‹‹አሰብ የማን ናት?›› መቄዶንያ የአረጋውያን ማእከልን ኢሕአዴግ ጥርስ ውስጥ ያስገባው የመጽሐፍ ስጦታ
በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን.)
እንደ መንደርደሪያ፤
‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው!›› በሚል መርሑ/ፍልስፍናው የሚታወቀው መቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ሕሙማን ማእከል፤ ሰው ከፈጣሪው/ከአምላኩ ዘንድ የተቸረውን ዘላለማዊ ፍቅር፣ ሰው የመሆን ክብሩንና የመንፈስ ልእልናውን ከፍ የሚያደርግ ስለ ሰው የተቋቋመ ነው፡፡ ይህ ስለ ሰው የተቋቋመ ድርጅት በአጭር ጊዜ ውስጥ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ትልቅ ተቀባይነትንና የክብር ስፍራ እንዲያገኝ ያደረገውም ይኸው በቃልም በተግባርም የተገለጸ ሰብአዊነትን ማእከል ያደረገ የፍቅር፣ የበጎነት ሥራው ነው፡፡

የማእከሉ መስራች ቢንያም በለጠ ደጋግሞ እንደሚለው መቄዶንያ፤ ‹‹ወገን ቢረዳዳ ችግርም አይጎዳ፤ ጋን በጠጠር ይደገፋል፤ ኀምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለኀምሳ ሰው ጌጡ ነው፤›› በሚሉት የኢትዮጵያውያን ዘመናትን በተሻገረው የመረዳዳት፣ የመተጋገጋዝ፣ የመደጋጋፍ ባህልን በተግባር ያሳየ ነው፡፡ የራሳችንን ችግር ራሳችን መፍታት እንችላለን፤ ‹ወገን ቢረዳዳ ችግርም አይጎዳ፤› እንደሚባለው በርግጥ ከተረዳዳን አሉብን የምንላቸው ማኅበራዊ ችግሮቻችን ከእኛ አቅም በላይ አይደሉም በሚል ጽኑ እምነት ሁሉን አቀፍ የሆነ ትልቅ የበጎነት ማኅበራዊ ንቅናቄን ለመፍጠር ተችሎታል፡፡
የዚህ ማኅበራዊ ንቅናቄው አካል የሆነው ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት ያደረጋቸው ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል ያሳተፈ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ነው፡፡ መቄዶንያ ያለበትን የቦታ ጥበት ለመቅረፍና እንዲሁም በመጦሪያ ዘመናቸው የጎዳናው ወድቀው ያሉ አረጋውያንን ለመደገፍ፣ እንክብካቤና የሕክምና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን የአእምሮ ሕሙማንን ወደማእከሉ ለማስገባት የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶችን አድርጎ ነበር፡፡
