

ዜና ጀርመን በፋይናንስ ተቋማት በኩል ለኢትዮጵያ የምታበረክተው ድጋፍ ጠንካራ መሆኑ ተገለጸ
ቀን: October 25, 2023
ጀርመን ለኢትዮጵያ በሁለትዮሽ የትብብር ማዕቀፍ ከምታደርገው የልማትና የፋይናንስ ድጋፍ በተጨማሪ፣ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በኩል የምታበረክተው ድጋፍ ጠንካራ መሆኑ ተገለጸ።
በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፋን አወር የቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ፣ የምሥራቃዊ ጀርመን ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ከምዕራብ ፌዴራል ጀርመን ሪፐብሊክ ጋር የተዋሃዱበትን 33ኛ ዓመት አስመልክቶ ትናንት ጥቅምት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ ሲከበር እንደተናገሩት፣ ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ትብብር ለማጠናከር ትሠራለች፡፡
ኢትዮጵያና ጀርመን ከ110 ዓመታት በላይ የዘለቀ የሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው የተናገሩት አምባሳደር አወር ጀርመን ያላትን የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እንደምትሠራ ተናግረዋል።
በኤምባሲው በተደረገው መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ፣ ኢትዮጵያና ጀርመን ከመቶ ዓመታት በላይ ያስቆጠረ ጠንካራ አጋርነት እንዳላቸው አንስተው፣ ጀርመን ውህደቷን ካረጋገጠች ጀምሮ ለዓለም ምሳሌ የሚሆን ጠንካራ ኢኮኖሚያዊ ማኅበረሰብ መገንባት መቻሏን ጠቅሰዋል።
በተለያዩ የትበብር መስኮች ላይ የተመሠረተው የኢትዮጵያና የጀርመን የሁለትዮሽ ግንኙነት እ.ኤ.አ. በ1905 መጀመሩንና የአገራቱ የሁለትዮሽ ትብብር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ መምጣቱም ተጠቁሟል፡፡
