October 26, 2023 – Konjit Sitotaw 

ጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ ከአመራሩ አንዱ መንገድ ላይ «መታፈናቸውን» ዐስታወቀ

ጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ፦ የጽ/ቤቱ ምክትል ኃላፊ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ አቶ መላኩ ሣኅሌ «ትናንት ጥቅምት 14 ቀን፣ 2016 ዓ.ም በፀጥታ ኃይላት መያዛቸውን ዐስታወቀ ። ከፓርቲው ከፍተኛ አመራር አንዱ የሆኑት የአቶ መላኩን መያዝ የፓርቲው የሕዝበ ግንኙነት መምሪያ ኃላፊ አቶ ጀሚል ሳኒ ለዶቼ ቬለ (DW) ዛሬ አረጋግጠዋል ።

አቶ መላኩ ሣኅሌ፦ «ትናንት በመኖሪያ ቤታቸው አቅራቢያ ከምሽቱ 12:00 ሰዓት አካባቢ መታፈናቸውን ከቤተሰቦቻቸው ተረድተናል» ሲልም ፓርቲው ጽፏል ። በአሁን ሰዓት አቶ መላኩ ሰሜን ሆቴል አካባቢ እሚገኘው 3ተኛ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ እንዳሉም ፓርቲው ዐስታውቋል ። ሆኖም ግን ፖሊስ የፓርቲያችንን አመራር ለምን እንዳሰራቸው አልገለፀም ሲልም አክሏል ።

አቶ መላኩ ከዚህ በፊት ተከሰው የማያውቁና ሊያስጠረጥራቸው የሚችል ወንጀል ፈጽመዋል የሚል እምነት እንደሌላቸው የጠቀሱት አቶ ጀሚል የአሁኑ እሥር ምናልባት በግል የማኅበራዊ መገናኛ አምዳቸው ከሚያነሷቸው ሀሳቦች እና ትችቶች ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት እንዳላቸው ተናግረዋል ። ጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ፦ ገዢው የብልፅግና ፓርቲን አጥብቆ በመቃወም ይታወቃል ።

ፎቶ፦ ከጎጎት ለጉራጌ አንድነት እና ፍትሕ ፓርቲ የፌስቡክ ገጽ የተወሰደ ።