አሜሪካ ሁለት የጦር ጄት ተሸካሚ መርከቦችን አስጠግታለች
የምስሉ መግለጫ,አሜሪካ ሁለት የጦር ጄት ተሸካሚ መርከቦችን አስጠግታለች

25 ጥቅምት 2023, 07:19 EAT

አሜሪካ እና እስራኤል፣ እስራኤል እና አሜሪካ፤ አንቺ ትብስ አንተ ትብስ መባባለቸው ሁለት አገር መሆናቸውን ያስረሳል። ወዳጅነታቸው ጥብቅ ነው።

ጆ ባይደን በድርጊትም በንግግርም ይህን አሳይተዋል፤ ገልጸውታልም።

በድርጊት የጦር ጄት የሚሸከሙ መርከቦችን ወደ ሜዲትራኒያን ባሕር በማስጠጋት፣ በቃል ደግሞ ቴል አቪቭ ተገኝተው ደግሞ እስራኤልን “በማንኛውም ሁኔታ ከጎንሽ ነን” በተደጋጋሚ ብለዋል።

“አሁን ያለውን ሁኔታ ተጠቅሞ በዚህ ጦርነት እጁን ለማስገባት ለሚሻ አንድ ማሳሰቢያ አለኝ፤ ‘እንዳይሞክረው’” ብለው ነበር ባለፈው ሳምንት።

ይህ ማስጠንቀቂያ የተወረወረው ለኢራን እንደሆነ ለማወቅ ፖለቲካ መተንተን አይጠይቅም።

በቅርብ ቀናት የአሜሪካ ወታደሮች በሶሪያ እና በኢራቅ ጥቃት ደርሶባቸዋል። ፔንታጎን እንደሚለው ከሆነ አሜሪካ ከየመን የተተኮሰ ሚሳኤል በቀይ ባሕር ሰማይ ላይ አምክናለች።

ሚሳኤሉ እየተምዘገዘገ የነበረው ወደ እስራኤል ነው።

ባይደን በሺህ የሚቆጠሩ አሜሪካውያን ወታደሮች በተጠንቀቅ እንዲሆኑ አዘዋል። ይህም በመካከለኛው ምሥራቅ ያልተጠበቀ ነገር ቢፈጠር ወደዚያው ለመዝመት ነው።

አሜሪካ ለእስራኤል ጦር ሠራዊት ከፍተኛውን የገንዘብ ድጋፍ ታደርጋለች። በየዓመቱ በአማካይ 3.8 ቢሊዮን ዶላር ትለግሳለች።

አሁን በጋዛ ቀን ተሌት ቦምብ የሚጥሉት ጄቶች አሜሪካ ሠራሽ ናቸው።

ሐማስ የሚተኩሳቸውን ሮኬቶች በአየር ቀልበው መና የሚያስቀሩት ‘አይረን ዶም’ የተባሉት ፀረ ሮኬት መሣሪያዎች በአሜሪካ ድጋፍ ነው የተመረቱት።

እነዚህን ውስብስብ ጦር መሣሪያዎች አሜሪካ ወደ እስራኤል ደጋግማ የምትልካቸው እስራኤል ጥያቄ እንኳ ሳታቀርብ ነው።

ባለፈው ዐርብ የአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት 105 ቢሊዮን ዶላር ወታደራዊ ወጪ ሲያጸድቅ 14 ቢሊዮን ዶላሩ አሁኑኑ ለእስራኤል የሚሰጥ እንደሆነ ባይደን ጠቅሰዋል።

ይህ ከፍተኛ ገንዘብ በሕግ መወሰኛው ምክር ቤት በጸደቀ በማግስቱ ፔንታጎን እጅግ ውስብስብ የሚባለውን ፀረ ሚሳኤል ሥርዓት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ልኳል። በምጽህጻሩ ታድ (THAAD) ይባላል። ተርሚናል ሃይ አልቲቲዩድ ኤሪያ ዲፌንስ ማለት ነው።

ይህ ሁሉ የሚነግረን አሜሪካ በእስራኤል ጉዳይ ሚናዋን መለየቷን ነው። ለእስራኤል የምትቆጥበው ጉልበትም፣ ገንዘብም፣ የጦር መሣሪያም የለም።

ይህን ብንልም ታዲያ ነገሮች በመካከለኛው ምሥራቅ ኢራን እንዳስጠነቀቀችው ከቁጥጥር ውጪ ቢወጡ አሜሪካ በቀጥታ ጦርነቱ ውስጥ ትሳተፋለች?

