የአስራኤል ወታደሮች በታንክ ላይ
የምስሉ መግለጫ,የእስራኤል ወታደሮች ከሐማስ ጥቃት ሁለት ቀን በኋላ ወደ ጋዛ ድንበር ተጠግተዋል

ከ 5 ሰአት በፊት

እስራኤል ጋዛን በአየር ስትደበድብ ከሁለት ሳምንት በላይ ሆኗታል።

በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿንም በጋዛ ድንበር አቅራቢያ አሰባስባ፣ በጋዛ ላይ ወረራ ለመፈጸም እየተዘገጀች ነው።

እስራኤል ከሐማስ የተቃጣባትን መብረቃዊ ጥቃት ለመበቀል ነው የተነሳችው። ሐማስን ከምድረ ገጽ ሳላጠፋ አልመለስም ስትል ዝታለች።

አሁን የሚጠበቀውም፣ የሚፈራውም እግረኛ ሠራዊት ወደ ጋዛ ሲገባ እዚያ ምን ሊፈጠር ይችላል የሚለው ነው። በዚህ ረገድ የቢቢሲ አረብኛ ዘጋቢ ፈራስ ኪላኒ ከልምዱ በመነሳት ሐሳቡን ያጋራናል።

ኪላኒ በመካከለኛው ምሥራቅ የተደረጉ በርካታ ተመሳሳይ ጦርነቶችን በመዘገብ ይታወቃል።

የከተማ ውስጥ ጦርነት ምን ይመስላል?

ከአምስት ዓመታት በፊት በጋዛ አልሻቲ የስደተኛ ካምፕ ለመጎብኘት በመኪና ሄድኩ። መሬቱ የረገበ ያህል ተሰማኝ። ይንጓጓል።

በተንጠልጣይ ድልድይ ላይ መኪና የመንዳት ያህል ሆነብኝ። ምንድነው ብዬ ጠየቅኩ።

የካሜራ ባለሙያ የሆነው ባልደረባዬ ነገሩን ገለጠልኝ። ከመሬቱ በታች መሾሎክሎኪያ ዋሻዎች ተቆፍረዋል። በሐማስ ነው የተቆፈሩት።

ጥልቅ ዋሻ ስለሆነ የመንገዱ መርገብገብ በዚያ ምክንያት የመጣ ነው።

ዋሻው ቀላል እንዳይመስላችሁ። ከመቶ ኪሎ ሜትሮች በላይ ያስኬዳል። አንዳንዶቹ ዋሻዎች እስከ እስራኤል ድረስም ይዘልቃሉ ተብሎም ይነገራል።

ሐማስ ትጥቅ እና ስንቅ የሚያስተላልፈው በዚያ ዋሻ አማካይነት ነው።

ጋዛ በዓለም ላይ በትንሽ ስፍራ ብዙ ሕዝብ እጭቅ ብሎ ከሚኖርባቸው አካባቢዎች አንዷ ናት።

በዚያ በታጨቀ ከተማ ውስጥ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስም ፈተና ነው። መንገዶች በጣም ጠባብ ናቸው።

ጋዛ ውስጥ ከመሬት በታች ያለ ዋሻ
የምስሉ መግለጫ,ጋዛ ውስጥ ከመሬት በታች ያሉት ዋሻዎች ለሐማስ ተዋጊዎች እና ለትጥቅ አቅርቦት ያገለግላሉ

በዚያ በተጨናነቀ ቦታ ነው መሿለኪያ ተፈልፍሎ የተገነባው። ቦታው ሲታይ ማንም በቦታው ሥር ዋሻ ይኖራል ብሎ አይጠረጥርም።

እስራኤል የአየር ጥቃት ስትሰነዝር ቆይታ አሁን ታንከኛ እና እግረኛ ሠራዊት ወደ ጋዛ ድንበር አስጠግታለች። በማንኛውም ቅጽበት ወደ ጋዛ ትገባለች ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ ማለት ዋሻዎቹ ለሐማስ ጦር ብቸኛ መዋጊያ ማዕከሎች ይሆናሉ።

ሐማስ የእስራኤል እግረኛ ጦር እንደሚመጣ ሳይገምት አልቀረም። ይህም በመሆኑ ምግብ፣ ውሃ እና የጦር መሣሪያ በበቂ ያከማቻል ተብሎ ይጠበቃል።

እነዚህ ዋሻዎች ሐማስ እንደልቡ ከጋዛ አንድ ጥግ ወደ ሌላ ጥግ እንዲሽሎከለክ ዕድል ይሰጡታል። አድብቶ ከኋላ የእስራኤልን ጦር ለመምታትም ያስችሉታል።

እስራኤል እንደምትለው ሐማስ አውቶማቲክ ጠመንጃን መጠቀም የሚችል መሠረታዊ ውትድርናን የሚያውቅ 30ሺህ ሠራዊት አለው። ሐማስ ብቻውን አይደለም። ከጎኑ ሊቆሙ የሚችሉ ኢስላሚክ ጂሐድ እና ሌሎች ትንንሽ ነፍጥ ያነገቡ ኃይሎችም አሉ።

የቅርብ ታሪኮች የከተማ የጨበጣ ውጊያዎች እንዴት አደገኛ እንደሆኑ አሳይተዋል። የተወሰኑትን በዐይኔ ተመልክቻለሁ።

የሐማስ ወታደሮች ንጽጽር

የከተማ እና የጨበጣ ውጊያ ምን ሊመስል ይችላል?

