፈናቀሉም ተነግሯል፡፡

ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪ በበኩላቸው፤ “በደራ ወረዳ ባሳለፍነው ሳምንት ከአንድ የቤተሰብ አባል ውስጥ፤ አንዲት የአምስት ወር ነፍሰጡር ሴትና ወንድሟ ለታጣቂ ቡድኑ በመወገን ባለቤታቸው በከፈተባቸው ውጊያ ተገድለዋል፡፡” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

“ግለሰቡ የአራት ልጆችና የአምስት ወር ነፍሰጡር ሚስታቸውን ገድለዋል” ያሉት ነዋሪው፤ የሟቿን እናት ጨምሮ ሌሎች ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸው በሕክምና ላይ እንደሚገኙ አዲስ ማለዳ ከሟች የቅርብ ቤተሰቦች ሰምታለች፡፡

ከደራ ወረዳ፤ ሰሜን ሸዋ ዞኑ እንዲሁም ከክልሉ ባስልጣናት ለጉዳዩ ምን ምላሽ እንዳላቸው የተደረገው ሙከራ ስልክ ለማምሳት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው አልተሳካም፡፡

ይሁን እንጅ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በደራ ወረዳ ታጣቂዎች እያደረሱት ነው የተባለውን ጥቃት በተመለከተ መረጃዎች እንደደረሱት ለአዲስ ማለዳ አረጋግጧል፡፡

ኮሚሽኑ በሰጠው ምላሽ ታጣቂዎች እያደረሱት ነው የተባለውን ጥቃት በተመለከተ ሪፖርት ደርሶናል፤ በጉዳዩ ዙሪያ ክትትል እናደርጋለን ሲል ገልጿል።