ከእነዚህ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች መካከል ደግሞ ከጥቂት ዓመታት በፊት በግሎባል ሆቴል ያደረገው የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት አንዱ ነበር፡፡ ይህ በግሎባል ሆቴል የተካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በርካታ ኢትዮጵያውያን በገንዘባቸው፣ በሙያቸው፣ በጉልበታቸውና በሐሳባቸው የተሳተፉበት ከክልል ከተሞች ሳይቀር በዝግጅቱ ቦታ በመታደም በጎነታቸውና ቅንነታቸውን ያሳዩበት መድረክ ነበር፡፡ ከአዳማ፣ ከቢሾፍቱና ከሌሎች ከተሞች አውቶቡስ ተከራይተው በርካታ ወገን ወዳድ ኢትዮጵያውያን ፍቅራቸውንና ለወገኖቻቸው ያላቸውን በጎነት ከቃል ባለፈ በተግባር ጭምር ለመግለጽ የተመሙበት ደማቅ ዝግጅት ነበር፡፡
ታዲያ በዚህ በግሎባል ሆቴል በተዘጋጀው የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ላይ ከታደሙ ታላላቅ ኢትዮጵያውያንን መካከል፤ አረጋዊው ምሁርና የአገር ባለውታ፣ ነፍሰ ኄር ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም፣ ዕውቁ የዓለም አቀፍ ሕግ ምሁር ፕ/ር ያዕቆብ ወ/ማርያም ይገኙበታል፡፡ በዝግጅቱ ላይ ገንዘብና በዓይነት ድጋፍ ያደረጉ በሚገርም ሁኔታ ሌላው ሳይቀር ቤታቸውን ለመቄዶንያ የተናዘዙ ኢትዮጵያውያን ወገኖችም ነበሩ፡፡
ታዲያ በዚህ ዝግጅት ላይ በተለየ መንገድ ፕ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም፤ ‹‹አሰብ የማን ናት›› በሚል ርእስ ለንባብ ያበቁትን አነጋጋሪ የሆነ መጽሐፋቸውን አንድ ሺሕ ኮፒ ተሸጦ ለማእከሉ የገንዘብ ድጋፍ ይሆን ዘንድ በስጦታ አበረክተው ነበር፡፡ ከስጦታቸው ባሻገርም ባላቸው አቅም ሁሉ ከመቄዶንያ ጎን እንደሚቆሙ ቃል ገቡ፡፡ ታዳሚዎች ስጦታቸውንና ንግግራቸውን በደማቅ ጭብጨባ ተቀበለው፡፡
የመድረኩ አጋፋሪዎች የነበሩት (ገጣሚ አበባው መላኩና አስናቀ) በኢትዮጵያዊ የአክብሮት ባህል አዛውንቱ ምሁር ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም ንግግር እንዲያደርጉና የመቄዶንያ ባለውለታዎችን እንዲሸልሙ እና የእውቅና ሰርተፊኬት እንዲያበረክቱ ወደ መድረክ ጋበዟቸው፡፡ ነፍሰ ኄር/የኔታ ፕ/ር መስፍን በንግግራቸው መካከልም እንዲህ አሉ፤
‹‹… የዘመናችን ሙሰኞችና አልጠግብ ባዮች የአገርን ገንዘብና ሀብት ወደ ውጪ ሲያሸሹ፣ ልጆቻቸውንና ዘመዶቻቸውን በሀገር አንጡራ ሀብት በአሜሪካና በአውሮፓ ሲያመነሸንሹ እንደ ቢንያም ያሉ ሰው የሆኑ ታላቅ ኢትዮጵውያን ደግሞ የሕዝባችን ችግር ችግራችን፣ ሰቆቃቸው ሰቆቃችን ነው በሚል የብዙዎች የቀንና የሌሊት ሕልም ከሆነችው አገረ-አሜሪካ ድረስ መጥቶ ወገኑን ያገለግላል…፤››
ፕሮፌሰር መስፍን በማግሥቱም ይህን ንግግራቸውን በማኅበራዊ ትስስር መድረካቸው አጋሩት፡፡ ታዲያ ይህ የፕ/ር ያዕቆብ፤ ‹‹አሰብ የማን ናት የመጽሐፍ ስጦታና ፕ/ር መስፍን ያደረጉት ሸንቋጭ ንግግር ለኢሕአዴግ ሰዎችና ለደጋፊዎቻቸው ብዙም አላስደሰተም ነበር፡፡ እንደውም መቄዶንያ በበጎ ፈደቃደኝነት ስም በስውር በቅንጅትና ሰማያዊ ፓርቲ አባላት ተጠልፏል ወደሚል ክስ ተሸጋገረ፡፡ የገቢ ማሰባበሲያ ዝግጅቱ ኮሚቴ አባላት በነበርነው በጎ ፈቃድ አገልጋዮች ላይም በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ክትትል ማድረግ ያዙ፡፡