በአውሮፓውያኑ 2016 ሞሱል ላይ ዘመቻ ሲከፈት ከኢራቅ ጦር ጋር ነበርኩ። ባለሥልጣናቱ እስላማዊ ቡድኖችን ለመክበብ እና መፈናፈኛ ለማሳጣት ወሰኑ። ከተከበቡ ወደየትም መሸሽ አይችሉም። ያ ወታደራዊ ስትራቴጂ ከተማዋን አኬልዳማ ሊያደርጋት ሆነ።

ልክ መጀመሪያ ወደ አንድ የሞሱል ቀበሌ እንደገባን በታጣቂዎቹ የተሰነዘረው መከላከል እና ጥቃት አስደንጋጭ ነበር። በተሽከርካሪዎች ላይ የማይተኩሱት ነገር አልነበረም። ቦምቦች እና በትከሻ የሚተኮሱ ሚሳኢሎች ሳይቀር ያስወንጭፉ ነበር።

መሬቱ በተቀበሩ ተቀጣጣይ ፈንጂዎች ተሞልቷል። የትኛውንም ቦታ መርገጥ ሞት ሊሆን ይችላል።

በየቤቱ ፍሪጆች፣ ቴሌቪዥኖች ሳይቀር ወዳድቀዋል። ማንኛውን ነገር ለማንሳት ወይም ለማቀናት መሞከር የሞት ጥሪ ሊሆን ይችላል።

ወደ ጋዛ የሚገቡትን የእስራኤል ወታደሮች እንዲህ ያለው ተመሳሳይ ዕጣ ሊገጥማቸው ይችላል።

ከስድስት ዓመት በፊት ሞሱል ውስጥ የኢራቅ ሠራዊት እና የበአይኤስ ተዋጊዎች ለዘጠኝ ወራት ተዋግተዋል
የምስሉ መግለጫ,ከስድስት ዓመት በፊት ሞሱል ውስጥ የኢራቅ ሠራዊት እና የበአይኤስ ተዋጊዎች ለዘጠኝ ወራት ተዋግተዋል

በሞሱል ሌላው ያስተዋልኩት ነገር ቢኖር የኢራቅ ወታደሮች ትኩረታቸው ጦርነት ውስጥ ከመግባታቸው በፊት እና በኋላ መቀያየሩን ነው።

ጦርነቱ ብርቱ ስለነበር ራሳቸውን ለማዳን ነበር የሚዋጉት። ሲቪሎችን ለመከላከል የሚባለው ነገር ፈጽሞ ይዘነጋል፤ የሞት-ሽረት ውጊያ ስለሚሆን።

ሌላው ለእስራኤል ወታደሮች ፈተና ይሆናል ብዬ የማስበው አልሞ ስናይፐር ነው። ስናይፐር ከርቀት አልሞ ተኳሽ መሣሪያ ነው። ተዋጊዎች የሞሱል ሕንጻዎችን ምሰሶዎች ተገን አድረገው በመደበቅ የኢራቅ ወታደሮችን ሲገድሉ ነበር።

ይህንን አደጋ ለማሰወገድም የአየር ኃይል አውሮፕላኖች አካባቢውን በሙሉ እያዋደመ ነው ስጋቱን መቅረፍ የተተቻለው።

እስራኤል ሁለት አማራጭ ነው የሚኖራቸው። አንዱ በጋዛ የሚገኙትን እያንዳንዱን ሕንጻዎች ወደ ፍርስራሽነት መቀየር። ሌላው ደግሞ በድፍረት የሐማስ አልሞ ተኳሾችን (ስናይፐሮችን) መግጠም። ሌላ መውጫ የለም።

የወታደር ተሽከርካሪዎችም በሞሱል መንቀሳቀስ ፈተና ሆኖባቸው ሰንብቶ ነበር። መንገዶች በፈንጂዎች ተሞልተዋል። ይህ ነገር ለእስራኤሎችም ፈተና እንደሚሆን ነው የሚጠበው።

ሐማስ ፈንጂዎችን በመጠቀም ብዙም አይታወቅም። ነገር ግን አጥፍቶ ጠፊዎችን የማሰማራት ልምድ አለው። ይህ ደግሞ ለእስራኤል ወታደሮች ሌላ ፈተናን ይደቅናል።

እስራኤል ጋዛ ውስጥ የምታካሂደው ዘመቻ ምን ያህል ጊዜ ሊወስድባት እንደሚችል አይታወቅም። ነገር ግን አጭር ዘመቻ አይሆንም። የኢራቅ ኃይል ሞሱልን ለመቆጣጠር ድፍን ዘጠኝ ወራት ወስዶበታል።

በሶሪያ ራቃ የተካሄደው የከተማ ውጊያ በጋዛ ሊደገም ይችላል?

