ዳዊት ታዬ

October 25, 2023

ፒደብሊው እና የአማራ ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ስምምነቱን በተፈራረሙበት ወቅት

አማራ ባንክ ለአምስት ዓመታት የሚገለገልበትን የስትራቴጂክ ዕቅድና ቢዝነስ ፕላን ለማሠራት ባወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ ፒደብልዩሲ (PwC) የተባለው የእንግሊዝ ኩባንያ አሸናፊ በመሆን ከባንኩ ጋር ውል መፈጸሙ ተገለጸ፡፡ 

ከባንኩ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ለአምስት ዓመታት ባንኩ የሚመራበትን አጠቃላይ ፍኖተ ካርታ እንዲዘጋጅለት በወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ ኤኤምጂ እና ፍራንክፈርት ስኩል ፎር ፋይናንስ ኤንድ ማኔጅመንት የተባሉ ኩባንያዎች ተሳታፊ የነበሩ ቢሆንም የእንግሊዙ ኩባንያ PwC (PricewaterhouseCoopers International Limited) አሸናፊ ሆኗል። ኩባንያው የአማራ ባንክን ስትራቴጂክ ዕቅድና የአምስት ዓመት ቢዝነስ ፕላን ለማዘጋጀት 600 ሺሕ ዶላር እንደሚከፈለው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ አሽናፊው ኩባንያ በገባው ስምምነት መሠረት በስድስት ወራት ውስጥ የስትራቴጂክ ፕላኑን አዘጋጅቶ ለባንኩ የሚያቀርብ ሲሆን ስትራቴጂክ ፕላኑ ሲተገበርም በትግበራ ሥራው ላይ ለአንድ ዓመት ከባንኩ ጋር የሚሠራ ይሆናል፡፡ 

በስምምነቱ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የአማራ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሔኖክ ከበደ፣ ይህ ስምምነት ባንኩን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማራመድ የሚያግዝ ይሆናል ብለዋል፡፡ አሸናፊው ኩባንያ የአምስት ዓመት የስትራቴጂ ዕቅድና የአምስት ዓመት የቢዝነስ ፕላን የሚያዘጋጅ እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ሔኖክ፣ በተለይ በዚህ ወቅት ተወዳዳሪነትን መሠረት ያደረጉ አዳዲስ አሠራሮችን መተግበር የግድ በመሆኑ ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት የባንኩን ስትራቴጂክ ዕቅድና የአምስት ዓመታት የቢዝነስ ፕላን ዓለም አቀፍ ልምድ ባለው ኩባንያ ማሠራት አግባብነት እንዳለው አመልክተዋል፡፡ 

ጨረታውን ያሸነፈው PwC የአማራ ባንክን አጠቃላይ ቀጣይ አቅጣጫ የሚያመላክት ስትራቴጂ የሚያዘጋጅ ቢሆንም በኮርፖሬት ገቨርነርስ፣ ካፒታል ማርኬትና ኢንቨስትመንት፣ በዲጂታልና ቴክኖሎጂ አቅም ማሳደግና በመሳሰሉት ላይ ባንኩን ሊያሳድግ የሚችል የስትራቴጂክ ዕቅድ የሚቀርጽ ይሆናል፡፡ ከዚህም ሌላ የባንኩን የሥጋት አስተዳደርና (ሪስክ ማኔጅመንት) አጠቃላይ የሰው ኃይል አጠቃቀሙን በተመለከተም ዝርዝር ስትራቴጂና አተገባበሩን የሚያመላክት ይሆናል፡፡ 

ባንኩ በአፍሪካ ደረጃ ጭምር ተወዳዳሪ ለመሆን ራዕይ ያለው በመሆኑ በኩባንያው የሚሠራው ፍኖተ ካርታ ትልቅ ዕገዛ ያደርጋል ተብሎ እንደሚታመን የሥራ አስፈጻሚው ማብራሪያ አመልክቷል፡፡ 

እንዲህ ያለው ስምምነት በተለይ በዚህ ወቅት ወሳኝ ስለመሆናቸው የሚጠቅሱት አቶ ሔኖክ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ እየታዩ ያሉ አዳዲስ ክስተቶች በተለይ የፋይናንስ ዘርፉ ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት እንዲሆን ከመደረጉ ጋር በተያያዘ ሊመጣ የሚችለውን ውድድር አሸንፎ ለመውጣት አዲሱ ስትራቴጂክ ያግዛልም ብለዋል፡፡ የካፒታል ገበያ መፈጠርና የውህደት (የመርጀር አኩሌሽን) ጉዳይም ወቅታዊ በመሆኑ የሚዘጋጀው ስትራቴጂክ ዕቅድ እነዚህን በሙሉ የሚያካትት አተገባበራቸውንም የሚያሳይ እንደሆነም አቶ ሔኖክ ገልጸዋል፡፡ ጥናቱ እንዳመለከተው የባንኩ ዕቅድ አካል እንዲሆን ተደርጓል፡፡ 

ከዕውቀት ሽግግሩ አንፃርም የአሸናፊው ኩባንያ ባለሙያዎች አሸናፊው ኩባንያ ከኢትዮጵያ የፋይናንስ ኩባንያዎች ጋር አብሮ በመሥራት የሚታወቅ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የስትራቴጂክ ዕቅድ በማዘጋጀት ትግበራውን አብሮ እያካሄደ መሆኑ ይታወቃል፡፡ 

አማራ ባንክ በቅርብ ኢንዱስትሪውን ከተቀላቀሉ ባንኮች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በ2015 የሒሳብ ዓመት 19.7 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰብ ችሏል፡፡ የብድር ሥርጭቱም 15.7 ቢሊዮን ብር መድረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡ 

አጠቃላይ ደንበኞቹንም ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በላይ መድረሱን የሚያመለክተው የባንኩ መረጃ የቅርንጫፎቹ ቁጥርም 273 እንደነበሩ አመለከቱ፡፡ የባንኩ አጠቃላይ የተከፈለ ካፒታልም በ2015 መጨረሻ 5.9 ቢሊዮን ብር ነው፡፡