

የቻይናው አምባሳደር ሚስተር ዣኦ ዢዬዋን መግለጫውን በሰጡበት ወቅት
ዜና ቻይና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ደኅንነት ለማስጠበቅ ድጋፍ እንደምታደርግ ተገለጸ
ቀን: October 25, 2023
ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን፣ ደኅንነቷንና የልማት ፍላጎቷን ለማስጠበቅ በምታደርገው ሒደት፣ ቻይና ድጋፏን እንደምታደርግ የቻይና ባለሥልጣናት አስታወቁ፡፡
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩዋን ሰኞ ጥቅምት 12 ቀን 2016 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነበር፣ የፕሬዚዳንታቸውን ሺ ጂንፒንግ መልዕክት በማብራራት ቻይና ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ የገለጹት፡፡
ሁለቱ አገሮች አንድነታቸውና ትብብራቸውን ማጠናከርና የየራሳቸው ዋና ዋና ፍላጎቶችና ሥጋቶች ላይ በጥንካሬ መደጋገፍ እንዳለባቸው ያስረዱት አምባሳደሩ፣ ‹‹ፕሬዚዳንት ሺ ቻይና የኢትዮጵያን ደኅንነት፣ ሉዓላዊነትና የልማት ፍላጎት ለማረጋገጥ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፤›› ብለዋል፡፡
የቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሼቲቭ (Belt and Road Initiative) በተጀመረበት በአሥረኛ ዓመቱ በተካሄደው ሦስተኛው ፎረም ለመካፈል ባለፈው ሳምንት በቻይና ቆይታ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ከፎረሙ በተጨማሪም ካከናወኗቸው ተግባራት መካከል ከቻይና ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳይ ላይ ያደረጉት ውይይት ይጠቀሳል፡፡
ሁለቱ መሪዎች ያደረጉት ውይይትና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቻይና ጉብኝት በሁለቱ አገሮች መካከል ለሚኖረው ግንኙነት ትልቅ አንድምታ እንዳለውና ሦስት ዋና ዋና ስኬቶች እንደተገኙበት ነው አምባሳደሩ ያስረዱት፡፡
አንደኛው ፕሬዚዳንት ሺ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ ባወጡት የጋራ መግለጫ እንደጠቀሱት፣ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ወደ ዘላቂና የማይቀየር ስትራቴጂያዊ አጋርነት (All-Weather Strategic Partnership) ማደጉን እንደሆነ አምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡ ቻይና ይህንን ስምምነት ከተፈራረመቻቸው ጥቂት አገሮች አንደኛዋ ኢትዮጵያ ስትሆን፣ በኢኮኖሚም ከቻይና ጋር ስምምነቱ ከተፈራረሙ አገሮች በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ በአምባሳደሩ ተገልጿል፡፡
ሁለተኛው በሁለቱ አገሮች ከፍተኛ አመራሮች የተደረጉ ውይይቶችና የጋራ መተማመን ማጠናከሪያ ሲሆኑ፣ ሦስተኛው ስኬት እንደሆነ አምባሳደሩ የገለጹት ደግሞ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) እና የቻይና ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ያንግ የተፈራረሟቸው 12 የመግባቢያ ሰነዶችና ሁለት በቤልት ኤንድ ሮድ ትብብር ላይ ያተኮሩ ስምምነቶች ናቸው፡፡
‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሻንጋይና በቼንጉ ከተሞች ዕድገት እጅግ መማረካቸውን፣ ለበለጠ ትብብርም ከኢትዮጵያ ቡድን እንደሚልኩ ነግረውኛል፤›› ሲሉ አምበሳደሩ በመግለጫው ላይ ለተገኙት ጋዜጠኞች ገልጸዋል፡፡
በቤልት ኤንድ ሮድ ፎረሙ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ንግግር አድርገው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከ151 አገሮችና ከ41 ዓለም አቀፍ ተቋማት የተውጣጡ ከአሥር ሺሕ በላይ ተወካዮች በፎረሙ ተገኝተው የነበረ መሆኑን፣ በተደረጉ ስምምነቶችም 458 ውጤቶች ከፎረሙ መገኘታቸው ተገልጿል፡፡
