October 27, 2023 – Konjit Sitotaw
ኢሰመኮ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ያወጣው መግለጫ በተሳሳተ አረዳድ የተሰጠ ነው አለ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ኮሚሽኑ የትግራይ ተፈናቃዮችን አስመልክቶ “ሐሰተኛ” ሪፖርት አውጥቷል በማለት ትናንት ማምሻውን ያወጣው መግለጫ፤ በተሳሳተ አረዳድ የተሰራጨ የተሳሳተ መረጃ ነው ሲል ገልጿል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት ጥቅምት 15/2016 ባወጣው መግለጫ፤ ኮሚሽኑ ጥቅምት 9/2016 ይፋ ባደረገው ኹለተኛው የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች መብቶች ኹኔታ ሪፖርት ላይ፤ በጦርነት ምክንያት ተፈናቅለው የነበሩ የትግራይ ክልል ተፈናቃዮች በብዛት ወደ መኖሪያ አካባቢያቸው እንደተመለሱ እና ሰብአዊ ድጋፍ እየቀረበላቸው እንደሆነ ተደርጎ የተገለጸው ስሕተት ስለሆነ ሊስተካከል ይገባል ሲል ገልጾ ነበር፡፡
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ከቤት ንብረታቸው በተፈናቀሉበት ወቅት ኮሚሽኑ ይህን ሪፖርት ማውጣቱ፤ “ኃላፊነት የጎደለው” እና “ዓለማቀፉን ኅብረተሰብ ለማሳሳት ሆን ተብሎ የተሠራ” ነው በማለትም ወቅሷል።
የክልሉ አስተዳደር አክሎም፤ ፌደራል መንግሥቱ ወደፊት ተመሳሳይ ሪፖርቶች እንዳይወጡ አስፈላጊውን ርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።
ኢሰመኮ በበኩሉ የክልሉን ጌዜያዊ አስተዳደር መግለጫ ተከትሎ ትናንት ምሽት ባወጣው እርማት፤ ሰሞኑን በወጣው ኹለተኛው አገር ዓቀፍ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሪፖርት ትግራይን አስመልክቶ የተሳሳተ መረጃ ማካተቱን አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ዓመታዊ የአገር ዉስጥ ተፈናቃዮች መብቶች ኹኔታን አስመልክቶ ባወጣው በሪፖርት፤ በሰሜኑ ጦርነት የተፈናቀሉ በርካታ ሰዎች ወደቀያቸው እንደተመለሱና ጅምሩ መልካም ርምጃ እንደሆነ ገልጾ ነበር።
“ለሪፖርቱ የተሠራው ጥናት ትግራይን አያካትትም ነበር” ያለው ኮሚሽኑ፤ የተሳሳተውን መረጃ ከክልሉ አስተዳደር ጋር በመተባበር እንደሚያጠራው ገልጿል።
በዚህም መሠረት ኮሚሽኑ ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች ጋር የተነጋገረ መሆኑን በዛሬው ዕለት ዳግመኛ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በሪፖርቱ ከሰኔ ወር 2014 እስከ ሰኔ ወር 2015 ያለውን ጊዜ እና በአፋር፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማእከላዊ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ሶማሊ ክልሎች የሚሸፍን መሆኑን ማስረዳቱን አዲስ ማለዳ ከመግለጫው ተመልክታለች።
የትግራይ ክልል በዚህ የጊዜ ወሰን ሊካተትበት ያልቻለበት ምክንያት ሪፖርቱ በተጠናቀረበት ወቅት ክልሉ በጦርነት ሳቢያ ተደራሽ ስላልነበር፣ እንዲሁም የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ኹኔታ የሚሸፍን ሌላ የክትትል ሥራ እየተካሄደ በመሆኑ እና ከዚህ ጋር ተያያዥ በሆኑ ምክንያቶች መሆኑንም ገልጿል።
በተጨማሪም በሪፖርቱ የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ተፈናቅለው የነበሩ በርካታ ሰዎች ወደቀያቸው የተመለሱ መሆኑን የተገለጸው፤ በጦርነቱ ምክንያት ከአፋር እና አማራ ክልሎች ተፈናቅለው የነበሩትን ሰዎች የሚመለከት መሆኑ አመላክቷል።
ሆኖም ኮሚሽኑ በተቻለ አቅም እና የጸጥታ ኹኔታው በፈቀደ ጊዜ ኹሉ ተደራሽ በሆነ መልኩ የሚያደርገውን የምርመራ እና ክትትል ሥራ የሚቀጥል መሆኑን ገልጿል።
