ለጥንቃቄ
በ ” ፌስቡክ ” እንደልብ በሚተዋወቁ መልዕክቶች ምክንያት በርካታ ወጣቶች ውድ ጊዜያቸውን እና ገንዘባቸውን እየተባሉ እየተጭበረበሩ ነው።
” ፌስቡክ ” ላይ ግለሰቦች ክፍያ ከፈፀሙ ” Sponsored ” የሆኑ መልዕክቶችን ብዙ ሺህ ተጠቃሚዎች ጋር ያደርሳሉ።
ተቋሙ ገንዘብ እየተቀበለ የማያሰራጫቸውን መልዕክቶች ትክክለኝነት እያረጋገጠ ይሁን አይሆን የሚታወቅ አንዳች ነገር ባይኖርም በርካቶች ግን በሀሰተኛ መልዕክቶች ወጣቶች እየተጭበረበሩ ይገኛሉ።
ከሰሞኑን ስለ ” ሀሰተኛ የትሬድ ስራ ” እና በዛ ምክንያት ገንዘባቸው ተበልቶ እና መፍትሄ አጥተው ስለተቀመጡ ሰዎች ዳሰሳ መስራታችን ይታወሳል።
ለዛሬ ደግሞ በተመሳሳይ መልክ ስለሚደረግ ማጭበርበር በአጭሩ እንመለከታለን፤ ይኸውም ዋና ዓላማቸው ስራ የሌላቸውን ወጣቶች እና ሌሎች የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን በሀሰተኛ መልዕክቶች አታሎ ገንዘባቸውን ማጭበርበር ነው።
በፌስቡክ ላይ ስፖንሰር በሚሆን መልዕክት ”
– ስራ የሌላችሁ ስራ እንቀጥራችኃለን፣
– በቀን ውስጥ ከ20 ሺህ ብር በላይ ትሰራላችሁ ፣
– በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥሩ ገንዘብ በማግኘት የራሳችሁን ስራ ትጀምራላችሁ ” የሚሉ የማጭበርበሪያ መልዕክቶች በስፋት ሲሰራጩ ተመልክተናል።
ወጣቶች እነዚህን አካላት ለዚሁ ጉዳይ በሚያናግሯቸው ጊዜ በቅድሚያ የምዝገባ ገንዘብ ይጠይቋቸዋል፤ በኃላም የውሃ ሽታ ይሆናሉ።
የወጣቶችን ስራ ማጣት እንደ አጋጣሚ ተጠቅመው ከሌላቸው ገንዘብ ላይ ለመንጠቅ የሚሰሩት እነዚህ አስነዋሪ አጭበርባሪዎች መልዕክታቸውን ተደራሽ ለማድረግ የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎችን የሚጠቀሙ ቢሆንም በይበልጥ የተከፈለባቸው የ ” ፌስቡክ ” መልዕክቶች ዋነኛዎቹ ናቸው።
ምን ጥንቃቄ ማድረግ አለብን ?
– አንድ የስራ ማስታወቂያ ስንመለከት ስራው የት እንደሆነ ? የቢሮው አድራሻ ? ህጋዊነቱን የሚያሳይ ማስረጃ ? መጠየቅ አለብን።
– ” ስራ ለመቀጠር ብር ክፈሉ ” የሚሉ ዘራፊዎችን ለምን ? ብሎ ማፋጠጥ ፤ እንዲሁም ስልካቸውን እና አድራሻቸውን መመዝገብ ይገባል።
– አንድ ስራ በቀን 100 ሺህ ፣ 50 ሺህ ብር ይከፈልበታል ሲባል እንዴት ? በምን መልኩ ? ምን ተሰርቶ ? በየትኛው ህጋዊ መንገድ ብሎ መጠየቅ እና መጠራጠር ይገባል።
በ ” ፌስቡክ ” ወይም በ ” ቴሌግራም ” ላይ የማረጋገጫ ምልክት ያላቸው ሰዎች ሁሉ እውነተኛ ናቸው ብላችሁ እንዳታምኑ፤ እነዚህ ምልክቱን ገዝተው መጠቀም ይችላሉና።
ከምን በላይ በተለይ ” ፌስቡክ ” በክፍያ የሚያስተላልፋቸውን መልዕክቶች ትክክለኝነትን የሚያረጋግጥበትን መንግድ መዘርጋት ካልቻለ ትልቅ ቀውስ መፍጠሩን ይቀጥላል።
ማንኛውም ሰው ተነስቶ ለፌስቡክ የመክፈያ መንገድ ካበጀ ፤ ዜሮ ተከታይ ቢኖረም ፤ ህገወጥ ዝርፊያ ላይ የተሰማራ ቢሆንም እስከከፈለ ድረስ ማስረጃ የሌለው መልዕክት ሊያሰራጭ ይችላል።
በተለይም በርካታ ወጣቶች ስራ ፈላጊ በመሆናቸው ስራ ያላቸው ዜጎችም ከሚያገኙት ገቢ የተሻለ ለማግኘት ሲሉ እነዚህን አካላት ያነጋግራሉ። የሚጠየቁትን ገንዘብም ክፈሉ ሲባሉ ሊከፍሉ ይችላሉ።
አንደንዶች ደግሞ በፌስቡክ የክፍያ መልዕክት የሌላቸው እና የማይሸጡትን ዕቃ በማስተዋወቅ ሰዎችን ገንዘብ ካስላኩ በኃላ የውሃ ሽታ ሆነው ይቀራሉ።
” ፌስቡክ ” አሰራሩን ማስተካከል ካልቻለና ገንዘብ እየሰበሰበ ብቻ በትንሽ ዶላር ብዙሃን ጋር ያልተረጋገጡ መልዕክቶችን የሚያሰራጭ ከሆነ በተዘዋዋሪ ቁጥጥር ባለማድረጉ በተጠቃሚዎች ላይ ለሚደርሰው ድርጊት ኃላፊነት ሊውስድ ይገባል።
ከምንም በላይ ግን ተጠቃሚዎች እንዲሁም ውድ ቤተሰቦቻችን እራሳችሁን ከአጭበርባሪዎች ጠብቁ።
Tikvah Ethiopia
