በኦሮሚያ ክልል ግጭት በተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ተፈናቅለዋል ተባለ
(አዲስ ማለዳ) በኦሮሚያ ክልል ግጭት በተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች መፈናቀላቸውን ሴንተር ፎር ዴቭሎፕመንት ኤንድ ካፓሲቲ ቢዩልዲንግ (CDCB) አስታወቀ።
ድርጅቱ በክልሉ ስላለው ኹኔታ አስመልክቶ ባወጣው ሪፖርት፤ “በክልሉ እየተካሄደ ያለው ግጭት ካስተለው መፈናቀል በተጨማሪ፤ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል እንዲሁም የልማት እንቅስቃሴዎች ተቀዛቅዘዋል” ያለ ሲሆን፤ የሕዝቡም ማህበራዊ ትስስር መሸርሸሩን ጠቁሟል፡፡
ድርጅቱ አደረኩት ባለው ጥናት መሰረት በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ ክልል 1 ሚሊየን 292 ሺሕ 323 ሰዎች ተፈናቅለዋል ያለ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ 374 ሺሕ 400 ወይንም 29 በመቶ የሚሆኑት ብቻ በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ገልጿል፡፡
የተቀሩት 71 በመቶ የሚሆኑት ተፈናቃዮች ደግሞ በማህበረሰቡ ውስጥ ተበታትነው እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ በዩኤስኤይዲ ትብብር ባዘጋጀው በዚህ ሪፖርት፤ በተለይም በምስራቅ ወለጋ እና ምዕራብ ወለጋ ያለው ኹኔታ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን የተገለጸ ሲሆን፤ ከአጠቃላይ ተፈናቃዮች ውስጥ 859 ሺሕ ወይንም 66 በመቶ የሚሆኑት ከኹለት ዞኖች ብቻ የተፈናቀሉ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም በክልሉ ያለው ግጭት በትምህርት ላይ ያመጣውን ተፅዕኖ በዝርዝር ያስቀመጠው ሪፖርቱ፤ በክልሉ 739 ትምህርት ቤቶች መዘጋታቸውን እንዲሁም ከ210 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ውጪ መሆናቸውን ገልጿል።
1 ሺሕ 117 መምህራንና የትምህርት ባለሙያዎች ከሥራቸው ገበታቸው ውጪ መሆናቸውንም ጨምሮ አመላክቷል፡፡
በተጨማሪም ድርጅቱ ከክልሉ ጤና ቢሮ አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት፤ ግጭት በተቀሰተባቸው አካባቢዎች የሚገኙ 208 ጤና ተቋማት ሙሉ በሙሉ፣ እንዲሁም 788 የሚሆኑት ደግሞ በከፊል መውደማቸው መገለጹን አዲስ ማለዳ ከሪፖርቱ ተመልክታለች፡፡
በዚህም 10 አምቡላንሶች መዘረፋቸውን፣ 45 የሚሆኑት መቃጠላቸውን እንዲሁም 25 ደግሞ ከአገልግሎት ውጭ መሆናቸው የተነገረ ሲሆን፤ በተጨማሪም 2 ሞተር ሳይክሎች መዘረፋቸውን፣ 5 የሚሆኑት ከአገልግሎት ውጭ መሆናቸውን እንዲሁም፤ 80 የሚሆኑት ደግሞ መቃጠላቸውን ገልጿል፡፡
“በምዕራብ ኦሮሚያ ወረዳዎች እና መካከለኛው አካባቢዎች በመንግሥት እና በክልሉ በሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች መካከል የሚስተዋለው ግጭት፤ እንዲሁም በተለይ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በፋኖ ታጣቂ ቡድን የሚደረሰው ጥቃት ውድመት አድርሷል” ሲልም ሪፖርቱ ገልጿል።
በተጨማሪም “ግጭት በተቀሰቀሰባቸው አካባቢዎች ማህበራዊ ደንቦች ተሽረዋል፣ ማህበራዊ ተቋማት ወድመዋል፤ ጭካኔ እና ሕገወጥነት የተለመደ ሆኗል።” ያለው ሪፖርቱ፤ “ለዚህም በጥቅምት ወር 2015 በምዕራብ ወለጋ ዞን ሳሲጋ ወረዳ በገሎ ቀበሌ በመካነ ኢየሱስ ቤተ ክርሰቲያን ውስጥ፤ፐለአምልኮ በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት የ14 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ማረጋገጫ ነው።” ሲል ገልጿል።
ሴንተር ፎር ዴቭሎፕመንት ኤንድ ካፓሲቲ ቢዩልዲንግ (CDCB) በሪፖርቱ በክልሉ የሚስተዋሉት ግጭቶች በተለይ ሴቶች እና ሕጻናትን ለአደጋ የጣሉ መሆናቸውን የገለጸ ሲሆን፤ ቤተሰቦቻቸውን በድንገት የሚያጡ ሕጻናት ቁጥር እየጨመረ መሆኑን አስታውቋል። በተጨማሪም ባለቤቶቻቸው የሞቱባቸው ሴቶች ለዝርፊያ፣ ለአስገድዶ መድፈ እና ለተለያዩ አካላዊ ጥቃቶች እየተጋለጡ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
ስለሆነም በክልሉ የወደሙ መሰረተ ልማቶቸ እንዲስሩ ለአርሶ አደሮች ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል ያለው ድርጅቱ፤ በተዋጊዎች መካከል በአስቸኳይ ሰላም እንዲወርድም በሪፖርቱ ጠይቋል።
ለደረሰውም ውድመት ከክልሉ፣ ከፌደራል መንግሥቱና ከግብ-ሰናይ ተቋማት አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።
