

ማኅበራዊ አብዛኞች ዘግይተው የሚደርሱበት የጡት ካንሰር
ቀን: October 25, 2023
በጡት ላይ የሚገኝ እብጠት፣ ደም የቀላቀለ ፈሳሽ ከጡት መውጣት፣ የጡት ቆዳ ወደ ውስጥ መሰርጎድ፣ የጡት ጫፍ ወደ ውስጥ መግባት፣ የጡት ቆዳ ቀለም ወደ ቀይነት ማድላት፣ የጡት ቆዳ መሻከር (የብርቱካን ልጣጭ ይመስል)፣ የጡት ንፍፊት መጠን መጨመር ወይም ማበጥ የጡት ካንሰር ምልክቶች ሊሆኑ ስለሚችሉ ወደ ሕክምና መሄድ እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ምልክቶቹ ሲታዩ ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ ካንሰር ስለመሆኑ በምርመራዎች ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ፣ ከምርመራዎቹም መካከል የናሙና ምርመራ፣ ደረጃውንም ለማረጋገጥ ራጅ፣ አልትራሳውንድና ሌሎችም መሠራት እንዳለባቸው ይገልጻሉ፡፡
እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት፣ በመላው ዓለም ወደ 2.3 ሚሊዮን የሚጠጉ ሴቶች በየዓመቱ በጡት ካንሰር ይያዛሉ፡፡ 685.000 ያህሉ ደግሞ ለሕልፈተ ሕይወት ይዳረጋሉ፡፡
ብዙውን ጊዜ ሴቶች የጡት ካንሰር ተጠቂዎች ሲሆኑ፣ ከ0.5 እስከ አንድ በመቶ የሚሆኑ ወንዶችም በበሽታው ይያዛሉ፡፡
እ.ኤ.አ በ2040 በየዓመቱ በአዲስ የጡት ካንሰር የሚያዙ ሴቶች ቁጥር ወደ ሦስት ሚሊዮን፣ ለሕልፈተ ሕይወት የሚዳረጉ ሴቶች ደግሞ አንድ ሚሊዮን ይሆናሉ ሲልም የድርጅቱ ትንበያ ያሳያል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ በየዓመቱ ከ60 ሺሕ በላይ ሴቶች በጡት ካንሰር ይያዛሉ፡፡ ለጡት ካንሰር የሚዳርጉ ብዙ ምክንያቶች ሲኖሩ፣ የታሸጉ ምግቦችንና መጠጦችን ማዘውተር፣ ትምባሆ ማጨስ፣ ከቤተሰብ ሲወርድ የመጣ የጡት ካንሰር በሽታ፣ ከክብደት በላይ ውፍረት ከምክንያቶቹ ይጠቀሳሉ፡፡
ምክንያቶቹ እንደተጠበቁ ሆነው መከላከል የሚያስችሉ መንገዶች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ክብደትን መቆጣጠር፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ አትክልትና ፍራፍሬ መመገብ፣ የአልኮል መጠጥ መጠንን መቀነስ ወይም ከነጭራሹ አለመጠቀም፣ አለማጨስ፣ የወሊድ መቆጣጠሪያ የሆኑ ፒልሶችን በተለይ ከ35 ዓመት ዕድሜ በኋላ አለመጠቀም ተጠቃሾች መሆናቸውን መረጃው አመላክቷል፡፡
በጡት ካንሰር ምክንያት የሚከሰት የሞት መጠንን ለመቀነስና የኅብረተሰብን ጤና አጠባበቅ ለማሻሻል በየዓመቱ በጥቅምት የካንሰር ወር በመባል የተለያዩ እንቅስቃሴዎች የሚከናወኑበት እንዲሆን ተደርጓል፡፡ በዚህም እንቅስቃሴ ቅድመ ምርመራዎችን ለማስፋት፣ ለኅብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ለማከናወንና ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ የተለያዩ ተግባራት ይከናወናሉ፡፡
ይህንንም ሥራ በጋራ የሚያከናውኑት ጤና ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ፣ ፓዮኔር ዲያግኖስቲክ ሴንተርና ክሊንተን አክሰስ ኢኒሼቲቭ ናቸው፡፡ ይህንኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ ወር አስመልክቶ በዘውዲቱ አጠቃላይ ሆስፒታል ነፃ የጡት ካንሰር ምርመራ የማስጀመር ፕሮግራምም ተካሂዷል፡፡
‹‹የጡት ካንሰርን ቀድሞ መለየትና ማከም ሕይወት ያድናል›› በሚል መሪ ቃል፣ በተከናወነው በዚሁ ፕሮግራም የጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሕይወት ሰለሞን (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለጡት ካንሰር ሕክምና ወደ ጤና ተቋማት ከሚመጡ ሰዎች መካከል 65 በመቶዎቹ መምጣት ከሚገባቸው ጊዜ ዘግይተው እንደሚመጡ ተናግረዋል፡፡
የጡት ካንሰርን በቀላሉ በእጅ በመዳሰስ፣ በመለየትና በወቅቱም ወደ ሕክምና በመሄድ በሽታውንና ሞትን ለመከላከል እንደሚቻል፣ ይህ እንዳይሳካ የሚያጋጥሙ እንቅፋቶች እንዳሉ፣ ከሚያጋጥሙትም እንቅፋቶች መካከል የግንዛቤ ማነስና ምቹ ተቋማት አለመኖራቸው ተጠቃሽ እንደሆኑና እንቅፋቶቹንም ለማስወገድ በጋራ መንቀሳቀስ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በመጀመርያ ደረጃ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ቢያንስ በወረዳ ተቋም እንዲኖር ለማድረግ የሚያስችል ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን ገልጸው፣ እስካሁንም በተሠራው ሥራ ከ1,300 በላይ የጤና ተቋማት አገልግሎቱን እየሰጡ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አዲስ አበባ በሚገኙት ዘውዲቱና ጋንዲ ሆስፒታሎች እንዲሁም በጃጋማ ኬሎ ጤና ጣቢያም የልየታ ሥራ ተጀምሯል፡፡
