ስርቆት የተፈጸመበት አካባቢ

ከ 2 ሰአት በፊት

በቤንሻንጉል ጉሙዝ የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ምሰሶዎች ላይ በተፈጸመ ስርቆት በክልሉ ሙሉ በሙሉ የኃይል አቅርቦት መቋረጡን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

ከመንዲ አሶሳ በተዘረጋው ባለ 132 ኪሎቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶ አካላት ላይ ስርቆት በመፈጸሙም ክልሉ ሙሉ በሙሉ መብራት እንደተቋረጠበት ተቋሙ ትናንት ጥቅምት 14/2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።

በማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶ አካላት ስርቆት ምክንያትም መስመሩን የሚሸከሙ ሁለት የብረት ምሰሶዎች ወይም ታወሮች መውደቃቸውን መግለጫው አስፍሯል።

ስርቆቱ የተፈጸመው መንደር 48 ወይም በተለምዶ አንበሳ ጫካ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲሆን ይህም ከአሶሳ ከተማ ወደ 30 ኪሎሜትር ርቀት እንዳለው መግለጫው ያስረዳል።

በዚህም የተነሳ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መዲና አሶሳ ከተማ እና የአሶሳ ዞን ወረዳዎች በሙሉ የኃይል አቅርቦት መቋረጡም ተገልጿል።

በአሁኑ ወቅት ተቋሙ የወደቁ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎችን በጊዜያዊነት በእንጨት ምሰሶዎች ለመተካት ጥረቶች መጀመሩንም ገልጿል።

ጥገናውን አጠናቆ ለአካባቢው ኃይል ለመስጠትም እስከ ሦስት ቀን ድረስ ሊወስድ እንደሚችልም ነው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በዚሁ መግለጫ ያሰፈረው።

ጥገናው ተጠናቆ ወደ አገልግሎት እስኪመለስ ኅብረተሰቡ በትዕግስት እንዲጠብቅም ጥሪውን አቅርቧል።

በክልሉ በስርቆት የተነሳ የኃይል መቋረጥ ሲያጋጥም የመጀመሪያው አይደለም።

ከዚህ ቀደም ባምባሲ በተባለ አካባቢ በስርቆት የተነሳ የኃይል መቋረጥ አጋጥሞ የነበረ መሆኑን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በዚሁ መግለጫ መሰረተ ልማቶችን መጠበቅ የክልሉ ኃላፊዎች ተግባር እንደሆነም ጠቅሷል።

“የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶችን መጠበቅ በየደረጃው ያሉ የሁሉም መስተዳድር አካላት ኃላፊነት በመሆኑ የመስተዳድር አካላቱ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ እናደርጋለን” ብሏል።