በ2017 (እአአ) ሕዝብ እጭቅ ብሎ በሚኖርባት ራቃ ታጣቂዎች ተከበቡ። በአሜሪካ ይመራ የነበረው እና ኩርዶችን የያዘው ኃይል ፈተና ውስጥ ገባ። በመጨረሻ ለታጣቂዎቹ ከከበባው የመውጫ ‘የማሪያም መንገድ’ ይሰጣቸው በሚል ወሰነ።

ለበርካታ ጊዜያት ኩርዶች ከአይኤስ ጋር ያደረጉትን ጦርነት ስዘግብ ነው የኖርኩት።

በዚያ ወቅት የአሜሪካ ወታደሮች ወደ አንድ ድብቅ ስብሰባ ይዘውኝ ሄዱ። ከአካባቢው የአረብ ሽማግሌዎች ጋር ተደራደሩ። ሽማግሌዎቹ ያቀረቡት ጥያቄ የአይኤስ ተዋጊዎች እና ቤተሰቦቻቸው በሰላም ራቃን ለቀው እንዲወጡ እንዲፈቀድላቸው ነበር።

ይህ ስምምነት ነው ራቃን ያዳናት። በሞሱል እና በራቃ ወታደራዊም ሆነ የሲቪል ሞት በጭራሽ የሚወዳደር አይደለም።

በራቃ የአይኤስ ተዋጊዎች ከተማውን ለቀው ሲወጡ ነዋሪዎች በእፎይታ ከቤታቸው ወጡ። ብዙዎቹ በውጊያው እንደሚያልቁ ነበር ያመኑት።

ይህ ዓይነቱ ስምምነት ለጋዛ የሚስማማ አይመስልም። መልከዓ ምድሩም ለዚህ ዓይነቱ ስምምነት ብዙ ምቹ አይደለም። ራቃ አንጻራዊ በሆነ መልኩ በሶሪያ ውስጥ ከማዕከል ርቆ የሚገኝ ከተማ ነው። ተዋጊዎች እንዲወጡ ሲፈቀድላቸው መሄድ የሚችሉባቸው ሥፍራዎች አሉ።

ይህ ለጋዛ አይመችም፤ የጋዛ ሰርጥ በጣም ጠባብ ነው። ሐማስ በሰላም ከጋዛ እንድወጣ መንገድ ይሰጠኝ ቢልም ወዴት ይሄዳል?

በጦርነት የወደመችው ራቃ
የምስሉ መግለጫ,በአሜሪካ እና ኩርድ ኃይሎች አማካይነት በተደረሰው ስምምነት ከስድስት ዓመት በፊት በሶሪያዋ ራቃ ከተማ ሊያጋጥም ይችል የነበረውን የተራዘመ የጎዳና ላይ ውጊያ ማስቀረት ተችሏል።

ሐማስ ወደ ሌላ አገር ልውጣ ሊል ይችላል?

ከዚህ ቀደም የፍልስጥኤም ነጻ አውጪ ድርጅት (ፒኤልኦ) ቤይሩትን እንዲለቅ ዕድል ተሰጥቶታል። ይህ የሆነው በ1982 (እአአ) በእነ ያሲር አረፋት ጊዜ ነው። ያን ጊዜ በእስራኤል ወታደሮች ከበባ ስር ወድቆ በነበረበት ጊዜ ነው ወደ ሦስተኛ አገር ልውጣ ብሎ የተፈቀደለት።

የፒኤልኦ መሪዎች እና ወታደሮች በዚያ ወቅት ከፊሎቹ ወደ ቱኒዚያ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ወደ ሌሎች መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ሄዱ።

የሲቪሎችን ሞት ለመቀነስ እንዲህ ዓይነቱ ስምምነት በከባድ ወታደራዊ ፍጥጫ ጊዜ አይሆንም አይባልም።

ነገር ግን በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ይህ ይሆናል ወይ? የሚለው አጠያያቂ ነው። አንዱ ምክንያት እስራኤል ሐማስን እስከመጨረሻው መቅበር ትፈልጋለች። የኔታኒያሁ መንግሥት ይህን ለማድረግ ለሕዝብ ቃል ገብቷል።

አሁን ሐማስ ወደ ሌላ አገር በሰላም ይውጣ የሚል ስምምነት በአደራዳሪዎች ቢቀርብለት የሚስማማ ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም።

የሞሱል እና የራቃ ልምዶች ይህን ይመስላሉ።

በጊዜ መፍትሄ ካልተበጀ በከተማ ውስጥ የሚደረግ የጨበጣ ውጊያ ጋዛን የደም መሬት ያደርጋታል።