ታሪኩን ለማሳጠር ያህልም፤ ከዚሁ ከግሎባል የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በኋላ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ለመቄዶንያ ማእከል ግንባታ ይውል ዘንድ በስጦታ የሰጠውን 30 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ለመረከብ፣ ምስጋና ለማቅረብና ለግንባታው የሚሆን ድጋፍ ለማሰባሰብ ሲባል በሚሊኒየም አዳራሽ ታላቅ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ለማድረግ ዝግጅት ተጀመረ፡፡
ይህን ዝግጅት የተሳካ ለማድረግ በፊት ከነበረነው የኮሚቴ አባላት የተወሰንን ሰዎች በዚሁ ዝግጅት ላይ መሳተፍ ጀመርን፡፡ ስለ ዝግጅቱ መገናኛ ብዙኃን፣ ታዋቂ ሰዎችና አርቲስቶች የተሳተፉበት የማስተዋወቅና የቅስቀሳ መድረክ በሰፊው ተካሄደ፡፡
የአዲስ አበባ ታክሲዎች፣ አንበሳ የከተማ አውቶቡስ፣ የቤት መኪናዎች፣ ካፌዎች፣ የንግድ ድርጅቶች… ስለ መቄዶንያ የሚሊኒየም የገቢ ማሰባሰቢያ በአንድ ድምፅ ከፍ ያለና ስኬታማ የሆነ የማስተዋወቅና የቅሳቀሳ ሥራ ላይ ተጠመዱ፡፡ በወቅቱ ኢሕአዴግ/መንግሥት በቃል እንጂ በተግባር ዕውን ማድረግ ያልቻለው ከፍተኛ የሆነ ሕዝባዊ የንቅናቄ መድረክ ነበር መቄዶንያ መፍጠር የቻለው- ሊያውም በኢትዮጵዊነት የአንድነትና የመረዳዳት መንፈስ፣ ሰው በመሆን ክብርና ፍቅር ውስጥ የተወለደ ታላቅ ሕዝባዊ ንቅናቄ ነበር ማለት ይቻላል!!
ታዲያ ይህን ዝግጅት ለማድረግ የሳምንት ያህል ዕድሜ ሲቀረው ከመንግሥት የፀጥታ የደኅንነት ኃይሎች ለመቄዶንያ እንዲህ የሚል ማሳሰቢያና ቀጭን ትእዛዝ ደረሰው፡፡ ‹‹በከተማው ውስጥ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ይህን ዝግጀቱን ማድረግ አትችሉም፤›› ነገሩ በግሎባሉ የገቢ ማሰባበሲያ ወቅት፤ ‹በአሰብ የማን ናት› የመጽሐፍ ስጦታና በፕ/ር መስፍን ንግግር ቅሬታና ጥርጣሬ ያደረበት መንግሥት ይህን የሚሊኒየሙን ዝግጅት በዋዛ ሊያልፈው አልፈለገም ነበርና ነው እንዲህ ዓይነቱን ቀጭን ትእዛዝ ማስተላለፉ፡፡
ለመንግሥት ስለሁኔታው ለማስረዳት በአካልና በስልክ ሙከራ ተደረገ ግን እምብዛም ውጤት አላስገኘም፡፡ በወቅቱም ኢሕዴግ ላይ ሕዝባዊ ቁጣውና መነሳሳቱ እየተጠናከረ የሄደበት ጊዜ ነበርና መንግሥት ዝግጅቱን ክፉኛ ተጠራጠረው፡፡ ብዙ የተለፋበት ዝግጅት በእንዲህ ዓይነቱ አጣብቂኝ ውስጥ መውደቁ የበዓሉ ዝግጅት ኮሚቴ አባላትን ውጥረትና ጭንቀት ውስጥ ከተተን፡፡ በመጨረሻም አንድ ውሳኔ ላይ ተደረሰ፡፡ ይኸውም፤ በወቅቱ ለስብሰባ አዳማ የነበሩትን የፀጥታና ደኅንነት ሹም ለማነጋገር ከኮሚቴዎች መካከል እኔ፣ አሁን በአዋሽ አርባ የሚገኘው ሀብታሙ አረጋ እና ሌሎች አባላት ሆነን ወደ አዳማ ጉዞ ጀመርን፡፡