ሎይድ ኦስቲን፣ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ከናታንያሁ ጋር
የምስሉ መግለጫ,ሎይድ ኦስቲን፣ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ከናታንያሁ ጋር

አሜሪካ ወደ ጦርነት ትገባለች?

በዚህ ምርጫ በተቃረበበት ጊዜ ባይደን ሌላ ጦርነት ውስጥ ለመግባት ይፈልጋሉ?

አሜሪካ በቅርብ ጊዜ የገባችባቸው ጦርነቶች በጣም ውድ ዋጋ አስከፍለዋታል። በፖለቲካም በምጣኔ ሃብትም።

ታዲያ በዚህ ሁኔታ እና በዚህ ጊዜ ባይደን ጦርነት ይመኛሉ?

ማይክል ኦረን በእስራኤል የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደር ናቸው።

“እነዚህን የጦር ጄት ተሸካሚ መርከቦችን የማትጠቀምባቸው ከሆነ እንዲሁ የምታንቀሳቅሳቸው ነገሮች አይደሉም” ሲሉ ጦርነት አይቀሬ እንደሆነ ይተነብያሉ።

ጄ ጆንስ ደግሞ የዓለም አቀፍ ደኅንነት ስትራቴጂ ማዕከል ዳይሬክተር ናቸው። እሳቸው ጆ ባይደን በጋዛ ጦርነት በቀጥታ እጃቸውን ያስገባሉ ብለው አያምኑም።

“ከባድ የጦር መሣሪያ ማስጠጋት ለብዙ አገልግሎት ሊውል ይችላል፤ ቀጥታ ጦርነት ውስጥ መግባት ለአሜሪካ የመጨረሻ፣ መጨረሻው አማራጭ ነው የሚሆነው” ይላሉ።

አሁን አሜሪካንንም ሆነ እስራኤልን በዋናነት እያሰጋ ያለው ሐማስ አይደለም። ከእስራኤል በስተሰሜን የሚገኘው ሒዝቦላህ እንጂ።

ሒዝቦላህ ከሐማስ በብዙ እጥፍ የበለጠ አቅም ነው ያለው። የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር ራሳቸው ያመኑት ሒዝቦላህ የሐማስ አሥር እጥፍ ማለት ነው።

ሒዞቦላሕ 150 ሺህ ሮኬቶች አሉት። ሮኬቶቹ ታዲያ የሐማስ ዓይነት አይደሉም። ወታደራዊ ዒላማቸውን መምታት የሚችሉ እና ጉልበታቸውም ከፍ ያለ ነው።

ማይክል ኦሬን አንድ ስጋት አላቸው። ሒዝቦላህ በዚህ ጦርነት መነሻ ምንም ላያደርግ ይችላል። ነገር ግን እስራኤል ጋዛ ገብታ በጦርነት ስትዳከም ሒዝቦላህ ሥራውን መሥራት ይጀምራል ይላሉ።

በአሜሪካ ድጋፍ የተሰራው የእስራኤል ፀረ ሚሳኤል መሳሪያ ከጋዛ የተተኮሰ ሮኬት ሲያከሽፍ
የምስሉ መግለጫ,በአሜሪካ ድጋፍ የተሰራው የእስራኤል ፀረ ሚሳኤል መሳሪያ ከጋዛ የተተኮሰ ሮኬት ሲያከሽፍ

በዚህ ጊዜ ታዲያ አሜሪካ በሊባኖስ ላይ ከፍተኛ የአየር ጥቃት መፈጸም ትጀምራለች። ማይክል ኦሬን አሜሪካ እግረኛ ጦሯን ለመጠቀም የምትገደድበት ሁኔታ አይታያቸውም።

