የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ፀጋዬ ቱኬ

ዜና የቀድሞው የሀዋሳ ከንቲባ ከውጭ አገር ሲመለሱ በቁጥጥር ሥር ዋሉ

ዮሐንስ አንበርብር

ቀን: October 25, 2023

በወንጀል ተጠርጥረው ሲፈለጉ የነበሩት የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ፀጋዬ ቱኬ፣ ትናንት ማክሰኞ ጥቅምት 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ቦሌ አየር ማረፊያ ላይ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለዋል።

አቶ ፀጋዬ ጥቅምት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ከረፋዱ አምስት ሰዓት ላይ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እንደደረሱ በሕግ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ከኢሚግሬሼንና ከኢንተር ፖል ጋር በተመባበር ግለሰቡን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ክትትል ሲያደርግ አንደቆየ ገልጾ፣ ሆኖም ግለሰቡ በራሳቸው መንገድ ወደ ኢትዮጵያ እየተመለሱ መሆኑን የሚገልጽ መረጃ እንደደረሰው፣ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ እንደደረሱ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስታውቋል።

ተጥርጣሪው የቀድሞ ከንቲባ በአሁኑ ወቅት በሀዋሳ ከተማ የእስረኛ ማቆያ በቁጥጥር ሥር እንደሚገኙም ፖሊስ ኮሚሽኑ አስታውቋል። 

ከጥቂት ወራት በፊት በሲዳማ ክልል ሲካሄድ የነበረውን ከፍተኛ የአመራር ግምገማ ረግጠው እንደወጡ የተወራባቸው የቀድሞው የሀዋሳ ከንቲባ፣ ከዚያን ወቅት ጀምሮ ደብዛቸውን አጥፍተው እንደቆዩ ምንጮች ገልጸዋል።

ተጠርጣሪውን የቀድሞ ሀዋሳ ከንቲባ በቁጥጥር ሥር ለማዋል በሲዳማ ብሔራዊ ክልል የፀጥታ ግብረ ኃይል ያልተቋረጠ ክትትል ሲደረግ እንደነበር የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዓለማየው ጢሞቲዎስ ገልጸዋል። 

ተጠርጣሪው የቀድሞው የሀዋሳ ከንቲባ በተለያዩ ወንጀሎች እንደሚፈለጉም ምንጮች ጠቁመዋል። 

በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ በነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም. ሲካሄድ በነበረው የአመራሮች ግምገማ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ያልተወጡና በብልሹ አሠራር ላይ የተሳተፉ አመራሮች በሕግ እንዲጠየቁ የፖለቲካ ውሳኔ መተላለፉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደስታ ሌዳሞ በወቅቱ ገልጸው ነበር።

በወቅቱ በተካሄደው ግምገማ በማዳበሪያ ሥርቆት የተሳተፉ አመራሮች በሕግ እንዲጠየቁ መወሰኑን የክልሉ ፕሬዚዳንት ተናግረው ነበር።

አክለውም፣ በሀዋሳ ከተማ ላይም ከፍተኛ ሌብነትና ብልሹ አሠራር ላይ የተነሳውን ውይይት በመሸሽ ስብሰባ ረግጠው የሄዱ አመራሮች መኖራቸውን አንስተው፣ ተጠያቂ መሆን ያለባቸው አመራሮች ስለሸሹ ከተጠያቂነት አያመልጡም ብለው ነበር።

በወቅቱ በተላለፈው ውሳኔ መሠረትም 97 የሚሆኑ እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ በተዘረጋ መዋቅር በማደበሪያ ሥርቆት ላይ የተሳተፉ የክልሉ የመንግሥት መዋቅር አመራሮች በሕግ እንዲጠየቁ ተብሎ ነበር። ከእነዚህ ወስጥም 25 አመራሮች በነሐሴ ወር ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውለዋል።