
26 ጥቅምት 2023
የቻይና ፖሊስ የአሳማ እና የበግ ሥጋ ተብለው ታረደው ለገበያ ሊቀርቡ የነበሩ አንድ ሺህ ድመቶችን መያዙን አስታወቀ።
ፖሊስ ከአንድ የእንስሳት መብት ተሟጋች ቡድን የደረሰውን ጥቆማ ተከትሎ ባደረገው ክትትል ድመቶቹን ሲያጓጉዝ የነበረን መኪና ዚያንግጂአጋንግ በተባለች ከተማ ላይ ይዟል።
ለእርድ ሲጓጓዙ የነበሩት ድመቶች ባለቤት ይኑራቸው አይኑራቸው እስካሁን አልታወቀም።
ፖሊስ ድመቶቹን የታደገው ወደ አገሪቱ ደቡባዊ ክፍል እየተጓጓዙ ሳለ ሲሆን፣ በመዳረሻውም ታርደው የአሳማ ወይም የበግ ሥጋ በሚል ተጠብሰው እና በቋሊማ መልክ ተዘጋጅተው ለገበያ ለማቅረብ ታስቦ ነበር ተብሏል።
እንደ የእንስሳት መብት ተሟጋች ቡድኑ ከሆነ 600 ግራም ያክል የድመት ሥጋ እስከ 0.61 ዶላር ያወጣል። ከአንድ ድመት 4 ዶላር የሚያወጣ ሥጋ ይገኛል ተብሏል።
‘ዘ ፔፐር’ የተሰኘው ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ ዚያንግጂአጋንግ ከተማ የሚገኙ የእንስሳት መብት ተሟጋቾች በአንድ የመቃብር ስፍራ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ድመቶች ከእንጨት በተሰራ ሳጥን ውስጥ ታጭቀው ከተመለከቱ በኋላ ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ ድመቶቹን ለመታደግ ተችሏል።
- ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎቷን በኃይል እና በወረራ ማሳካት አትፈልግም፡ ጠ/ሚ ዐቢይ26 ጥቅምት 2023
- ጋዛ ውስጥ እየተፈጸሙ ባሉ ጥቃቶች የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ7 ሺህ አለፈ22 ጥቅምት 2023
- በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ወንድማቸውን የገደሉት እህትማማቾች በእስራት ተቀጡ26 ጥቅምት 2023
ይህ ዘገባ ከወጣ በኋላ ጉዳዩ በርካታ ቻይናውያንን ያስቆጣ ሲሆን፣ በአገሪቱ ያለው የምግብ ደኅንነት እና ጥራት ጉዳይ መነጋገሪያ ሆኗል።
‘ዌይቦ’ በተሰኘው የቻይና ማኅብራዊ ሚዲያ ላይ ተጠቃሚዎች እንስሳትን የሚጠብቅ ጠንከር ያለ ሕግ በአገሪቱ እንዲረቀቅ የጠየቁ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ ከአሁን በኋላ በሬስቶራንቶች ምግብ አንመገብም ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በተመሳሳይ ከጥቂት ወራት በፊት በጂያንግሱ ግዛት አንድ የኮሌጅ ተማሪ ምግቡ ውስጥ የአይጥ ጭንቅላት ካገኘ በኋላ ጉዳዩ ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
በቻይና በስፋት ባይሆንም የውሻ እና የድመት ሥጋ ለምግብነት የሚቀርብባቸው ማኅብረሰቦች አሉ።
የኮቪድ ስርጭት ወቅት የቫይረሱ መነሻ የእንስሳት ሥጋ መሸጫ ስፍራ ነው መባሉን ተከትሎ አንዳንድ ግዙፍ የቻይና ከተሞች የድመት እና የውሻ ሥጋ ሽያጭን አግደው ነበር።