ልክ ዱከም ከተማ ላይ ስንደረስ ከዶ/ር ብንያም ስልክ ተደወለ፡፡ መንግሥት ዝግጅቱ እንዲካሄድ ጊዜያዊ ፈቃድ ሰጥቷልና ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ አለን፡፡ በግማሽ ደስታና ጥርጣሬ ውስጥ ሆነን ወደ አዲስ አበባ ተመለስን፡፡ ኢሕአዴግ ከእኛ/ከበዓል ዝግጅቱ ኮሚቴዎች የመርሐ-ግብሩን ዝርዝር ክንውኖች እንድናስረክባቸውና ዝግጅቱን የሚመሩ ሰዎችን መንግሥት ራሱ እንደሚመድብ ተነገረን፡፡ በዚህም መሠረት የሚሊኒየሙ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅትም በመንግሥት እይታ ስር ሆኖ እንዲካሄድ ሆነ፡፡
እንደ መውጫ
ከሰሞኑን ከመንግሥት ዘንድ የቀይ ባሕር ጉዳይ የህልውናችን መሠረት ነው በሚል የተሰጠው ማብራሪያ በአንዳንዶች ዘንድ የመወያያ አጀንዳ ሆኗል፤ በኤርትራ በኩልም የቀይ ባሕርን ጉዳይ ባታነሱት ይሻላችኋል የሚመስል ስሜትን ያዘለ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡ የሆነስ ሆነና ኢትዮጵያ ቀይ ባሕር ትናንትና በታሪክ የነበራቸውን ቁርኝት በተመለከተ አንድ ሁለት የታሪክ አጋጣሚ ለወጋችን መቋጫ ሆነን ዘንድ ለማንሳት ወደድኹ፡፡
ከሁለት መቶ ዓመታት ገደማ በፊት የትግራይ መኳንንት የነበሩት ደጃዝማች ሰባጋዲስ ወደብን/ቀይ ባሕርን በተመለከተ እንዲህ ሲሉ ተናግረው ነበር፡፡ ‹‹ወደብ ለአንድ ሀገር እስትንፋስ ነው፡፡ ወደብ የሌለው ሀገር ሳምባ እንደሌለው ሰው ይቆጠራል፡፡›› እኚህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ የወደብን ጥቅም የተረዱና ያጠኑ ነበሩ፡፡ ‹‹ይህ ባሕር ጉሮሯችን ስለሆነ ጠላት እንዳይደፍረው መጠበቅ አለብን፤ ብሞት እንኳን እዚሁ ቀይ ባሕር ዳርቻ ቅበሩኝ ካልሆነ ደግሞ ፊቱን ወደ ቀይ ባሕር አድርጋችሁ ቅበሩኝ” ብለው ተናግረዋል፡፡
ደጃዝማች ሳባጋዲስ የአከባቢው ባላባቶች ለሆኑት የናይብ ተወላጆች ሹመትና ሽልማት እየሰጡ፡ የጋብቻም ትስስር እያደረጉ ያን ጊዜ በነበሩ በኢትዮጵያ ወደቦች በምጽዋና በኢድ እየተጠቀሙ ንግድ እንዲስፋፋ የአከባቢው ጸጥታና ሰላም እንዲጠበቅ አድርገዋል፡፡ ለኤርትራ ሕዝብም ሕግና ሥርዓት አውጥተው በሰላምና በደስታ ይኖር ስለነበር የደጃዝማች ሰባጋዲስ አስተዳደር ይመስገን ስለነበር “ወርቃማ ጊዜ” በሚል ቅጽል ለ14 ዓመታት ኤርትራን በትግራይ ትግርኝ ውስጥ አስተዳድረዋል፡፡
እናም ደጃዝማች ሰባጋዲስ እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜም ለቀይ ባሕር እንደተሟገቱ የባሕር ወሰናችንን የትኛው የጎበዝ ነው የሚደፍረው?! በማለት የሀገራችን ወሰን እንደ ዓይናቸው ብሌን ሲያዩትና ሲሳሱለት ኑረው እንዳለፉ በታሪክ ተጽፎላቸዋል፡፡
ሰላም ለኢትዮጵያ! ሰላም ለምድራችን!
