October 25, 2023 – BBC Amharic
ኢትዮጵያ ወደ ሕዋ የላከቻቸው ሳተላይቶች ሥራ አቆሙ።
ለመሬት መልከታ ሥራ ወደ ሕዋ የተላኩት ሳተላይቶች የአገልግሎት ጊዜያቸው በመጠናቀቁ ሥራ ማቆማቸውን የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጆኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት ገልጿል።

ወደ ሕዋ የሚላኩ ሳተላይቶች የቆይታ ጊዜ (ሕዋ ላይ የሚቆዩበት) ቀድሞ የሚታወቅ መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ የመጀመሪያ የሆነችውን Ethiopian Remote Sensing Satellite – 01 (ETRSS – 01) የተሰኘች 70 ኪሎ ግራም የምትመዝን ሳተላይት ታኅሣሥ 10/2012 ዓ. ም. ከቻይና ማምጠቋ ይታወሳል።
ይህች ሳተላይት ለግብርና፣ ለማዕድን፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለአየር ንብረት ጥበቃ እና ለመልከዓ ምድር ጥናት የመረጃ አገልግሎትን ስትሰጥ የቆየች ሲሆን ከተያዘላት ቀነ ገደብ ተጨማሪ 9 ወራት ሰርታለች ተብሏል።
ከ ETRSS – 01 መምጠቅ ከአንድ ዓመት በኋላ ተመሳሳይ አገልግሎት የምትሰጥ ET-Smart-RSS ሌላ ሳተላይትም ማምጠቋ ተዘግቦ ነበር።
ሳተላይቶቹ መጨረሻቸው ምን ይሆናል?
ኢትዮጵያ ወደ ሕዋ የላከቻቸው የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች ከመሬት ያላቸው ከፍታ 628 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው። ይህም የመሬት ስበትን ለመቋቋም እንዳይችሉ ስለሚያደርጋቸው እድሜያቸው አጭር ነው።
የሳተላይቶቹ ስሪትም በረዥም ጊዜ በራሳቸው ተሰባብረው ወደ ጥቃቅን ስብርባሪ እንዲቀየሩ ተደርገው ስለተሰሩ “በ15 እና 20 ዓመት ወደ ጥቃቅን ስብርባሪ ተቀይረው ይጠፋሉ።” ሲሉ አቶ አብዲሳ ያስረዳሉ።
አሁን ላይ ከሌሎች አገራት ሳተላይቶች መረጃ እየተቀበሉ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በዚህም ምክንያት የሚፈጠር ክፍተት አይኖርም ብለዋል።
በቀጣይ ሁለት ዓመታት ኢትዮጵያ ለተመሳሳይ ዓላማ የሚውል ሌላ የበለጠ የጥራት ደረጃ ያለው ሳተላይት ለማምጠቅ ዝግጅት ላይ መሆኗን አቶ አብዲሳ ተናግረዋል።
ስለ ኮሚኒኬሽን ሳተላይት አቶ አብዲሳ ምን አሉ?
ከመሬት ምልከታ ሳተላይት በተጨማሪ ኢትዮጵያ የኮሚዩኒኬሽን ሳተላይት የማምጠቅ ፍላጎት እንዳላት የገለጹት አቶ አብዲሳ፦
“የአዋጭነት ጥናት አካሂደን አዋጭነቱን ተመልከተናል። ፍላጎቱም አለ። ከፋይናንስ አንጻር የኮሚዩኒኬሽን ሳተላይት የሚያስፈልገው ወጪ ከፍተኛ ስለሆነ ፋይናንሱ በሚገኝበት ወቅት አልምቶ ጥቅም ላይ ለማዋል ዝግጅት አለን” ብለዋል።
የኮሚኒኬሽን ሳተላይቶች እስከ 15 ዓመት አገልግሎት እየሰጡ ሊቆዩ ይችላሉ። እነዚህ ሳተላይቶች ወደ 36 ሺህ 500 ኪሎ ሜትር ርቀው ነው የሚቀመጡት። በዚህ ቦታ የመሬት ስበት አነስተኛ ስለሆነ ብዙ ዓመት የማገልገል አቅም አላቸው።
Credit : BBC Amharic