ውጭ ጉዳይ ኃላፊው አንቶኒ ብሊንከን እና መከላከያ ሚኒስትሩ ሎይድ ኦስቲን ሁለቱም ከዚህ ቀደም ያረጋገጡት፣ በመካከለኛው ምሥራቅ ሁኔታዎች እየከፉ ከመጡ አሜሪካ እጇን አጣምራ እንደማትመለከት ነው።

“አሜሪካ ተመጣጣኝ የምትለውን ወታደራዊ እርምጃ መውሰዷ አይቀርም” ብለዋል መከላከያ ሚኒስትሩ ሎይድ ኦስቲን እሑድ ዕለት።

ሚስተር ጆንስ ይህም ሆኖ፣ እነዚህ ሁሉ ማስፈራሪያዎች ተደርድረውም የአሜሪካ ቀጥተኛ ተሳትፎ አይታያቸውም።

እስራኤል እስከ አሁን ከሐማስ ጋር በምታደርገው ጦርነት የአሜሪካንን ጠልቃ ገብነት አልጠየቀችም። በሒብሩ ዩኒቨርስቲ መምህር እና የወታደራዊ ታሪክ ፕሮፌሰር ዳኒ ኦርባች የእስራኤል ወታደራዊ መርኅ ራስን በራስ መከላከል የሚል ነው ይላሉ።

ምናልባትም በዚህ መርኅ ምክንያት ይሆናል የአሜሪካ ቀጥተኛ ድጋፍ ከእስራኤል በይፋ ያልተጠየቀው።

ይህ ሁኔታ ግን የኢራን ጣልቃ ገብነት በመጣ ቅጽበት የሚቀየር ይሆናል።

የባይደን የቴል አቪቭ ጉብኝት አንድ የገለጠው ነገር ቢኖር፣ አሜሪካ ለእስራኤል የምትሰጠው ድጋፍ ገደብ የለሽ ቢሆንም በእስራኤል ላይ ግን ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጧል።

ወደ ጋዛ ሰብአዊ ድጋፍ እንዲገባ እስራኤል እንድትፈቅድ አንድ ቅድመ ሁኔታ ነው።

እስራኤል ጋዛ ከገባች በኋላም በዚያው አልወጣም እንዳትል አሜሪካ ጠይቃለች፤ ይህም ሌላው ቅድመ ሁኔታ ነው።

ባይደን “60 ሚኒትስ” ለተሰኘው የሲቢኤስ ቴሌቪዥን መርሐ ግብር እንደተናገሩት እስራኤል ጋዛ ከገባች በኋላ አካባቢውን ይዛ እስከ ወዲያኛው ለመቆየት ካሰበች ያ ትልቅ ስህተት ይሆናል።

አሜሪካ ምናልባት ሁለት የጦር ጄት ተሸካሚ መርከቦችን ወደ አካባቢው ማስጠጋቷ እና ከእስእራኤል ጎን በማያወላዳ ሁኔታ መቆሟ በራሱ ጦርነቱ እንዳይስፋፋ ያደርጋል ብላ ሳታምን አልቀረችም።

አሜሪካ ከዚህ ቀደም በቀጥታ በእስራኤል ጉዳይ ጦር መዛ የምታውቅበት አጋጣሚ እምብዛም ነው። ከዚህ ቀደም በባሕረ ሰላጤው ጦርነት ወቅት እስራኤልን ከኢራቅ ከሚመጣ የሚሳኤል ጥቃት ተከላክላታለች።

ከዚያ ውጪብዙም የሚጠቀስ አጋጣሚ የለም።

አሜሪካ እስራኤልን የምትከላከለው ወታደራዊ ኃይሏን በማሳየት ነው።

ይሁንና ወታደራዊ ኃይሏ ለእስራኤል ጠላቶች ብቻ ማስፈራሪያነት አይውልም።

እስራኤልም በጠላቶቿ ላይ መጠን ያለፈ ወታደራዊ ጥቃት እንዳታደርስ አደብ ለማስገዛትም ትጠቀምበታለች።